የዘጠናዎቹ ኮከቦች | ከቺቾሮ .. ባሎኒ .. እስከ አዲስ አበባ ስታዲየም የዘለቀ የእግርኳስ ጉዞ

የእግር ኳስ ሕይወቱን በኤርትራው የኤርትራ ጫማ ክለብ ጀምሮ በሀገሪቱ ውስጥ ትልቅ ስም ላላቸው ጉና ንግድ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት እና ለወጣት እና ዋናው ብሄራዊ ቡድን መጫወት የቻለው አማካዩ ኤፍሬም ዘርዑ በ1990ዎቹ ከታዩ ድንቅ አማካዮች አንዱ ነው።

በለጋ ዕድሜው በአስመራ እግር ኳስ መጫወት ጀምሮ በዛ ወቅት በሁለቱ ሀገራት በተፈጠረው መቃቃር በየመን በኩል ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ የመጣው ይህ አማካይ በዛን ወቅት ገብረኪሮስ አማረ፣ ዳዊት ዕቁባይ፣ ያሬድ ሰገድ እና ሌሎች የደመቁበት የባሎኒ ስታዲየም የተወዳጅነት ዙፋን ለመቆናጠጥ ብዙ ጊዜ እንዳልፈጀበት በዛን ወቅት እግርኳሱን በአንክሮ የሚከታተሉ ይናገሩለታል። ከተጫዋቹ ጋር ሰፊ ቆይታ ያደረገችው ሶከር ኢትዮጵያም ቆይታውን በሁለት ክፍሎች የምታቀርብላቹህ ይሆናል። ለዛሬ የመጀመርያው ክፍል እነሆ!

ስለ ትውልድ ቦታው እና የታዳጊ ቡድን ቆይታው

ትውልዴ እና እድገቴ አስመራ ነው። እግርኳስን መጫወት የጀመርኩትም አስመራ ተማሪ እያለው ነው። ስምንተኛ ክፍል እያለሁ ለሁለተኛም ለሦስተኛም ቡድን ሳልጫወት ነው በቀጥታ ከትምህርት ቤት ወደ ዋናው ቡድን የተዘዋወርኩት። የመጀመርያ ክለቤም በዛን ወቅት በኢትዮጵያ ደረጃ ታዋቂ የነበረው ኤርትራ ጫማ ነው። ተማሪ ከሆንክ በክለብ ደረጃ መጫወት አይቻልም ነበር፤ በዛ ምክንያት ልክ ትምህርት ቤት ሲዘጋ ነው ክለቡን የተቀላቀልኩት። በወቅቱ በአእምሮ ካልሆነ በስተቀር በአካል ብቃት ደረጃ ብቁ አልነበርኩም፤ ክብደቴም 46 ኪግ. ብቻ እንደነበር አስታውሳለው።

በ1990 የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ የመጀመርያ ጨዋታዬን አደረግኩ። በዓመቱም የሊግ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ከቡድኑ ጋር አንስቻለው። ትምህርት ቤት ቅዳሜ ተዘጋ ከሁለት ቀን በኋላ ክለቡን ተቀላቅዬ በመጀመርያው ጨዋታ ሁለት ለግብ የሆኑ ኳሶች አቀበልኩ። በዛ ዓመትም በአፍሪካ ውድድር ጨዋታ አድርጌያለሁ። ከኤርትራ ጫማ እስከ 1991 ተጫውቼ ከዛ በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ወሰንኩ። በየመን በኩል አድርጌም ወደ ኢትዮጵያ መጣው።

ስለ ኢትዮጵያ የመጀመርያ ዓመት ቆይታው እና ፈተናዎቹ

በ1992 ወደ ኢትዮጵያ ከመጣው በኋላ የመጀመርያው ክለቤ ጉና ንግድ ነበር። ፈተናው ብዙም አልነበረም። በመጀመርያው ዓመቴ ለኢትዮጵያ ቡና የመጫወት ዕድል ገጥሞኝ የነበረ ቢሆንም በአንዳንድ ነገሮች ሳይሳካ ቀርቷል።

ከኤርትራ ነጋሲ ደስታ ከሚባል ጓደኛዬ ነበር በየመን በኩል የመጣሁት። እንዳልኩህ ፈተናው ከባድ ባይባልም እንዲው ቀላል ግን አልነበረም። በሜዳም ከሜዳ ውጭም አንዳንድ ፈተናዎች ነበሩ። የቋንቋ እና አኗኗር መጠነኛ ፈተና ነበር። ከዛ ውጭም በጉና በመጀመርያዎቹ ጊዜያት የግራ ተመላላሽ አድርገው ነበር ያጫወቱኝ። ለቦታው አዲስ ስለነበርኩና በአካል ብቃትም ብቁ ስላልነበርኩ ትንሽ ከብዶኝ ነበር። መቐለ “ባሎኒ” ላይ ብዙም የመሰለፍ ዕድል አይሰጠኝም ነበር። አንድ ቀን ገብቼ ጥሩ ከተንቀሳቀስኩ በኋላ ግን በደጋፊው ጥሩ ተቀባይነት ነበረኝ፤ ከዛ በኃላም በቋሚነት ነበር ዓመቱን የጨረስኩት። ከዛ ዓመት በኃላ ደግሞ ወደ ትራንስ ኢትዮጵያ ነው ያመራሁት።

ስለ ትራንስ ኢትዮጵያ የተሳካ ቆይታው

በትራንስ ቆይታዬ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። የነበረው ስብስብ እና የቡድን ስሜት በጣም ጥሩ ነበር። ትራንስ ስብስቡ ሳይበተን ለሁለት እና ለሦስት ዓመታት ቢቆይ የሊግ ዋንጫዎች ለተከታታይ ዓመታት ማንሳት ይችል ነበር። ቡድኑ በሂደት ነው የተገነባው ላለመውረድ እንጫወት ነበር፣ መሀል ሰፋሪም ነበርን። ከዛ ደግሞ ለዋንጫ የሚፎካከር አሪፍ ቡድን ነበረን። ቡድናችን ለሁለት እና ከዛ በላይ ዓመታት በሜዳው ተሸንፎ አያቅም ነበር። በዛ ላይ ጥሩ የአሸናፊነት መንፈስ የነበረው ቡድን ነበር። በግሌም ጥሩ ግዜ ነበር ያሳለፍኩት፤ ለኮከብነት የታጨሁባቸው ግዜያትም ነበሩ። እና በአጠቃላይ ሲታይ በትራንስ የተሳካ እና አሪፍ ቆይታ ነበረኝ።

ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያልተሳካ ቆይታው እና ትራንስን ለመልቀቅ የወሰነበት አጋጣሚ

ትራንስን የለቀቅኩበት ምክንያት ያው እንደ ሌላው ተጫዋች ለትልቅ ክለብ የመጫወት ፍላጎት ነበረኝ። ዋነኛው ምክንያት እሱ ነው ሌላ ምንም ምክንያት የለውም። ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታዬ ደግሞ እንደተጠበቀው ባይሆንም አስከፊ ጊዜ አልነበረም። የተሰራ ሙሉ ቡድን ውስጥ ነበር የገባሁት። በዛ ምክንያት ቶሎ ሰብሬ መግባት አልቻልኩም። ግን ቅድም እንዳልኩህ ቆይታዬ በጣም የወረደ አልነበረም፤ ወደ ጊዮርጊስ ስሄድ ሰው ከኔ ብዙ ጠብቆ ስለነበር ነው። ትራንስ እያለው የበድኑ ቋሚ ተጫዋች ነበርኩ። ጊዮርጊስ ስሄድ ግን በአሰልጣኙ ፍላጎት እየተቀያየርን ነበር ምንሰለፈው (Rotation) በዛ በዛ ምክንያት ነው።
በሁለተኛው የጊዮርጊስ ቆይታዬ ግን እኔን ፈልጎ ያመጣኝ አሰልጣኝ ሚቾ ለቀቀ። የመጣው አሰልጣኝ ደግሞ በደምብ ሊያውቀኝ አልቻለም አጨዋወቴ። ትንሽ ጉዳት እና የክብደት መጨመርም ነበረብኝ። በዛ ምክንያት ሁለተኛው ዓመት እንደምፈልገው አልተንቀሳቀስኩም።

ስለ የኢትዮጵያ ቡና አጭር ቆይታው

ኢትዮጵያ ቡና ለመሄድ ስወስን ከልቤ ያለኝን ለመስጠት በመወሰን ነበር የሄድኩት፤ ምክንያቱም ከዛ ጥሩ ያልሆነ አንድ ዓመት ማገገም ነበረብኝ። ግን በአጋጣሚ በዛን ወቅት በነበረው ያልተረጋጋ ሁኔታ እንደምፈልገው አልሆነም። (1999) በፌደሬሽኑ እና በክለቦች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት የተረጋጋ ነገር አልነበረም። በዛም በሦስት ጨዋታ ብቻ ነበር የቡናን ማልያ አርጌ የተጫወትኩት። በቡና ውጤታማ ያልሆንኩበት ምክንያት ጊዜው አጭር ነበር በመሀል ደግሞ ይቆራረጥ ነበር። በሚቀጥለው ዓመት ግን ክለቡ እንድቆይ ይፈልግ ነበር። (የቡና አሰልጣኝ በወቅቱ ክፍሌ ቦልተና ነበር) እኔ ግን ወደ ትራንስ በድጋሜ መመለስ ነው የፈለግኩት።

ትራንስ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ተመልሶ የነበረው ቆይታ

ትራንስ ለሁለተኛ ጊዜ ተመልሼ የነበረኝ ቆይታ በመጀመርያው ዓመት በጣም ጥሩ ነበር። በሁለተኛው ዓመት ግን ስብስባችን ፈረሰ ውሳኝ ተጫዋቾች ለቀቁ በዛ ምክንያት ቡድኑ ተቸግሮ ነበር። ሚካኤል ደስታ፣ መድሃኔና ታደሰ፣ አማኑኤል ግደይ እና ሌሎች ወሳኝ ተጫዋቾች ቡድኑን ለቀቁ። በዛ ዓመት ደግሞ በወጣቶች የተገነባ ቡድን ነበር። በዛ ዓመት ቡድኑ የአሰራር ክፍተቶች ነበሩበት። የታሰበው በወጣቶች የተገነባ ቡድንም እንደሚፈለገው ውጤት ማምጣት አልቻለም። በሁለተኛው ዙር ግን ተሻሽለን ከዘጠኙ ስድስቱን በማሸነፍ ጥሩ መሻሻል አሳይተን ነበር። ሆኖም በመጨረሻው ሳምንት እኛ ወደ አዳማ ሄደን አዳማ ከተማን ብናሸንፍም በሌላው ስታድየም ሆነ ተብሎ የውጤት መላቀቅ ተደረገና ባልተገባ መንገድ ትራንስ ኢትዮጵያ ወረደ። እንደውም ከተሸናፊው ቡድንም የተቀጡ ተጫዋቾች እንደነበሩ አስታውሳለው። ሁለተኛው ዓመት የትራንስ ቆይታዬ ይህን ይመስላል ጥሩ ቆይታ አልነበረም በብዙ ምክንያት። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ግን እኔ ወደ ደደቢት ከሄድኩ በኃላ በዛው ክረምት ትራንስ በጥሎ ማለፍ ወደ ፕሪምየር ሊግ ተመልሷል።

ከተጫዋቹ ጋር ያደረግነው የመጀመርያው ክፍል ቆይታ ይህንን ይመስላል። በቀጣይም ስለ ደደቢት እና ብሔራዊ ቡድን ቆይታው ሜዳ ውስጥ ገንዘብ ስለተሸለመበት አጋጣሚ እና ከኤርትራ ስለቀረበለት ጥያቄ እና ተያያዥ ጉዳዮች ያደረግነውን ቆይታ በሁለተኛው ክፍል ይዘንላችሁ እንቀርባለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ