ተስፈኛው ግብጠባቂ ፋሲል ገ/ሚካኤል

ኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎች እምብዛም ዕድል በማያገኙበት ፕሪምየር ሊጋችን ላይ ወደፊት ተስፋ ከተጣለባቸው ግብ ጠባቂዎች አንዱ የሆነው ፋሲል ገብረሚካኤል የዛሬ ተስፈኛ አምዳችን ላይ ይዘን ቀርበናል።

በዳሽን ቢራ በአረንጓዴ መታወቂያ በመጫወት የጀመረው ተስፋኛው ወጣት ግብጠባቂ ፋሲል ገ/ሚካኤል በ2008 በአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ በሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለመጠራት ችሏል። ብሔራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው የግብፅ እና የማሊ የማጣርያ ጨዋታ ላይ ምንም አንኳ የመጀመርያ ተሰላፊ ሆኖ ባይጫወትም ወደ ፊት ተስፋ የሚጣልበት ግብጠባቂ እንደሚሆን በወቅቱ መመልከት ችለናል። ዳሽን ቢራ በ2008 ከፕሪምየር ሊጉ መውረዱ እና ኋላ ላይ መፍረሱ ግብጠባቂው ከ2009-10 ለሁለት ዓመታት ቆይታ ወደ አደረገበት ደደቢት አምርቷል። ደደቢት በሊጉ መውረድ እና ያጋጠመው የፋይናስ ቀውስ ተከትሎ ግብጠባቂው ወደ ከፍተኛ ሊግ አምርቶ ለአንድ ዓመት ለአክሱም ከተማ በ2011 መጫወት ችሏል። ከዳሽን ቢራ አንስቶ አቅሙንና ወደ ፊት የሚኖረውን እድገት ቀድሞ የተረዳው የአሁኑ የሰበታ ከተማ የግብጠባቂ አሰልጣኝ አዳሙ ኑመሮ በዘንድሮ ዓመት ለአዲስ አዳጊው ክለብ ሰበታ ከተማ እንዲፈርም አድርጎት በመጫወት ላይ ይገኛል። በተለይ ወደ ሊጉ መቋረጥ መቃረቢያ ላይ በ16ኛው እና በ17ኛው ሰበታ ያደረጋቸውን ሁለት የሊጉ ጨዋታዎችን በመጀመርያ ተሰላፊነት ያገለገለው ፋሲል እጅግ ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ አሳይቷል። በዛሬው ተስፈኛ ወጣት አምዳችንም ከዚህ ግብጠባቂ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።

” ትውልድ እን እድገቴ ጎንደር ከተማ ነው። የቀድሞ የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ተገኝ እቁባይ በዳሽን ቢራ በአረንጓዴ ቲሴራ እንድጫወት አድርጎ አሳድጎኛል። አቅሜን አውቆ የቀድሞ በዳሽን ቢራ የግብጠባቂ አሰልጣኝ አሁንም በሰበታ ከተማ በግብጠባቂነት እያሰለጠነኝ የሚገኘው አዳሙ ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንድመረጥ ማድረጉ ለዛሬ ማንነቴ ትልቅ አስተዋፆኦ አድርጓል። ሁሌም ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ጠንክሬ መስራቴ እንዳለ ሆኖ ከጋናዊው ምርጥ ግብጠባቂ ዳንኤል አጃይ ጋር አብሮ መስራት በጣም ብዙ ነገር ጠቅሞኛል። እርሱ በእግር መጫወት የሚችል፣ ንቁ እና በጣም ምርጥ ግብጠባቂ ነው። እርሱ ከምነግርህ በላይ ያለውን ከፍተኛ ልምድ እያካፈለኝ እያስተማረኝ ይገኛል። ባልነበረባቸው ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች እንኳ በስልክ እየደወለ በጨዋታ ወቅት ምን ማድረግ እንዳለብኝ ይመክረኝ ነበር። ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አብሬ በመስራት ብዙ ነገሮችን እማራለው ብዬ አስባለው። በሰበታ ጥሩ የመጫወት እድል እያገኘሁ ነው። በተለይ በ16ኛ ሳምንት ከወልዋሎ ጋር የመጀመርያውን የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዬን አድርጌያለው። በመቀጠል ከቅዱስ ጊዮርጊስ የነበረው ጨዋታ ከፍተኛ ክብደት የነበረው ቢሆንም አሰልጣኞቼ የሚሰጡኝን ምክር ተቀብዬ ጎል ሳይቆጠርብኝ በጥሩ አገልግሎት ጨዋታውን መጨረስ ችያለው። ያው በቀጣይ በጨዋታ ብዛት ያለኝን በራስ መተማመን ለማዳበር የማገኘውን እድል እጠቀማለው ስል ሊጉ በኮሮና ቫይረስ ሊቋረጥ ችሏል። ነገ የተሻለ ጊዜ ሲመጣ እራሴን ለማሳየት እጥራለው። ወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የግብጠባቂ ችግር እንደሌለ ጠንክሬ በመስራት በክለብም በብሔራዊ ቡድን ማገልገል እንዲሁም ከኢትዮጵያ ውጭ በመውጣት መጫወትን እፈልጋለው። ዳሽን በነበሩበት ወቀት እነርሱን ለመሆን የምመኛቸው ግብጠባቂ ደረጄ እና ቢንያም የእኔ አርያአ ሲሆኑ አሰልጣኝ ተገኝ እና አዳሞ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ ትልቁን አስተዋፆኦ የተወጡ ስለሆነ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እፈልጋለው”።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ