የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 0-1 መቐለ 70 እንደርታ

በአብዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም በተካሄደ የ16ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መቐለዎች ከሜዳቸው ውጪ ሀዲያ ሆሳዕናን 1-0 ከረቱ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።


“ከሜዳችን ውጭ አሸንፈን መውጣታችን ዕድለኛ ያደርገናል” ገብረመድህን ኃይሌ (መቐለ 70 እንድርታ)

ከሜዳችሁ ውጭ አሸንፋችኋል። የጨዋታው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል ?

ጨዋታው ከባድ ነበር። ምክንያቱም እነርሱ ላለመውረድ እየተጋሉ ነው ያሉት እኛ ደግሞ ከፊት ያሉት እንዳይርቁን በዚህ መሐል ያለው ፍትጊያ ጨዋታውን ከባድ አድርጎታል። ከሜዳችን ውጭ አሸንፈን መውጣታችን ዕድለኛ ያደርገናል። የኳስ ፍሰቱን፣ አጠቃላይ የጨዋታውን እንቅስቃሴን በዚህ ሜዳ ላይ መግለፅ በጣም አስቸጋሪ ነው።

ስለዋንጫ ፉክክሩ

ቡድናችን ከመሪዎቹ ውስጥ ነው ያለው። ሁለተኛው ዙር ምን እንደሚፈጠር አታውቅም። ከወዲሁ ብዙ ነገር መናገር ባይቻልም ፉክክሩ ውስጥ አለን በዚህ አቋማችን በቀጣይም ይቀጥላል።



” እግርኳስ ነው ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም፤ ደጋፊዎቻችን በተቻለ አቅም ከጎናችን ሊቆሙ ይገባል” ፀጋዬ ኪ/ማርያም (ሀዲያ ሆሳዕና)

ስለ ጨዋታው

እንዳያችሁት ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ነው። ሁለታችን በሁለት ጫፍ ያለን ክለቦች ነን። መቐለ ለዋንጫ የሚፎካከር እኛ ደግሞ በሜዳችን ከታች ካለንበት ርቀት ወደ ላይ ጠጋ ማለት ዕቅዳችን ነበር። ጨዋታው ተመጣጣኝ ነገር ቢታይበትም በእነርሱ በኩል ብስለት እና ልምድ ከእኛ ጋር ልዩነቱ ይታይ ነበር። እንደ ምክንያት ባላቀርብም በመጀመርያው አጋማሽ አግኝተነው የነበረው ፍፁም ቅጣት ምት ልጆቻችንን ሊያነሳሳ የሚችል ግልፅ የሆነ በእጅ የተነካ ኳስ ፍ/ቅ/ምት እየተገባን የተከለከል ነው። በዚህ ጨዋታ በዋናው ዳኛ እና በረዳቱ በኩል የተቀናጀ ዳኝነት አይቻለው ብዬ አላስብም። ውጤታችንን በፀጋ እንቀበላለን። በሜዳችን እየተጫወትን ደጋፊዎቻችንን የሚያስቆጣ ነገር ትንሽ ዳኞቻችን ቢያስቡበት መልካም ነው። በተረፈ በልምድ በአጨዋወት ስህተት ተሸንፈናል። ከድክመታችን ተነስተን አርመን ለቀጣይ ጨዋታ እንዘጋጃለን።

ተጫዋቾቹ ላይ ጫና እንዳለ በሜዳ ውስጥ እየተመለከትን እንገኛለን። አዲስ ያስፈረምካቸው ተጫዋቾች በዚህ ቡድን ላይ ለውጥ ያመጣሉ ብለህ ታስባለህ?

ባሉን ክፍተቶች ላይ ተጨማሪ አምስት ተጫዋቾች አምጥተን ቡድኑ ውስጥ አካተናል። ሁለት ተጫዋቾች በቅርቡ ይካተታሉ። ፎፋና የነበረውን የወረቀት ሁኔታዎችን ጨርሷል። ተስፋዬ አለባቸው እዚህ ከመጣ በኃላ ታሞ ነው ያልገባው። ሙሉ የቡድን ስብስባችንን ስናገኝ ወደ ጥሩ አቋም እንመለሳለን። እግርኳስ ነው ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም። ደጋፊዎቻችን በተቻለ አቅም ከጎናችን ሊቆሙ ይገባል። ከድክመቶቻችን ተነስተን በቀሪ ጨዋታዎች በፕሪምየር ሊጉ ለመቆየት ጥረት እናደርጋለን።

©ሶከር ኢትዮጵያ