ከፍተኛ ሊግ | ለገጣፎ መሪነቱን የሚያሰፋበትን አጋጣሚ ሲያመክን ደደቢት ከሜዳው ውጪ አሸንፏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ 11ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታ ደብረ ብርሀን እና አዲስ አበባ ላይ ተካሂደው ሰ/ሸ/ደ/ብርሀን ከለገጣፎ ለገዳዲ ነጥብ ሲጋሩ ደደቢት በአንጋፋው አጥቂ መድኃኔ ታደሰ ብቸኛ ጎል ከሜዳው ውጭ አሸንፏል።

ደብረ ብርሀን ላይ የተካሄደው ተጠባቂ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። በኳስ ቁጥጥር ረገድ ተሽለው የታዩት ለገጣፎዎች ከጨዋታው ጅማሮ አንስተው በተደጋጋሚ ወደ ደብረ ብርሀን የግብ ክልል ሲደርሱ ተመልክተናል። በ10ኛው ደቂቃም የከፍተኛ ሊግ ውድድርን በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየመራ የሚገኘው የለገጣፎው አጥቂ ልደቱ ለማ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ፊት በመግባት በተሞከረ ጥሩ ሙከራ ጣፎዎች የመጀመሪያ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ከደቂቃዎች በኋላም ከመስመር ተሻጋሪ ኳስ ተመስገን አዳሙ ጥሩ ኳስ አምስት ከሀምሳ ውስጥ አግኝቶ በቀላሉ ጎል መሆን የሚችል እድል አግኝቶ ወደ ውጭ የሰደዳት ኳስ ለገጣፎዎችን መሪ ማድረግ የምትችል መልካም ዕድል ነበረች።

ባለሜዳዎቹ ደብረ ብርሀኖች ቀጥተኛ አጨዋወት በመምረጥ በሁለት ኳስ ንክኪ ወደ ጎል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ብዙም የተሳካ እንዳልነበረ መመልከት ችለናል። ያም ቢሆን በአንድ አጋጣሚ የጣፎ ተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ ነፃ ኳስ ሰለሞን አጋሮ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አስቀድመው እንደወሰዱት ብልጫ ጎል ማስቆጠር የሚገባቸው እንግዶቹ ለገጣፎዎች በ20ኛው ደቂቃ የመስመር አጥቂው አብዲሳ ጀማል የተቀበለውን ኳስ ወደ ሳጥኑ በመግባት በጥሩ አጨራረስ የመጀመርያውን ጎል በማስቆጠር እንግዶቹን መሪ ማድረግ ችሏል።
እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ያልቻሉት ለገጣፎዎች ብልጫ የወሰዱበት እንቅስቃሴ ማስቀጠል አልቻሉም። በአንፃሩ ባለሜዳዎቹ ደብረ ብርሀኖች በተለይ በቆሙ ኳሶች የጣፎን መረብ ለመጎብኘት የጣሩት ጥረት ተሳክቶላቸው በ40ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ የተጣለ የቅጣት ምትን ኳስን ቢንያም ፀጋዬ ከተከላካዮች መሐል በግንባሩ መቶ ባለሜዳዎቹን አቻ የምታደርግ ጎል አስቆጥሯል።


ከእረፍት መልስ ተዳክመው የቀረቡት ጣፎዎች በባለ ሜዳዎቹ ደብረ ብርሀን በጎል ሙከራ እረገድ ብልጫ ተወስዶባቸዋል። ሰለሞን አጋሮ የለገጣፎ ተከላካዮች የሚሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ጥሩ አጋጣሚ ማግኘት ቢችልም ከውሳኔ ችግር በተከላካዮች ተደርቦ ወደ ውጭ ሊወጣበት ችሏል። 68ኛው ደቂቃ ደብረ ብርሀኖችን መሪ ማድረግ የሚችል አጋጣሚ ግብጠባቂው ፍስሀ ረዲ በፍጥነት ያስጀመረውን ኳስ ይዘው በመግባት ሙሉቀን ተስፋዬ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት የሚያስቆጭ ነበር። ብዙም ሳይቆይ በድጋሚ ከቀኝ መስመር በፍጥነት ወደ ሳጥን የገቡት ባለሜዳዎች በብሩክ ግርማ አማካኝነት የሞከሩት የጣፎው ግብጠባቂ አንተነህ ሀብቴ ወደ ውጭ አውጥቶባቸዋል።

የለገጣፎ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝን የተመለከቱት የለገጣፎው አሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ የተጫዋች ለውጥ ቢያደርጉም ግልፅ የማግባት አጋጣሚ የፈጠሩት በአንድ አጋጣሚ ነበር። አብዲሳ ጀማል ከግራ መስመር ያሻገረውን ፋሲል አስማማው ራሱ መጠቀም ሲችል ወደ ኃላ ለአንዋር ሰጥቶት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። የነበራቸውን ብልጫ አጠናክረው ከመጠቀም ይልቅ አቻነቱን የፈለጉት የደብረ ብርሀን አሰልጣኝ እዮብ ማለ የጥንቃቄ አጨዋወትን በመከተል ሰዓት ከማባከን ጋር ተደምሮ ጨዋታውን አሰልቺ ወደ ሆነ መልክ ቀይሮት አንድ አቻ በሆነ ውጤት እንዲጠናቀቅ ሆኗል።

አዲስ አበባ ላይ ደደቢትን የገጠመው አቃቂ ቃሊቲ 1-0 ተሸንፏል። ደደቢት ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ሦስት ነጥቦች ሰብስቦ ደረጃውን እንዲያሻሽል የረዳችውን ጎል ያስቆጠረው አንጋፋው አጥቂ መድኃኔ ታደሰ ነው።

©ሶከር ኢትዮጵያ