“ኢትዮጵያ ቡና ገቢ የሚያገኝባቸው ምንጮች እየደረቁበት ይገኛል” አቶ ገዛኸኝ ወልዴ (ሥራ አስኪያጅ )

ኢትዮጵያ ቡና የተመሰረተበትን አርባ አራተኛ ዓመት በዐሉን እያከበረ ባለበት ወቅት በክለብ ወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ማብራርያ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ቡና የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ በመቅረብ በዛሬው ዕለት ማብራሪያ የሰጡት የክለቡ ሥራ አስኪያጅ የኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት የውድድሮች ሙሉ ለሙሉ መቋረጣቸው በክለቡ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ እና ክለቡ ያለበትን የፋይናስ ችግር ለመቅረፍ ሊከተለው ስላሰበው አቅጣጫ ይሄን ብለዋል።

“ኢትዮጵያ ቡና እንደሚታወቀው በከተማ መስተዳድር (በመንግስት) ገንዘብ የሚደገፍ ክለብ አይደለም። በራሱ መንገድ ተጣጥሮ ከስፖንሰር ከሚያገኘው ገቢ የሚተዳደር ህዝባዊ መሠረት ያለው ትልቅ ክለብ ነው። ሆኖም ውድድሮች መቋረጣቸው እና እንቅስቃሴ መቆማቸው የገቢ ምንጩ እንደሚደርቅ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ቡና የገቢ ምንጮች

– ከቡና ላኪዎች ማኀበር በዓመት ከ15–20 ሚሊዮን ብር

– ትልቁ የክለቡ ስፖንሰር ሀበሻ ቢራ በዓመት በጥሬ ገንዘብ 18 ሚሊዮን እና ተጨማሪ በዓይነት (የቁሳቁስ)

– የስታዲየም (ከተመልካች) ገቢ

– የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ከደጋፊዎች የምነሰበስበው ገቢ

” እነዚህን መሠረት አድርገን ስንመለከት የሜዳ ገቢው ሙሉ ለሙሉ ቆሟል። ከውድድሩ መቋረጥ በፊት በሜዳችን ካደረግናቸው ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ ከ5.5 ሚሊዮን ብር ከተመልካች ገቢ አግኝተናል። ውድድሩ በመቋረጡ ምክንያት በቀጣይ ከሰባት ጨዋታ ልናገኝ የሚገባውን ገቢ አጥተናል። የቡና ላኪ ሴክተሩ ጋር ተያይዞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የንግድ እንቅስቃሴ እየቆመ በመምጣቱ ከቡና ላኪዎች የምናገኘው ገቢ እየቀነሰ መጥቷል። ሌላው የገቢ ምንጫችን የሆነው ሀበሻ ቢራ በየትኛውም ጊዜ ከክለቡ ጋር አብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ቢያረጋግጥልንም ከታክስ፣ የማስታወቂያ ስራ በመቆሙ እና ከኮረና ወረርሺኝ ጋር ተያይዞ የአልኮን መጠጦች እንቅስቃሴ በመቆማቸው ከስፖንሰራችን የምንፈልገውን ገቢ በሚጠቅሙ ነገሮች ላይ ለማግኘት እክሎች እየገጠሙን ይገኛሉ።

” በአጠቃላይ ያለውን ነገር ስንመዝነው ክለባችን ከላይ በቀረቡ ምክንያቶች እየተነሳ ገቢው እየቀነሰ ይገኛል። በዚህም ከተጫዋቾች ደሞዝ፣ ከለቡ የሚያደርጋቸው የተለያዮ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያደረገ ይገኛል። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ቡና የገቢ የሚያገኝባቸው ምንጮች እየደረቁበት ይገኛል።

” ኢትዮጵያ ቡና ሕዝባዊ ክለብ ነው። በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያ ቡና ያጋጠሙት ፈተናዎችን ተቋቁመውና ከመፍረስ ታድገው እዚህ ያደረሱት ደጋፊዎቹ ናቸው። ይህንንም ጉዳይ መፍታት የምንችለውም በደጋፊዎቻችን እንደሆነ በፅኑ እናምናለን። በቀጣይ አጠቀላይ አሁን ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚገልፅ ሠነድ አዘጋጅተን ከክለቡ ሥራ አመራር እና ከደጋፊ ማኀበር ጋር ተነጋግረን የተለያዮ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ደጋፊውን ወደ ገቢ የምንቀይርበት እና ድጋፍ የሚያደርጉበትን ሥራ እንሰራለን። ኢትዮጵያ ቡና ህዝባዊ ክለብ እንደመሆኑ መጠን የበርካታ ደጋፊዎች ያሉት የመዲናዋ ታላቅ ክለብ ነው። የከተማዋን ገፅታ በበጎ በማስተዋወቅም ትልቁን ድርሻ እየተወጣ ነው። በአዲስ አበባ ባለው በርካታ ደጋፊዎች አማካኝነትም በከተማው ውስጥ በማኀበራዊ፣ በልማት እና በበጎ ተግባሮች ውስጥ እየተሳተፈ መቆየቱ ይታወቃል። ስለሆነም የከተማ አስተዳደር ከዚህ ቀደም የሚያደርግልን መልካም ድጋፍ እንዳለ ሆኖ አሁን ክለቡ ያጋጠውን ችግር ተረድቶ ድጋፍ ሊያደረግ ይገባል።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ