ዜና ዕረፍት | የአርባምንጩ ግብ ጠባቂ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

የአርባምንጭ ከተማ ግብ ጠባቂ ፍሬው ገረመው በቅፅል ስሙ (ሰጌቶ) ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

ተጫዋቹ ከሰሞኑ በጉልበቱ ላይ መጠነኛ ዕጢ ነገር ወጥታበት የነበረ ሲሆን እስከ ትላንት ድረስ ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወት ከቆየ በኋላ ጉልበቱ ላይ ያለችውን ዕጢ ለማስወጣት ወደ ህክምና ስፍራ አምርቶ ክትትል በማድረግ ላይ ሳለ ዛሬ ማለዳ ህይወቱ ሊያልፍ መቻሉን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ እና ከጓደኞቹ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የአማሟቱ ሁኔታን ለማረጋገጥም በጥልቀት ምርመራ ስለሚያስፈልገው ጉዳዩ በህግ መታየት ጀምሯል፡፡

1985 በአርባምንጭ ከተማ የተወለደው ይህ ወጣት ግብ ጠባቂ የልጅነት የእግር ኳስ ህይወቱን በአርባምንጭ ከተማ የታዳጊ ፕሮጀክቶች ካሳለፈ በኃላ በአርባምንጭ ዙሪያ በሚገኝ ጊዶሌ በተባለ ክለብ የክለቡ ህይወቱን ጅማሮ አድርጓል፡፡ ከመጀመሪያ ክለቡ በመቀጠል በጂንካ ከተማ፣ ሻሸመኔ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ በመጫወት አስደናቂ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ በተለይ ደቡብ ፖሊስ ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ አስተዋጽኦው ከፍተኛ የነበረ ሲሆን በክለቡም በሁለት አጋጣሚዎች ተጫውቷል። በመሀል ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ካመራ በኃላ ከ2010 እስካለፈው ዓመት ድረስ በደቡብ ፖሊስ በመጫወት ቆይታን አድርጓል፡፡

በቅፅል ስሙ ሰጌቶ እየተባለ የሚጠራው ግብ ጠባቂው በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በተለያዩ የከፍተኛ ሊግም ሆነ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ቢፈለግም ምርጫውን ተወልዶ ላደገባት አርባምንጭ ከተማ በማድረግ በክለቡ የዘንድሮው ወጥነት ላለው የውጤት ጉዞው የራሱን የጎላ ድርሻ እያበረከተ ይገኝ ነበር።

ሶከር ኢትዮጵያ በተጫዋቹ ህልፈት የተሰማትን ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰቦቹ፣ ለክለቡ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች እንዲሁም ለስፖርት ቤተሰቡ በሙሉ መፅናናትን እንመኛለን፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ