ስለ ዓለማየሁ ዲሳሳ “ዴልፒዬሮ” ሊያውቋቸው የሚገቡ ዕውነታዎች

እንደነበረው ችሎታ እና አቅም ብዙ ያልተጠቀምንበት የዘጠናዎቹ ኮከብ እና ባለ ክህሎቱ አማካይ ዓለማየሁ ዲሳሳ (ዴልፒዬሮ) ማነው ?

በአንድ ኳስ ቅብብል ብቻ ትልቅ ተጫዋች የመሆን አቅሙን የተመለከተው የቀድሞ ኤሌክትሪክ ታዳጊ ቡድን አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ወዲያውኑ ነበር በ1990 ወደ ታዳጊ ቡድኑ የቀላቀለው። በዓመቱም ፈጣን እድገት አሳይቶ ወደ ዋናው ቡድን አድጓል።

ጥበበኛው ተጫዋች ዓለማየሁ ዲሳሳ (ዴልፒዬሮ) ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ልደታ ሜዳ ነው። በአካባቢው “ጨፌ ሜዳ” ቢኖርም አብዛኛውን የታዳጊ እድሜውን የተጫወተው አስፋልት ሜዳ ላይ ነው። በዘጠናዎቹ መጀመርያ ኢትዮ ኤሌትሪክ በተትረፈረፈ ተሰጥዖ የእግርኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ሲገዛ እና በ1993 የሦስትዮሽ ዋንጫ ሲያነሳ በስብስብ ውስጥ ከነበሩት ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር። አንበል በመሆን ጭምር እስከ 1996 ድረስ ማገልገልም ችሏል። በሰባት ዓመታት የኢትዮ ኤሌትሪክ ቆይታው ለኢትዮጵያ ታዳጊ፣ ኦሊምፒክ እና ዋናው ብሔራዊ ቡድን መጫወትም ችሏል። በአንድ ዓመት ውስጥ ለሦስቱንም የዕድሜ እርከኖች በአንድ ዓመት ውስጥ ተመርጦ ለብሔራዊ ቡድን መጫወቱ በወቅቱ የነበረውን ልዩ ችሎታውን ይመሰክር ነበር። በአንድ ወቅት ኤሌትሪክ በአፍሪካ ቻምፒዮስ ሊግ ከአልጄሪያው ኬጂ ከቢሌ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ባሳየው ምርጥ እንቅስቃሴ በስታዲየሙ የነበረው ተመልካች ቆሞ እንዳጨበጨበለት ይታወሳል። ከኤሌክትሪክ በኋላ ከሐረር ቢራ ጋር የአንድ ዓመት ቆይታ በማድረግ ወደ የመን ሊግ አምርቶ የሊጉ ቻምፒዮን ከመሆኑም ባሻገር የዓመቱ ምርጥ ተጫዋችነት ክብር አግኝቷል።

ከፍተኛ በራስ መተማመን ያለው፣ ራሱን ሜዳ ላይ በሚገባ መግለፅ የሚችል፣ ከራሱ ስም ጋር የተቆራኘው ቅጽል ስሙ (ዴልፒዬሮ) እንደሚያመለክተውም የቴክኒክ ክህሎቱ የላቀ ተጫዋች የሆነው ዓለማየሁ ከየመን መልስ ለኢትዮጵያ መድን ከቀድሞ አሳዳጊው ክፍሌ ቦልተና ጋር አይረሴ የሆነ የእግርኳስ ቆይታ እንዳደረገ ይነገራል። በድጋሚ ወደ የመን በማምራት ሁለት ዓመት ቆይታ አድርጎ እንደተመለሰ ለሦስት ወራት ያህል በደደቢት ቆይታ ቢያደርግም በአንዳንድ ነገሮች ባለመስማማት ተለያይቶ በድጋሚ ወደ መድን ተመልሶ ከተጫወተ በኃላ እግርኳስን አቁሞ ከሀገር በመውጣት በአሁኑ ሰዓት በሲውዘርላንድ እየኖረ ይገኛል።

“እንደ ነበረኝ ችሎታ እና አቅም በእግርኳሱ ብዙ ማድረግ እየቻልኩ አለማድረጌ አረና ሀገሬን መጥቀም አለመቻሌ በጣም እቆጫለው። ይህም የሆነው ከእኔ ችሎታ ማነስ ሳይሆን ካለኝ የአኗኗር ዘይቤ ነው። ፊት ለፊት መናገር እና ነገሮችን የመጋፈጥ ባህርዬ በአሰልጣኞች ዘንድ አይወደድም። በዚህም ምክንያት ብዙ ማሳካት የሚገቡኝን ነገሮች እንዳላሳካ እንቅፋት ሆኖብኛል። ይሄም ቢሆን ግን በጣም ደስተኛ ነኝ። በተለይ በኢትዮ ኤሌክትሪክ፤ በዛ ድንቅ ስብስብ ውስጥ በዋንጫ የታጀበ ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ። በየመንም በሌሎችም ክለቦች ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። ግን እንዳለኝ ነገር ግን ብዙ ማድረግ ነበረብኝ። ሌላው አላደረኩትም የምለው ልጅ ሆኜ የቅዱስ ጊዮርጊስ የለየለት ደጋፊ ነበርኩ፤ አባቴም የጊዮርጊስ ቀንደኛ ደጋፊ ስለነበረ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንድጫወት በጣም ይፈልግ ነበር። ይህ የአባቴን ምኞት አለመፈፀሜ ትንሽ ያላሳካሁት የምለው እርሱን ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ከያዙት ክለብ ጋር ስጫወት ቀድመው ማርክ የሚያደርጉት እኔን ቢሆንም ብሔራዊ ቡድን ሲይዙ ግን “እርሱ ፊት ለፊት ይናገራል” በማለት አይመርጡኝም። ለሀገሬ ብዙ አንዳልጫወት የተደረገበት መንገድ ያሳዝነኛል። አሰልጣኞች ብዙ ነገሬን ነው ያሳጡኝ። በአጠቃላይ ግን በተጫወትኩባቸው ዘመናት በጣም ደስተኛ ነኝ ። በእግርኳስ ዘመኔ በ1993 የካፍ ካፕ (አሁን ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ) የአልጄሪያው ጄስ ካቢሌን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ 1-0 ስናሸንፍ ባሳየሁት እንቅስቃሴ ተመልካቹ ያጨበጨበልኝን ጨዋታ መቼም አረሳውም። ቅፅል ስሜን በተመለከተ ከልጅነቴ አስር ቁጥር ማልያ ስለምለብስ እና አጨዋወቴ ከአሌሳንድሮ ዴልፒየሮ ጋር ይመሳሰል መሰለኝ ይህን ቅፅል ስም አውጥተውልኛል። ”

ዓለማየሁ ዲሳሳ እግርኳስን ካቆመ በኃላ ከኢትዮጵያ ውጭ በሲውዘርላንድ ሀገር እየኖረ ሲገኝ በተለያዩ አውሮፓ ሀገሮች በሚካሄዱ የኢትዮጵያ ባህል ፌስቲቫል የእግርኳስ ውድድሮች ላይም እየተሳተፈ ይገኛል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ