“የቡናማዎቹ የፕሪምየር ሊጉ ብቸኛ ዋንጫ ስኬት” ትውስታ በዕድሉ ደረጄ አንደበት

2003 ኢትዮጵያ ቡና የፕሪምየር ሊጉን የመጀመርያ ዋንጫ ሲያነሳ የወቅቱ የቡድኑ አንበል ዕድሉ ደረጄ ጊዜውን ወደ ኃላ አስታውሶ በትውስታ አምዳችን ይናገራል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ ተስፋ ቡድን እግርኳስን በክለብ ደረጃ በመጫወት መነሻውን ያደረገው ታታሪው እና ወደፊቱ ትልቅ አሰልጣኝ ለመሆን እየተጋ የሚገኘው ዕድሉ ደረጄ በአየር መንገድ፣ በታክሲ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫውቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ1998 ሩዋንዳ ላይ የሴካፋ ዋንጫ (የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ) አሸናፊ ከሆነው ስብስብ ውስጥ ነበር። ስኬታማ ቆይታ ወደ አደረገበት ኢትዮጵያ ቡና በመምጣት ለአምስት ዓመታት ቆይታ ቢያደርግም በተለይ አይረሴውን በ2003 ኢትዮጵያ ቡና ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ወዲህ የመጀመርያውን ዋንጫ ሲያነሳ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ትልቁን ሚና ከተወጡ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር። ወደ ኢትዮጵያ መድን በማምራት በአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ እየተመራ 2005 መድን ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ እድሉ ደረጄ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች እንደነበረም ይታወቃል። እግርኳስን ካቆመ በኃላ ወደ አሰልጣኝነቱ ጎራ በመቀላቀል በኢትዮጵያ ቡና ተስፋ እና ዋናው ቡድን የአሰልጣኝነት ህይወቱን የጀመረው እድሉ ቀጥሎም በሰሜን ሸዋ ደብረብርሀን ያሰለጥን እንደነበረ ይታወሳል። በኢትዮዽያ ቡና ደጋፊዎች መቼም የማይረሳውን የ2003 የሊጉን ዋንጫ በአምበልነት ያነሳው ዕድሉ ወደ ኃላ ዘጠኝ ዓመት ተጉዘን ወቅቱን እንዲያስታውሰን በትውስታ አምዳችን የዛሬ እንግዳችን አድርገነዋል።

” በወቅቱ ምንም አታስበውም፤ ዓመታት ሲገፋ ነው ትልቅ ታሪክ እንደሰራህ የምታስበው። ግን ከአሸናፊ ግርማ ጋር በ1998 ለሁለት ዋንጫ እየተጓዝን በነበረበት ወቅት እናወራ ነበር። በቃ ቡና የሆነ የማይታይ እጅ አለበት ዋንጫ አይበላም በማለት ያልተሳካውን ዓመት እናወራለን። ይህ በሒደት በሁሉም ጭንቅላት ውስጥ አለ። 2003 ሊጉን እየመራን እንኳን ፍራቻ፣ ጭንቀት፣ በደጋፊው በአመራሩ ዘንድ በስብሰባም ወቅት ሁሉ ይንፀባረቅ ነበር። ይህ ፍራቻ አልፎ እውን ሲሆን አንዳንዴ ህልም ሁሉ ይመስለኝ ነበር። ትልቅ ስሜት የሚፈጥርብኝ ዋንጫ ነው። ካስታወስክ ስምንት ጨዋታ ሲቀረው ደጋፊው ቡና ዘንድሮ ዋንጫ ይበላል የሚል ተስፋ አድርጎ በየጨዋታዎቹ ሙሉ ለሙሉ ስታዲየሙ ይሞላ ነበር። እኛም የተለየ ትኩረት ሰጥተን በእያንዳንዱ ጨዋታ በጥንቃቄ ተጫውተን በመጨረሻም ዋንጫውን የተቀበልንበት ወቅት የደጋፊው ደስታ፣ የነበረው ሁኔታ በአጠቃላይ አሁን ሳስበው ልዮ ትዝታ ይፈጥርብኛል። በወቅቱ ከቡና ተጫዋቾች ብዙ ጊዜ የተጫወትኩት እኔ በመሆኔና አንበል ከመሆኔ አንፃር የነበረብኝ ሀላፊነት ለመወጣት ከተጫዋቾች ከአሰልጣኙ ጋር በመሆን የሰራናቸው ጠንካራ ስራዎች ይህን ታሪካዊ ዋንጫ እንድናነሳ አድርጎናል”።

የቀድሞ ተጫዋች እና የአሁኑ አሰልጣኝ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በስፖርት ሳይንስ የመጀመርያ ዲግሪ ያለው ሲሆን በአሁኑ ወቅት በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በስፖርት ማኔጅመት ሁለተኛ ዲግሪውን እየሰራ ይገኛል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ