ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቅርቡ ዝግጅቱን ይጀምራል

በ2020 የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ በቅድመ ማጣርያ ቡሩንዲን በድምር ውጤት 7-1 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቅርቡ ዝግጅቱን ይጀምራል።

በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ አንደኛ ዙር የማጣሪያ የመጀመርያ ጨዋታውን በባህርዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም መጋቢት 13 ቀን ዚምባብዌን ይገጥማል። በደርሶ መልስ ጨዋታ ቡሩንዲ ከረታው ስብስባቸው ጥቂት ተጫዋቾች ላይ ለውጥ በማድረግ ቡድኑን ለማጠናከር እንዲያግዛቸው ከኢ/ወ/ስ/አካዳሚ፣ መከላከያ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ጌድዮ ዲላ አዳዲስ ተጨማሪ ተጫዋቾችን በማካተት ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ እና ጨዋታቸውን በሚያደርጉበት ባህር ዳር ከተማ ዝግጅታቸውን ለመጀመር ጥያቄያቸውን ለፌዴሬሽኑ አቅርበዋል።

በቀጣይ ለተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅቱን የሚጀምረው ብሔራዊ ቡድኑ ዚምባብዌን ድል የሚያደርግ ከሆነ ቀጣይ ተጋጣሚው ከቦትስዋና እና ደቡብ አፍሪካ አሸናፊ ጋር እንደሚሆን አስቀድሞ የወጣው መርሐ ግብር ይጠቁማል።

© ሶከር ኢትዮጵያ