ሪፖርት | ብርቱካናማዎቹ ሁለተኛውን ዙር በድል ጀምረዋል

በ16ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ድሬዳዋ ከተማ ላይ ሀዋሳን የገጠመው ድሬዳዋ 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን ያሻሻለበትን ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክቷል።

ድሬዳዋ ከተማዎች በ15ኛው ሳምንት መቐለ 70 እንደርታን ሲገጥሙ ከተጠቀሙበት ስብስባቸው ውስጥ አዲስ ፈራሚያቸው ሄኖክ ኢሳይያስን በፈርሀን ሰዒድ እንዲሁም ፍሬው ጌታሁንን ደግሞ በሳምሶን አሰፋ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል። በመጀመሪያው ዙር መገባደጃ ከፋሲል ከነማ ጋር ተገናኝተው የነበሩት ሀዋሳዎች ደግሞ በዳንኤል ደርቤ ምትክ ሄኖክ አየለን የተጠቀሙበት ቅያሪ ብቸኛው ለውጣቸው ነበር።

በርካታ ደጋፊ በተገኘበት ጨዋታው የባለሜዳው ቡድን በአባይ ግድብ ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መፈክሮችን አሳይተዋል።

ፌደራል ዳኛ ወልዴ ንዳው በመራው በዚህ ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ በእንግዳው ቡድን በኩል ማራኪ እንቅስቃሴ ያልታየበት ኃይል የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ የተበራከተበት ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ተሽለው የተገኙት ባለሜዳዋቹ ጎል ያስቆጠሩት ገና በ14ኛው ደቂቃ ነበር። በብርቱካናማዎቹ መለያ አብቦ የዋለው ሄኖክ ኢሳይያስ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ሪችሞንድ ኦዶንጎ በግንባሩ በመግጨት የድሬዳዋ ከተማን የድል ደውል በጊዜ ማሰማት ችሏል።

እንግዶቹ በመጀመሪያው አጋማሽ በራሳቸው ሜዳ በቁጥር በዝተው የሚነቀሳቀሱበትን ትዕይንት ያሳዩ ሲሆን ከራሳቸው ሜዳ የሚወነጨፉ ኳሶችን ለመጠቀም ጥረት ቢደርጉም ስኬታማ አልነበሩም። በ40ኛው ደቂቃ በዚሁ መንገድ የተገኘውን አጋጣሚ መስፍን ታፈሰ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

እምብዛም የጠራ የግብ ዕድል ያልፈጠሩት ሀዋሳዋች በ37ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል። ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ኤልያስ ማሞ ላይ በተሰራ ጥፋት ፍፁም አጨቃጫቂ የነበረው ፍፁም ቅጣት ምት ነው ወይስ ቅጣት ምት’ የሚለው ጉዳይ በዕለቱ ዳኛ ቅጣት ምት መሆኑ ሲወሰን ቢንያም ጥዑመልሳን በአግባቡ በመጠቀም ወደ ግብነት ለውጦት የግብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።

በራሳቸው ሜዳ ተገድበው በመጫወታቸው ለድሬዳዋ ከተማ በተደጋጋሚ ወደ ግብ ክልላቸው እንዲመጡ የፈቀዱላቸው ሀዋሳዎች ረጃጅም ኳሶችን በማሻገር ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢደርጉም ሳያሳካላቸው ቀርተዋል፤ ጨዋታውም በድሬዳዋ 2-0 መሪነት ወደ ዕረፍት አምርቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ድሬዳዋዎች ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት የመረጡት አጨዋወት ሰምሮላቸዋል። በአንፃሩ ኃይቆቹ ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ መንቀሳቀስ በቻሉበት በዚህ አጋማሽ ሙከራዎች ቢያደርጉም ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በ47ኛው ደቂቃ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በረጅሙ ወደ ጎል የተመታውን ኳስ ብሩክ በየነ ሳይታሰብ ከተከላካዮች መሀል ነፃ ኳስ አግኝቶ ቢመታውም ወደ ውጪ ሊወጣበት ቻለ እንጂ ጥሩ የጎል አጋጣሚ ነበር። እንዲሁም ዘላለም ኢሳያስ የመታው ኳስ ጎል ከመሆን ለጥቂት ነበር የወጣበት።

ድሬዳዋች ከ50ኛው ደቂቃ ጀምሮ ጫና ፈጥረው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ኃይቆቹ በመልሶ ማጥቃት ከግብ ክልላቸው ኳሱን በማራቅ ወደነበሩበት እንቅስቃሴ ተመልሰዋል። በ56ኛው ደቂቃ አማረ በቀለ ሁለት የሀዋሳ ተከላካዮችን በማለፍ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ቢመልሰውም በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ቢንያም ጥዖመልሳን ለራሱ ሁለተኛ ሉቡድኑ ደግሞ ሦስተኛ ግቡን አስቆጥሯል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ብርቱካናማዋቹ ጥቃት ስንዘራውን እንዲቀንሱ በሚስገድድ ሁኔታ ተፈጥሮባቸዋል። በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ ወደፊት የሚሄደውን የኃይቆቹን ጥቃት ሲያስቆም የነበረው ፍሬድ ሙሸንዲ በ70ኛው ደቂቃ በመሀል ሜዳ ላይ ቲክኒካል ጥፋት በመስራቱ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ተገዷል። ተጫዋች የተቀነሰባቸው ባለሜዳዎቹ በመልሶ ማጥቃት የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት እየፈተናቸው ቆይቶ በጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ቢጫወቱም በ85ኛው ደቂቃ መስፍን ታፈሰ ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት አልደፈር ብሎ የዋለው የድሬዳዋን በር አስከፍቷል። ሆኖም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይታይበት ባለሜዳዎቹ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ሳምንት ውጤት ሰምሮላቸው ጨዋታውን በ3-1 አሸናፊነት አጠናቀዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ