ስለ አንዋር ሲራጅ ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

በኢትዮጵያ እግርኳስ ስማቸው ጎልተው ከሚጠሩ የዘጠናዎቹ ኮከቦች አንዱ አንዋር ሲራጅ ነው። “ትንሹ” እና “ሚስማሩ” በሚሉ ቅፅሎች ይበልጥ ስለሚታወቀው አንዋር ሊያውቋቸው የሚገቡ ጉዳዮችን እናስቃኛችኋለን።

ሜክሲኮ አካባቢ የተወለደው አንዋር በ1986 ነበር የኢትዮ ኤሌትሪክን ታዳጊ ቡድን መቀላቀል የቻለው። ባሳየው ፈጣን ዕድገት እና አብዛኛዎቹ የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች በብሔራዊ አገልግሎት ምክንያት ከሀገር መጥፋታቸውን ተከትሎ ባገኘው መልካም አጋጣሚ ብዙም ሳይቆይ ሳይቆይ ነበር ዋና ቡድንን ለመቀላቀል የቻለው። ገና በ18 ዓመቱ ከኢትዮ ኤሌትሪክ ጋር በ1989 የአዲስ አበባ ሻምፒዮና በ1989 ዋንጫ ያነሳው አንዋር የውድድሩም ኮከብ ተጫዋችነትን ተብሎ ተሸልሟል። ሽልማቱ በፔፕሲ ስፖንሰር አድራጊነት 10ሺ ብር የተሸለመ ሲሆን ይህ ሽልማትም በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ሽልማት ነበር። በወቅቱ ለተከላካዮች ሁሉ እጅግ ፈታኝ የነበሩት አሰግድ ተሰፋዬ እና ሀሰን በሽርን አላፈናፍን ብሎ በመቆጣጠሩ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ አድናቆት እንዲቸረው እና ዕይታ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። አንዋር ትንሹ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ዋንጫን በ1990 እና 1993 ከኤሌትሪክ ጋር ማንሳት ከመቻሉም በተጨማሪ በግሉ በ1992 ደግሞ የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋችነትን ክብር አግኝቷል። ብልህ፣ ባለ አዕምሮ እና የተረጋጋ ተጫዋች መሆኑ የእርሱ መለያዎቹ ሲሆን በ1993 ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የሦስትዮሽ ዋንጫ ማንሳት የቻለ ምርጥ ተከላካይ ነው። በ1994 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በማምራት የሁለት ዓመት ቆይታ ያደረገ ሲሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የማይረሳውና በመጨረሻ ደቂቃ የተገኘው የ1995 ዋንጫን ማንሳት ችሏል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታው በኋላ ወደ የመን በማቅናት ለአምስት ዓመታት መጫወት የቻለው አንዋር በየመንም ከአልሳቅር ክለብ ጋር የሊግ ቻምፒዮን መሆን የቻለ ሲሆን በ2001 ነበር እግርኳስን አቁሞ ወደ ንግዱ ዓለም ያመራው።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አገልግሎቱ ከ18 ዓመቱ ጀምሮ በኢትዮጵያ ታዳጊ ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ለተከታታይ ሰባት ዓመት ያለ እረፍት አገልግሏል። አስገራሚው ነገር በሁለቱ የተለያየ የአጨዋወት ፍልስፍና ባላቸው አንጋፋ አሰልጣኞች ሥዩም አባተ እና አሥራት ኃይሌ ይወደድ የነበረና የእነርሱ ቀዳሚ ምርጫም ነበር። ሌላው አስገራሚው የእግርኳስ ህይወቱ በአንድ ዓመት ውስጥ ለታዳጊ፣ ለኦሊምፒክ እና ለዋናው ብሔራዊ ቡድን የተጫወተ ጠንካራ ተከላካይ መሆኑ ነው። በ1989 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) የታዳጊ የሴካፋ ዋንጫን ያነሳው አንዋር በተለይ በ1994 በሩዋንዳ አስተናጋጅነት የተካሄደውን የሴካፋ ዋንጫን ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በአሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ እየተመራች ከሀገር ውጭ ዋንጫውን አንስታ ስትመለስ የቡድኑ አንበል በመሆን ማገልገሉ ይታወሳል።

ከፊቱ ፈገግታ የማይጠፋው አንዋር በእግርኳስ ህይወቱ መቼም የማይረሳው አጋጣሚ “በ1993 የኢትዮጵያ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን በኢትዮጵያ ቡና 2-0 እየተመራን ሁለት ተጫዋች በቀይ ካርድ ወጥቶብን በጎዶሎ ተጫዋች 3-2 ያሸነፍንበት ጨዋታ ነው” ይላል። የተለያዩ ቅፅል ስሞች ያሉት አንዋር በብዙዎቹ ዘንድ ከአንዋር ያሲን ለመለየት”አንዋር ትንሹ” እየተባለ የሚጠራ ቢሆንም ብዙዎቹ ስለማያውቋት “ሚስማሩ” ስለሚባለው ቅፅል ስሙ ይህን ይናገራል። “ማልዲኒ፣ ሚስማሩ እያሉኝ ሲጠሩኝ አውቃለው። ለምን አንዳሉኝ ብዙም አላውቅም። ይመስለኛል ሚስማሩ ያሉኝ በወቅቱ የነበሩትን ታላላቅ አጥቂዎችን አጥብቄ በመያዜ ሳይሆን እንዳልቀረ እገምታለው። ያም ሆኖ አሁንም ድረስ መለያ ስሜ ሆኖ የቀረው በኢትዮ ኤሌክትሪክ እያለሁ ከእኔ ቀድሞ ይጫወት ከነበረው አንዋር ያሲን እኔን ለመለየት አንዋር ትንሹ ብለው የሰየሙኝን ስያሜ ነው።” ብሏል።

አንዋር ሲራጅ እግርኳስን ካቆመ በኋላ ወደ አሰልጣኝነቱ ጎራ ያልተቀላቀለ ሲሆን በጤና ስፖርት ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ ከእግርኳሱ ባይርቅም በንግዱ ዓለም የተዋጣለት ነጋዴ በመሆን ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ከባለቤቱ ጋር የአራት ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ሲሆን ወንድ ልጁ ምን አልባት ወደ ፊት እግርኳሰ ተጫዋች በመሆን ብቅ እንደሚል ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ