ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ስሑል ሽረ

ከሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ቀን ጨዋታዎች አንዱ የሆነውና ኢትዮጵያ ቡና ስሑል ሽረን የሚያስተናግድበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ሳምንታት አራት ነጥቦች አግኝተው ፋታ ያገኙት ቡናማዎቹ በሜዳቸው ያላቸውን ጥሩ ክብረ ወሰን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የኢትዮጵያ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አቻ አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ

ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥሩ መሻሻል ያሳዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሒደት የተጫዋቾች የግል ስህተት ቢቀንሱም የነገው ተጋጣሚያቸው ሽረ ተጋጣሚን ጫና ውስጥ በማስገባት ረገድ የተሻለ በፈጣን ተጫዋቾች የተገነባ ቡድን እንደመሆኑ በነገው ጨዋታ ቡድኑ የቅብብል ስኬቱ ከማሻሻል አልፎ በጫና ውስጥ የመጫወቱን ክህሎት ከፍ ማድረግ ይጠበቅበታል።

ከዚህ በተጨማሪ የነገው ተጋጣሚ ስሑል ሽረ ባለፉት የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች እንደተከተለው ወደ ግብ ክልሉ አፈግፍጎ እና ጥቅጥቅ ብሎ ይጫወታል ተብሎ ስለ ሚጠበቅ ቡናዎች ጠጣሩን ቡድን አስከፍቶ የግብ ዕድል ለመፍጠር ይቸገራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ስለዚህም ቡድኑ በአጨዋወቱ ንፁህ የግብ ዕድል ለመፍጠር የመቸገሩ ዕድል የሰፋ ስለሆነ በጨዋታ ሒደት የሚያገኛቸው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በአግባቡ መጠቀም የተሻለ ምርጫው ነው።

ቡናዎች በነገው ጨዋታ በቅጣትም በጉዳትም የሚያጡት ተጫዋች የለም።

የስሑል ሽረ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አቻ አቻ አሸነፈ ተሸነፈ

በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሳምንታት ተከታታይ ነጥቦች ጥለው ነጥባቸውን ከፍ የማድረግ ዕድላቸው ያባከኑት ስሑል ሽረዎች ከአሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ጋር በስምምነት ከተለያዩ በኋላ አዲስ አሰልጣኝ ዛሬ ቢቀጥሩም በረዳት አሰልጣኞቹ እየተመሩ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ ተብሏል።

በመጀመርያው ዙር ጠንካራ የመልሶ ማጥቃት እና ጠጣር ቡድን የነበራቸው ስሑል ሽረዎች በነገው ጨዋታ አጨዋወቱን ከሚከተሉት ዋና አሰልጣኙ ውጪ ወደ ጨዋታው እንደ መግባታቸው የተለየ አቀራረብ ይኖራቸዋል የሚል ግምት ቢኖርም ቡድኑ ከመጠነኛ ለውጥ በስተቀር በአጨዋወትም ሆነ በአደራደር ለውጥ ያደርጋል ተብሎ አይጠበቅም።

በዚህም ቡድኑ የተለመደው የሜዳ ውጭ ጠጣር አቀራረቡ መርጦ ይገባል ተብሎ ሲጠበቅ የወሳኙ ተጫዋቻቸው ዓብዱለጢፍ መሐመድ በጨዋታው አለመኖር ግን በቡድኑ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩ አይቀርም። ሆኖም ቡድኑ ዲዲዬ ለብሪ እና ዮናስ ግርማይን ከቅጣት መልስ ማግኘቱ ወሳኝ ተጫዋቹን ላጣው ቡድን ጥሩ ዜና ነው።

በጨዋታው ለማጥቃት የሚደፍር እና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ አልሞ የሚገባ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብለው የማጠበቁት ሽረዎች የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው በተሻለ ጥራት መተግበር እና ደካማው የአጨራረስ ብቃታቸው ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል።

ስሑል ሽረ በነገው ጨዋታ ዓብዱለሒፍ መሐመድን በቅጣት (አምስት ቢጫ) አያሰልፉም። በአንፃሩ ዮናስ ግርማይ ከጉዳት ዲዲዬ ለብሪን ከቅጣት መልስ አግኝተዋል።

እርስ በእርስ ግነኙነት

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሦስት ጊዜ ተገናኝተው ሽረ ሁለቱን ጨዋታዎች ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና አንድ አሸንፏል። ሦስቱም ጨዋታዎች በ1-0 ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።

– በመጀመርያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ስሑል ሽረ በዲዲዬ ለብሪ ጎል 1-0 ማሸነፉ ይታወሳል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ተክለማርያም ሻንቆ

አሕመድ ረሺድ – ፈቱዲን ጀማል – ወንድሜነህ ደረጀ – አሥራት ቱንጆ

ታፈሰ ሰለሞን – አማኑኤል ዮሐንስ – ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን

ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – ሀብታሙ ታደሰ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ምንተስኖት አሎ

ዐወት ገብረሚካኤል – ዮናስ ግርማይ – አዳም ማሳላቺ – ረመዳን የሱፍ

ነፃነት ገብረመድኅን – አክሊሉ ዋለልኝ

ዲዲዬ ለብሪ – ያስር ሙገርዋ – መድሃኔ ብርሃኔ

ብሩክ ሐድሽ

© ሶከር ኢትዮጵያ