የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 5-3 ወላይታ ድቻ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ ስድስተኛው ሳምንት ጨዋታ ሲዳማ ቡና በሜዳው ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ወላይታ ድቻን 5ለ3 ካሸነፈበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ክለብ ዋና አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡

” ሜዳችን ላይ አጥቅተን ነው የምንጫወተው” ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ስለጨዋታው እና ስለተቆጠሩት ግቦች

የመከላከል ችግራችን ዛሬ ላይ የለም። ለምሳሌ የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር የመሳይ በረኛው አቋቋም ነው፤ ስለዚህ የተከላካይ ስህተት አንለውም። ሌላው የኳስ አጀማመር ችግር ነው፡፡ በመከላከሉ በፊት ከነበረው ዛሬ የተሻልን ነን። ጎል ገባ እንጂ ስህተቱ በተቃራኒው ነው፡፡

ሜዳህ ላይ ስትጫወት አጥቅተህ ነው የምትጫወተው። አጥቅተህ በምትጫወትበት ሰዓት ተቃራኒ ቡድን ወደ መከላከሉ ይመጣል፡፡ የመስመር ወይም የፊት አጥቂዎቻችን የሚያገኙትን ያገቡ ነበር፤ እዚህ ላይ ተሳክቶልናል፡፡ ምክንያቱም ማጥቃት አንደኛ አማራጫችን ስለሆነ ሜዳችን ነው አሸነፈን መውጣት ስላለብን። ከዛ ውጪ ፉልባኮቹ ተደርበው መጥተው ነው ጫና የሚፈጥሩት። መስመር አጥቂዎቻችንን እንጠይቃለን በዚህ መንገድ ነው ጎሉ የገባብን። ከሜዳ ውጪ ግን ያልኩትን እንደ ሁለተኛ አማራጭ እንጠቀማለን። የመስመር አጥቂዎች ተመልሰው ተከላካዩን አግዘው እንዲጫወቱ ማድረግ እንችላለን፡፡ ግን አንደኛ ዙር ላይ በነበረው አይደለም ግቦች የተቆጠሩብን። ይሄ ደግሞ የሚቀረፍ ስለሆነ እናስተካክላለን፡፡

በገባው መጠን ስለባከኑ ጎሎች

70 ፐርሰንት ያገኘናቸውን ተጠቅመናል። 80 ወይም 90 ለማድረግ ደግሞ መስራት ነው፡፡ ግን ያገኘናቸውን በሚገባ ተጠቅመናል ብዬ አስባለሁ። እና ብዙም የሳትነውም የለም። አልፎ አልፎ ያገኘናቸው ዕድሎችን ካለመጠቀም በቀር የምናገኘውን አጥቂዎች እንደ አጥቂ እያገቡ ነው፡፡ ስለዚህ ግን አሁንም እዚህ ላይ ላይ መጠናከር አለብን ።

” የተከላካይ ስህተት ግቦች እንዲቆጠርብን ሆኗል” ደለለኝ ደቻሳ (ወላይታ ድቻ)

ስለ ጨዋታው

“በቅድሚያ ሲዳማ ቡናዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ወደ ጨዋታው ስመለስ የመጀመሪያው ጎል ሁሉን ነገር ቀይሮታል፡፡ ልጆቻችንን ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት አድርገን ነበር። ግን የተከላካይ ስህተት ግብ እንዲቆጠርብን ሆኗል። በሁለተኛው አጋማሽ የተፈጠረው በቡና ጨዋታ እንደነበረው አይነት ነው፡፡ ከኃላ ተደራጅቶ ያለ መከላከል ዋጋ አስከፍሎናል፡፡

መጀመሪያ 4-2-3-1 አጨዋወትን ነበር ይዘን የገባነው። ኳስ ስንይዝ 4-1-4-1 እንጠቀማለን፡፡ በዛ አጨዋወት ለመጫወት አስቤ ነበር። ቀይሬ ያስወጣሁት አማካዩ ተመስገን የድካም ስሜት ስለተሰማው እሱን ቀይሬ 4-1-4-1 ለመጫወት ሞክረናል። ነገር ግን ያው ጎል ስለተቆጠረብን ለማጥቃት ወደ ፊት ስንሄድ የነሱ አጥቂዎች ፈጣኖች ናቸው፡፡ በመልሶ ማጥቃትም አስቆጥረውብናል፡፡ ይሄ እግር ኳስ ነው፡፡ መስራት አለብን፤ በተለይ ማግባቱ ላይ እና ኃላ ክፍል ላይ።

© ሶከር ኢትዮጵያ