ወንድወሰን ሚልኪያስ የት ይገኛል ?

በአዳማ ከተማ በተጫወተባቸው ዓመታት ስኬታማ ቆይታ በማድረግ የሚታወቀው የተከላካይ አማካዩ ወንድወሰን ሚልኪያስ አሁን የት ይገኛል?

ከአርባምንጭ የፕሮጀክት ተመልምሎ ለደቡብ ክልል ውድድር ሀዋሳ ከተማ ላይ ባሳየው ተሰፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በአንጋፋው አሰልጣኝ ሥዩም አባተ መልማይነት ዘጠናዎቹ መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ መድንን መቀላቀል ችሏል። በመድን የጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ በደደቢት እና ኒያላ እስከ 2005 ድረስ ቀጥሎ አቅሙን ወዳሳየበትና ጥሩ ቆይታ ወዳደረገበት አዳማ ከተማ አምርቷል። በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በአጨዋወቱ ከሚወደዱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረው ይህ አማካይ 2006 አዳማ ከተማ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ ትልቁን ሚና ተወጥቷል። በ2007 አዳማ ከተማ በክለቦች የሴካፋ ውድድር (የምስራቅ እና መካከለኛው የክለቦች ዋንጫ) ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝቶ በተወዳደረበት ወቅት ከአጥቂዎቹ ታከለ ዓለማየሁ፣ ቢንያም አየለ ያላነሰ ጎሎችን ከመሐል ሜዳ እየተናሳ ጎል ያስቆጥር እንደነበረም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ይልቁንም በሴካፋ ባሳየው መልካም እንቅስቃሴ በውጪ ሀገር የመጫወት እድል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካለት ቀርቷል። ከአዳማ የሦስት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ትውልድ ከተማው አርባምንጭ በማቅናት ለአንድ ዓመት ከጉዳት ጋር እየታገለ ያልተሳካ ቆይታ አድርጓል። ጥሩ አቅም እንዳለው የሚነገርለት ይህ ተጫዋች ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከእግርኳሱ መድረክ ርቆ መገኘቱን ተከትሎ ይት ይገኛል ብለን አፈላልገን አግኝተነው ይሄን ብሎናል።

” የጉልበት ጉዳት አጋጥሞኝ በምፈልገው ደረጃ እንዳልጫወት ፈተና ሆኖብኛል። አዳማ ከተማን ለማገልገል ስል በተደጋጋሚ የምወስደው መርፌ ጎድቶኛል። አርባምንጭ ከሄድኩ በኋላም በተመሳሳይ ጉዳት አስቸግሮኛል። እርግጥ ነው ሁለቱን ዓመት ከሜዳ ርቄ ቆይቻለሁ፤ ሆኖም እግርኳስ አቁሜያለው ማለት አይደለም። በግሌ ህመሜ እስኪሻለኝ ድረስ ልምምድ በሚገባ እየሰራሁ እገኛለው። ነገር ግን ከምቀመጥ ብዬ በምኖርበት አቃቂ አካባቢ “ቤተል አምልኮ አማኞች” በተሰኘ ተቋም ብዙ ትውልድን ሃይማኖታዊ ትምህርት በማስተማር ከአላስፈላጊ ሱሶች እያወጣው ፈጣሪዬን እያገለገልኩ እገኛለሁ። የጤናዬ ሁኔታ ይስተካከል እንጂ ወደፊት ወደ እግርኳሱ መመለሴ አይቀርም”።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ