ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

የ17ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ሲደረጉ የወልቂጤ ከተማ እና የአዳማ ከተማን ብቸኛ የነገ መርሃ ግብር እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

የሁለተኛው ዙር የሊጉ መርሐ ግብርን በድል የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች በቅጣች ምክንያት የሜዳቸውን ጨዋታ በአዲስ አበባ በሚያደርጉት ጨዋታ ያገኙትን የአሸናፊነት መንፈስ ላለመልቀቅ እና ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ 9 ሰዓትን ይጠባበቃሉ።

የወልቂጤ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አቻ ተሸነፈ አቻ አሸነፈ

በአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው የሚመራው ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የአጥቂዎቹን ፍጥነት በመጠቀም ለተጋጣሚዎቹ ከፍ ያለ ስጋት ሲደቅን ይስተዋላል። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ አስደናቂ ድልን የተቀዳጀው ቡድኑ የነገው ተጋጣሚው አዳማ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በተወሰነ መልኩ ከተከላካይ ጀርባ የሚገኝን ክፍት ቦታ ለማጥቃት የሚታትር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ባሳለፍነው ጨዋታ የተመለከትነውን በትይዩ የሚንቀሳቀስ የኃላ አራት ተከላካይ መስመር በዚህኛው ጨዋታ ላይ የመጠቀማቸው ነገር የሚቀር አይመስልም።

በአንፃሩ ተጋጣሚያቸው አዳማ ከተማ ከሜዳው ውጭ በሚያደርጋቸው ጨዋታ ወደ ኃላ መሰብሰብን ተቀዳሚ ምርጫው የሚያደርግ ከመሆኑ አንፃር ወልቂጤዎች መሀል ሜዳ ላይ የተወሰነ የፈጠራ ብቃታቸው ላይ መሻሻሎችን አድርገው መቅረብ ይኖርባቸዋል። ከምንም በላይ በነገው ጨዋታ ላይም ወጣቶቹ አጥቂዎች ጫላ ተሺታ እና አህመድ ሁሴን ለአዳማ ከተማ ተከላካዮች ከፍተኛ ስጋት ይደቅናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመከላከል አወቃቀሩ ጥንካሬ ተጠቃሽ የሆነው ወልቂጤ ከተማ አሁንም የተከላካይ መስመሩ በተለያዮ ጉዳዮች መታመሱን ቀጥሏል። በዚህኛው ሳምንት ደግሞ ሌላኛውን የመሀል ተከላካይ ዳግም ንጎሴን በ5 ቢጫ የሚያጣ ይሆናል። ይህም ከቶማስ ስምረቱና ዐወል መሐመድ አለመኖር ጋር ተዳምሮ ለአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ተጨማሪ የቤት ስራን የሰጠ ሆኗል።

የአዳማ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አቻ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ባህር ዳር በማቅናት በፍሲል ከነማ የተሸነፉት አዳማ ከተማዎች በቶሎ ወደ አሸናፊነት ለመምጣት እና ያሉበትን ደረጃ ለማሻሻል ወልቂጤ ከትመዋል።

ለጥንቃቄ ቅድሚያ የሚሰጠው የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን በተለይ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት ከኳስ ጀርባ በመሆን ጊዜውን ያሳልፋል። በተለይ ፍጥነት ያላቸው የተጋጣሚ አጥቂዎችን ቡድኑ በሚጋፈጥበት ጊዜ በይበልጥ ወደ ራሱ የግብ ክልል በመጠጋት ይጫወታል። ይህንን ተከትሎ በነገውም ጨዋታ ቡድኑ ከተከላካዮች እስከ አጥቂዎች ያለውን የፊትዮሽ ርዝመት በማጥበብ ጨዋታውን እንደሚከውን ይገመታል።

በሁለት የተከላካይ አማካዮች የመጫወት ልማድ ያለው ቡድኑ በነገውም ጨዋታ በርከር ያሉ የአማካይ ተጨዋቾችን ወደ ሜዳ እንደሚያስገባ ይታሰባል። በተለይ ይህ ጉዳይ ለተከላካዮቹ ሽፋን ለመስጠት እና የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ለመቆጣጠር እንዲረዳው ሊያደርግ ይችላል።

እንደተለመደው የቡድኑ የወገብ በላይ ተጨዋቾች በነገው ጨዋታ ለባለሜዳዎቹ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ። በተለይ በፈጣን የመስመር ላይ ሽግግሮች አደገኛ የሆኑት ቡልቻ እና በረከት ቡድናቸውን በመልሶ ማጥቃት ሊጠቅሙ ይችላሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን እና የአግድሞሽ ኳሶችን ቡድኑ አዘውትሮ ስለሚጠቀም ተጨዋቾቹ ፍሬያማ ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም የቡድኑ የቆመ ኳስ አጠቃቀሙ ጥሩ ስለሆነ ግቦችን በዚህ አማራጭ ሊያገኝ ይችላል።

አዳማዎች ሱሌማን ሰሚድን በጉዳት ደረጀ ዓለሙ ደግሞ በግል ጉዳይ ምክንያት በነገው ጨዋታ አያሰልፉም። ባሳለፍነው ሳምንት የቡድኑ ጨዋታ ሜዳ ያልነበረው ዳዋ ሆቴሳ ከመጠነኛ ጉዳቱ ማገገሙ እና ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ተነግሯል።

እርስ በርስ ግንኙነት 

በሁለተኛው ሳምንት አዳማ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ተገናኝተው አዳማ ከተማ 1-0 ማሸነፉ ይታወሳል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ይድነቃቸው ኪዳኔ

ይበልጣል ሽባባው – መሀመድ ሻፊ – ዐወል ከድር – አቤነዘር ኦቴ

አሳሪ አልማህዲ – በረከት ጥጋቡ – ሙሀጅር መኪ

ጫላ ተሺታ – ሳዲቅ ሼቾ – አህመድ ሁሴን

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ጃኮ ፔንዜ

ሱሌይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – መናፍ ዐወል – ተስፋዬ ነጋሽ

አማኑኤል ጎበና – አዲስ ህንፃ

ቡልቻ ሹራ – ከነዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ

ዳዋ ሆቴሳ

© ሶከር ኢትዮጵያ