ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

ሀዋሳ ላይ የሚደረገውን የሲዳማ ቡና እና የወላይታ ድቻን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከወጣ ገባ አቋም በኋላ በጥሩ ሁኔታ የሊጉን አጋማሽ ያገባደዱት ሲዳማ ቡናዎች ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት እና ሁለተኛ ዙሩን በአሸናፊነት ለመጀመር አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የሲዳማ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

እስካሁን በተደረጉ 15 የሊጉ ጨዋታዎች ምንም የአቻ ውጤት ያላስመዘገበው ሲዳማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ቀድሞ ብቃቱ የተመለሰ ይመስላል። በተለይ ቡድኑ ኃይሉን ሙሉ ለሙሉ ተጠቅሞ በማጥቃት በጎ ነገሮችን ለራሱ ማምጣት ጀምሯል። ከምንም በላይ ቡድኑ ከተከላካይ ጀርባ መሮጥ የሚችሉ ፈጣን ተጨዋቾችን ከወገብ በላይ በመያዙ ውጤታማ ሆኗል። ይህንን ተከትሎ ቡድኑ በነገው ጨዋታም የቀድሞ አቀራረቡን በመከተል ከሜዳው 3 ነጥብ ይዞ ለመውጣት ይጥራል።

28 ግቦችን ተጋጣሚ ላይ በማሳረፍ ቀዳሚ የሆነው ቡድኑ ነገም የኋላ ክፍላቸው በጉዳት ለሳሳው ድቻዎች ፈተና ሊሆን ይችላል። በተለይ በሚዋልል እንቅስቃሴ ቦታዎችን በየቅፅበቱ የሚቀያይሩት የቡድኑ አጥቂዎች ለጨዋታው ድምቀት ሊቸሩት ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ከመሐል ወደ መስመር በሚሰራጩ ኳሶች አደጋዎችን ለመፍጠር እንደሚታትር ይገመታል።

በአንደኛው ዙር የሊጉ መርሐ ግብር ከፍተኛ ግብ የማስተናገድ ችግር የነበረበት ቡድኑ ነገም ከዚህ ችግሩ ካልታረመ በደጋፊው ፊት ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል። በተለይ ቡድኑ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በአግባቡ የማይመክት ከሆነ እጁን በቀላሉ ሊሰጥ ይችላል።

ባለሜዳዎቹ ግርማ በቀለን በአምስት ቢጫ ምክንያት በነገው ጨዋታ አያሰልፉም።

የወላይታ ድቻ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

በአዲሱ አሰልጣኛቸው እየተመሩ ወደ ጥሩ ጎዳና የተሸጋገሩት ወላይታ ድቻዎች በዓመቱ አጋማሽ በተደረገ ጨዋታ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም እና የያዙትን መልካም መንገድ ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

በከፍተኛ የመነሳሳት ስሜት ውስጥ ሆነው ጨዋታዎችን እያደረጉ የሚገኙት ድቻዎች በነገውም ጨዋታ በጥሩ ሞራል ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል። በተለይ አሰልጣኝ ደለለኝ ቡድኑን ከያዙት በኋላ በፍላጎት የሚጫወት እንዲሁም በአላማ የሚንቀሳቀስ እና የተደራጀ ቅርፅ ያለው ሆኗል።

ከተጋጣሚያቸው ሲዳማ ቡና አጨዋወት ጋር የሚመሳሰል የጨዋታ መንገድ ያላቸው ድቻዎች በነገው ጨዋታም እንደ ከዚህ ቀደሞቹ መርሐ ግብሮች በመስመር ለመስመር በሚያደርጉት ፈጣን እንቅስቃሴ ተጋጣሚን እንደሚፈትኑ ይገመታል። በተለይ ቸርነት እና እዮብ የሜዳውን መስመር ይዘው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እጅግ ሲዳማን ሊፈትን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ የቡድኑን 50% (8) ጎል ያስቆጠረው ባዬ ገዛኸኝ ወደ መስመር እየወጣ የሚያደርጋቸው እና በተጨዋቾች መካከል በመገኘት የሚፈጥራቸው እድሎች ድቻዎችን ሊጠቅም ይችላል።

ፈጣን አጥቂዎች ያሉት ቡድን ሲያገኝ የሚቸገረው ድቻ በነገው ጨዋታ ፈተና ውስጥ እንዳይገባ አስግቷል። በተለይ ቡድኑ ወደ መሐል ሜዳ ተጠግቶ የሚከላከል ከኖነ በፈጣኖቹ የሲዳማ አጥቂዎች ሊቀጣ ይችላል።

ደጉ ደበበ በገጠመው መጠነኛ ጉዳት መድረሱ አጠራጣሪ ሲሆን አጣማሪው ውብሸት ዓለማየሁም በጉዳት አይኖርም። አዲስ ፈራሚዎቹ መሐመድ ናስር እና አማኑኤል ተሾመ ደግሞ ከቡድኑ ጋር ወደ ሀዋሳ ተጉዘዋል፡፡ ሌሎቹ አዲስ ፈራሚዎች አበባው ቡጣቆ እና ሚካኤል ለማ ግን ለዚህ ጨዋታ አይደርሱም ተብሏል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 13 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና ስድስት ጨዋታ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን በአምስት ጨዋታ አቻ ተለያይተው ወላይታ ድቻ 2 ጊዜ አሸንፏል።

– በሁለቱ ግንኙነት እስካሁን 20 ጎሎች ሲቆጠሩ ሲዳማ ቡና 12፣ ወላይታ ድቻ 8 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

አማኑኤል እንዳለ – ክፍሌ ኪአ – ጊት ጋት – ግሩም አሰፋ

ዳዊት ተፈራ – ዮሴፍ ዮሐንስ – አበባየው ዮሐንስ

አዲስ ግደይ – ይገዙ ቦጋለ – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

መክብብ ደገፉ

ፀጋዬ አበራ – አንተነህ ጉግሳ – ሙባረክ ሽኩር – ያሬድ ዳዊት

በረከት ወልዴ – ተመስገን ታምራት – እድሪስ ሰዒድ

እዮብ ዓለማየሁ – ባዬ ገዛኸኝ – ቸርነት ጉግሳ

© ሶከር ኢትዮጵያ