የአንድ ቤተሰብ ሦስት ተጫዋቾች ወግ

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በተገታበት በዚህ ወቅት በፕሪምየር ሊጉ እየተጫወቱ የሚገኙ ሦስት ወንድማማቾች ጊዜያቸውን በምን መልኩ እያሳለፉ እንደሚገኙ ያወጉናል።

የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ የኮሮና ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ሲባል ከተቋረጠ አንድ ወር ማስቆጠሩ ይታወሳል። ምንም እንኳ ስፖርታዊ ውድድሮች ይቋረጡ እንጂ የስፖርት ቤተሰቡ በበጎ ተግባር ላይ በመሳተፍ ከፍተኛ የገንዘብ፣ የምግብ እህሎች እና የተለያዩ የቁሳቁሶችን ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ እያደረጉ መቆየታቸው ይታወቃል። ተጫቾችም በቤታቸው ጊዜያቸውን በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ። ከነዚህ ውስጥ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተጫወቱ የሚገኙት ሦስት ወንድማማቾች ሽመክት ጉግሳ (ፋሲል ከነማ) ቸርነት ጉግሳ እና አንተነህ (በወላይታ ድቻ) የአንድ ቤተሰብ አካል እንደመሆናቸው መጠን በአንድ ላይ በመሆን ጊዜያቸውን በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ። ታዲያ ይህን አጋጣሚ አስመልክተን ከቤተሰቡ አንዱ አባል ከሽመክት ጉግሳ ጋር ሶከር ኢትዮጵያ አጭር ቆይታ አድርጋለች።

ውድድሮች መቋረጣቸው የፈጠረባችሁ ስሜት?

በጣም ከባድ ነው። በእግርኳስ ላደገ እና እየተጫወተ ለሚገኝ ሰው ውድድሩ መቋረጡ እና ከእግርኳስ መራቅ በጣም ይከብዳል። ያም ቢሆን በሽታውን መቆጣጠርና መከላከል የሚቻለው ሰዎች መሰባሰባቸውን ሲያቆሙ በመሆኑ ይህ ችግር እስኪያልፍ ድረስ ውድድሮች መቋረጣቸው ተገቢ እንደሆነ እናስባለን። ከሁሉም ነገር በላይ ጤና የሚቀድም በመሆኑ።

ውድድሩ ቢቋረጥም እናንተ አንድ ላይ በመሆናቹ ጊዜውን በምን አይነት እንቅስቃሴ ታሳልፉታላቹ ?

ከቤተሰባችን ጋር አብረን ነው ያለነው። ብዙን ጊዜ በጋራ በመሆን ጊዜውን እያሳለፍን እንገኛለን። የልምምድ መርሐግብር አውጥተን ጠዋት ጠዋት ሁሌም አንድ ላይ በመሆን ቤታችን ውስጥ የተለያዩ ልምምዶችን እንሰራለን። በመቀጠል በቂ እረፍት ካደረግን በኃላ የተለያዩ እግርኳሳዊ የሆኑም ያልሆኑም ፊልሞችን እየተመለከትን በእንዲህ ሁኔታ ነው ጊዜውን እያሳለፍን የምንገኘው።

የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በሽታውን ለመቆጣጠር በስፖርቱ የሚገኙ አካላት የተለያዩ መልክቶችን እያስተላለፉ ይገኛሉ። አንተም ወንድሞችህን በመወከል የምታስተላልፈው መልዕክት ካለ?

በመጀመርያ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን መልዕክት ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። በመቀጠል አስገዳጅ ካልሆነ በቀ ከቤት ሳንወጣ እና አካላዊ ርቀታችንን በመጠበቅ በመንቀሳቀስ የእጅ ንፅህናችንን በመጠበቅ ይህ አስቸጋሪ ጊዜ እስኪያልፍ ከሌለው ጋር ተካፍለን እንድንኖር በወንድሞቼ ስም መልክቴን አስተላልፋለው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ