የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር ክለቦች ዳሰሳ – ሲዳማ ቡና

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንደኛውን ዙር ዳሰሳ የምንዘጋው በመጨረሻዎቹ ሳምንታት መሻሻል በማሳየት በ24 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ይዞ ዙሩን ባጋመሰው ሲዳማ ቡና ይሆናል።

የውድድር ዘመኑ ጉዞ

በሊጉ በውጤትም ሆነ በስብስብ ደረጃ የተረጋጉ ከሚባሉት ክለቦች አንደኛው የሆነው ሲዳማ ቡና በክረምቱ ወሳኝ ተጫዋቾቹን በማቆየት እምብዛም ዝውውር ላይ ሳይሳተፍ መቐለ ላይ የተደረገውን የትግራይ ዋንጫ በማሸነፍ ነበር ወደ ውድድር የገባው።

በመጀመርያው ሳምንት ወደ ሶዶ በማቅናት በወላይታ ድቻ 2-0 ተሸንፎ ዓመቱን የጀመረው ሲዳማ ቡና በሁለተኛው እና ሦስተኛው ሳምንት ስሑል ሽረ (በሜዳው) እና ጅማ አባ ጅፋርን (በገለልተኛ ሜዳ) በማሸነፍ ወደ ቀድሞው አስፈሪነቱ የተመለሰ ቢመስልም በአራተኛው ሳምንት በሜዳው በቅርብ ተፎካካሪው መቐለ መሸነፉ መልሶ ተነሳሽነቱን አቀዝቅዞታል። በመቀጠል ሀዋሳን ማሸነፍ ቢችልም ባልተለመደ ሁኔታ በተከታታይ በሜዳው በድሬዳዋ እና ከሜዳው ውጪ በሆሳዕና መሸነፉ ሲዳማ በዓምናው የብቃት ደረጃ ላይ አይገኝም የሚሉ አስተያየቶች እንዲበረክቱ አድርጎት ነበር። በ8ኛ ሳምንት ባህር ዳርን አሸንፎ በድጋሚ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች በቡና እና ፋሲል የተሸነፈ ሲሆን ወልዋሎን በአስደናቂ ጨዋታ 5-0 ረተው ወደ አስፈሪነታቸው የተመለሱ ቢመስሉም በቀጣዩ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ መራር የ6-2 ሽንፈት ተጎንጭተዋል።

እስከ ቅዱስ ጊዮርጊሱ ሽንፈት ድረስ ወጥ አቀቀም ማሳየት የተሳነውና በአስራ ሁለቱ ሳምንታት አንድ ጊዜ ብቻ መረቡን ያላስደፈረው ቡድኑ የኋላ ክፍሉ ላይ ፈጣን ጥገና በማድረግ በተከታታይ አዳማ ከተማ፣ ወልቂጤ (ከሜዳ ውጪ) እና ሰበታ ከተማን በማሸነፍ ነጥቡን 24 አድርሶ መሪዎቹን በቅርብ ርቀት እየተከተለ የመጀመርያውን ዙር ማጠናቀቅ ችሏል።

የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር

ዓምና ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው በወጥ አቋም የዘለቀው ሲዳማ ቡና ዘንድሮ የተዳከመ ይመስላል። ዓምና በዚህ ወቅት በ30 ነጥቦች ሁለተኛ የነበረው ቡድን ዘንድሮ በ6 ነጥቦች ዝቅ ባለ ሲሆን ዓምና በአጠቃላይ 6 ጨዋታ ብቻ የተሸነፈው ቡድን ዘንድሮ ቁጥሩን ከወዲሁ 7 አድርሷል። የተቆጠረበት ጎልም ከዓምናው በእጥፍ የበለጠ ሆኗል። የዘርዓይ ሙሉ ቡድን ዘንድሮ ያሻሻለው ነገር ቢኖር ጎል ማስቆጠር ነው። ከዓምናው በ5 የበለጡ ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

የቡድኑ አቀራረብ

በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመራው ቡድን በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች በአንዱም አቻ ያልተለያየ ብቸኛ ቡድን ያደርገዋል። ይህም ምንም እንኳን አጋጣሚ ሆኖ ወይም ሌሎች ጉዳዮች ቢኖሩም የቡድኑን ማጥቃት እና ማጥቃት ላይ ስላተኮረው አጨዋወታቸው የሚነገርን ነገር ይኖራል። የአጥቂዎቻቸውን አቅም ይበልጥ ለመጠቀም በማሰብ 4-3-3 / 4-2-3-1 አደራደር ይዞ ወደ ሜዳ የሚገባው ቡድኑ በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጭ ማጥቃት ተቀዳሚ እቅዱ ስለመሆኑ መናገር ይቻላል። በዚህም ከሦስቱ አማካዮች አንደኛው ይበልጥ ለአጥቂዎቹ በመጠጋት አራት ተጫዋቾች የማጥቃት መስመሩን አስፈሪ አድርገውታል።

በግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ መሳይ አያኖ እና ፍቅሩ ወዴሳ የሚጠቀመው ቡድኑ በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ በስብስብ ውስጥ የሚገኙትን ሦስቱንም የተጠቀመ ሲሆን ከኃላ አራቱ ተከላካዮች ላይ ተደጋጋሚ ለውጦችን ሲያደርግ ይስተዋላል። እንደ ቡድን ደካማ የመከላከል አወቃቀር ያለው ቡድኑ በተለይ የመሐል ተከላካዮቹ በዚሁ ድክመት እጅጉን ተጋላጭ በመሆናቸው ለበርካታ ስህተቶች ሲዳረጉ ይስተዋላል። በዚሁ የመሀል ተከላካዮች ጥምረት ላይ ግርማ በቀለ፣ ጊትጋት ኮች፣ ሰንደይ ሙቱኩ፣ ክፍሌ ኪአ እና ግሩም አሰፋን እያፈራረቁ ሲጠቀሙ ይስተዋላል። ይህም ለቡድን ውህደት እና ግንባታ መሰረት በሆነ በዚህ ቦታ መፍትሄን በመሻት የሚደረጉ ተደጋጋሚ ለውጦች አለመረጋጋትን ከመፍጠር በዘለለ የችግር መንስኤ ሲሆኑ ይስተዋላል።

በተመሳሳይ በመስመር ተከላካይ ሚና በወጥነት ቡድኑን የሚያገለግሉ ተጫዋቾች የሉትም ብሎ መናገር ይቻላል። ዮናታን ፍሰሃ፣ ግሩም አሰፋ፣ አማኑኤል እንዳለ እንዲሁም ተስፉ ኤልያስ በቀኝ እና ግራ መስመር ተከላካይነት ሚና ቡድኑን ያገለግላሉ። እምብዛም የማጥቃት ተሳትፏቸው በበጎነት የማይጠቀሰው እነዚሁ የመስመር ተከላካዮች የቡድኑ አጨዋወት የመስመር ተከላካዮችን ከመገደቡ ጋር ተዳምሮ በመከላከሉ ላይ ያመዘነ ሚናን ሲወጡ ይስተዋላል።

በተከላካይ አማካይ ሚና ቡድኑን በቋሚነት እያገለገለ የሚገኘው ዮሴፍ ዮሐንስ የቦታ አረዳድ ችግር ቢኖርበትም ከፍ ባለ ብርታት እንደቡድን ደካማ የመከላከል አደረጃጀት ላለበት ቡድን ነገሮች ከዚህ የከፉ እንዳይሆኑ ከፍተኛ መስዋዕትነት ሲከፍል ይስተዋላል። ከእሱ ፊት በ8 ቁጥር ሚና የሚጫወቱት አበባየሁ ዮሐንስ እና ዳዊት ተፈራ በተለይ ወደ ሁለቱ ፈጣን የመስመር አጥቂዎች ያነጣጠሩ ኳሶችን ወደ መስመር በማሰራጨት ረገድ አይነተኛ ሚና ሲወጡ ኳሱ ቡድኑ ሲያጣ ያላቸው ተሳትፎ ግን እጅግ አናሳ ሲሆን ይስተዋላል።

ሦስቱ የቡድኑ አጥቂዎች አዲስ ግደይ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና የረገዙ ቦጋለ ፍጥታቸውን በመጠቀም ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉና እንዲሁም በተለዋዋጭ የቦታ አያያዝ ተገማች ሳይሆኑ ከመስመር እያጠበቡ በመግባት ለተጋጣሚዎች ፈተና ሲሆኑ ይስተዋላል።

ጠንካራ ጎን

እንደ አጠቃላይ የተሻለ የማጥቃት ሒደት ባለቤት የሆነው ቡድኑ በተለይ ሦስቱ የአጥቂ መሰመር ተሰላፊዎች በሚዋልል እንቅስቃሴ ከተከላካይ ጀርባ የሚገኙ ክፍት ቦታዎችን እንዲሁም ከመስመር በመስበር ተጋጣሚ ቡድንን ለመበታተን የሚያደርጉት ጥረት እጅግ ድንቅ የሚባል ነው ፤ ሶስቱ ተጫዋቾች መጠነኛ የአጨራረስ ችግር ቢኖርባቸውም የቡድኑ ትርታ ናቸው ብሎ መግለፅ ይቻላል።

ሌላኛው የቡድኑ ጥንካሬ የሆነውና አለመሸነፍ ተቀዳሚ ምርጫቸው ያደረጉ ቡድኖች በበዙበት ሊግ ውስጥ እንደ ሲዳማ ቡና አይነት በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጭ በጀብደኝነት አጥቅተው ለማሸነፍ የሚጫወቱ ቡድኖች ሲገኙ ትልቅ እውቅና መስጠት ተገቢ ይሆናል። በ15 ሳምንት የሊጉ ጉዞ ምንም ጨዋታ በአቻ ውጤት ያልፈፀመው ቡድኑ ይህ ድፍረቱ ሊበረታታ ይገባል።

ደካማ ጎን

በርካታ ግቦችን የሚያስቆጥረው ቡድኑ በአንፃሩ ከሚያስቆጥረው በላይ በቀላሉ ግቦችን ሲያስተናግድ ይስዋላል። እንደ ቡድን በቁጥር በዝቶ በመከላከል ረገድ እጅግ ደካማ የሆነው ቡድኑ በተጋጣሚ የማጥቃት ሽግግሮች ወቅት በቀላሉ በቁጥር ሲበለጡና ግቦችን ሲያስተናግዱ ይስተዋላል። ምንም እነኳን በሊጉ የመጨረሻ ሳምንታት የመሻሻል ምልክቶችን ቢያሳይም በዚህ ረገድ በሁለተኛው ዙር ይበልጥ ተሻሽሎ መቅረብ ይኖርበታል።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

በመጀመርያው ዙር ደካማ የተከላካይ መስመር የነበራቸው ሲዳማ ቡናዎች በሁለተኛው ዙር ጥሩ ጉዟቸው ለማስቀጠል በተከላካይ ክፍላቸው ላይ ለውጦች ማድረግ የግድ ይላቸዋል። ከሌሎች የቡድኑ ክፍሎች አንፃር ሲታይ ደካማ የመከላከል አደረጃጀት ያላቸው ሲዳማዎች በያዝነው የዝውውር መስኮት የመሐል ተከላካይ ማስፈረም አልያም አሁን በቀጠሉበት መሻሻል ካልዘለቁ ችግሩ ለተፎካካሪነት በሚያደርጉት በጉዞ ላይ እንቅፋት መሆኑ ስለማይቀር ለክፍተቱ በጊዜ መፍትሔ መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

ሌላው በመጀመርያው ዙር በርካታ የማጥቃት አማራጮች የነበሩት ቡድኑ በሁለተኛው ዙርም ይህን ጥሩ ጎን ማስቀጠል ይኖርበታል። በመስመር አጨዋወት እና ከመሐል ሜዳ ባሉት ፈጣሪ አማካዮች ቡድናቸውን ለማዋቀር ጥረት ያደረጉት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በሁለተኛው ዙር ይህ ቡድን ተገማች እንዳይሆን ያደረገውን ለውጥ ማስቀጠል እንዳለበት ይታመናል።

የአንደኛው ዙር ኮከብ

ዳዊት ተፈራ፡ ዘንድሮ በሲዳማ ውጤት ትልቅ ድርሻ ያለው ዳዊት ለሚቆጠሩት አመዛኞቹ ጎሎች መነሻ በመሆን የቡድኑ ኮከብ ሆኖ አጋማሹን አጠናቋል። አብዛኛው ጊዜ በመስመር የሚጫወተውን ቡድን የማጥቃት ሚዛን በመጠበቅ ድንቅ የሆነው ባለ ክህሎቱ አማካይ የመጨረሻ ኳሶቹ ጥራት የቡድኑን የፈጠራ አቅም ከፍ አድርጎታል። ለቡድኑ ማጥቃት ክፍል ንፁህ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የማይቸገረው ዳዊት በአሰልጣኙ አጨዋወት ወሳኝ ሚና እየተሰጠው ይገኛል።

በቡድኑ ከዳዊት ተፈራ ውጪ ወሳኝ ግቦች እያስቆጠረ የሚገኘው አጥቂው ይገዙ ቦጋለ እና አማካዩ አበባየሁ ዮሐንስም ሌሎች የቡድኑ ኮከቦች ነበሩ።

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች

አማኑኤል እንዳለ፡ ባለፈው ዓመት ወደ ዋናው ቡድን ቢያድግም ዘንድሮ እድል እያገኘ ያለው አማኑኤል የተሰጠውን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ቀጣይ የቡድኑ ተስፋ መሆኑ እያሳየ ይገኛል። በመስመር አጥቂነት እና በመስመር ተከላካይነት መጫወት የሚችለው አማኑኤል በውድድር ዓመቱ ጥሩ ከመንቀሳቀስ አልፎ ሦስት ግቦችም ማስቆጠር ችሏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ