ወልዋሎ ከአማካዩ ጋር እንደሚቀጥል ሲያሳውቅ ረዳት አሰልጣኝ ጨምሮ አዳዲስ ሹመቶች አከናውኗል

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከክለቡ ሊለቅ እንደሆነ ሲነገር የቆየው ራምኬል ሎክ ከቡድኑ ጋር እንደሚቀጥል ሲያስታውቅ ምክትል አሰልጣኝ እና የአስተዳደር ሹመቶች አከናውኗል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ድሬዳዋ ከተማን ለቆ ወልዋሎን በመቀላቀል በመጀመርያው ዙር በአስራ ሦስት ጨዋታዎች ተሳትፎ በማድረግ በ1035 ደቂቃዎች ቢጫውን ማልያ ለብሶ የተጫወተው ይህ አማካይ ወደ ሌሎች ክለቦች ያመራል ተብሎ የሚወራውን ነገር ከእውነት የራቀ እንደሆነ የክለቡ የቡድን መሪ አቶ ሀዲ ሰዊ ገልፀዋል። ተጫዋቹ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጥሩ ፍላጎት ልምምድ እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ሀዲ ሰዊ ገልፀዋል። “ተጫዋቹ ከክለባችን ጋር ይቀጥላል፤ ከቀናት በፊት ክለቡን ተቀላቅሎ ልምምድ እየሰራም ይገኛል።” ብለዋል።

ቡድኑ መሪው ጨምረውም በቀጣይ ቀናት ክለቡን ለማጠናከር ተጨማሪ ዝውውሮች ለማድረግ በሂደት መሆናቸው ገልፀዋል።

ከወልዋሎ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ክለቡ በርካታ ለውጦች አድርጓል። ከዚህ ቀደም በቡድን መሪነት እና ምክትል አሰልጣኝ ቡድኑን ያገለገሉት አቶ አብርሀ ተዓረ የክለቡ ገቢ አሰባሳቢ ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ ምክትል አሰልጣኝ የነበሩት ኮማንደር ኪዳነ ሀፍተ በሥራ አስከያጅነት ተመድበዋል። በሥራ አስከያጅነት ሲሰሩ የቆዩት አቶ አሸናፊ አማረ ደግሞ የአዲሱ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ ምክትል ሆነው መሾማቸውን ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

© ሶከር ኢትዮጵያ