ስለ ብርሀኑ ቃሲም ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

በእግርኳሱ እንደለፋው ልፋት የሚገባውን ያላገኘው አስፈሪው አጥቂ እና የዘጠናዎቹ ኮከብ ብርሐኑ ቃሲም “መድሀኒቴ” ማነው?

አንተ የችግራን (የህመማችን) ደራሽ ነህ ሲሉ የአዳማ ደጋፊዎች “መድሀኒቴ” የሚል ቅፅል ስም አውጥተው ይጠሩታል። እርሱ ካለ ጎል አለና ብርሀኑ ቃሲም ትውልድ እና እድገቱ ባቱ (ዙዋይ) ነው። የመጀመርያ ክለቡ ኢትኮ የሚባል ሲሆን ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ተጫውቶ በ1991 ነበር ትልቅ ስም እና ከፍተኛ ተወዳጅነት ወዳገኘበት አዳማ ከተማ ያመራው። ባለ ክህሎቱ አጥቂ ብርሀኑ ለስድስት ዓመታት አዳማ ከተማን በሚገባ አገልግሏል። በወጥነት ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት በተከታታይ ዓመታት የተፎካከረ ሲሆን ከቆሙ ኳሶች ቅጣት ምት ተገኝቶ እንደሚያገባ እርግጠኛ የሆኑ የአዳማ ደጋፊዎች “ብሬ ጎል… ብሬ ጎል…” እያሉ ይዘምሩ ነበር። እርሱም አያሳፍራቸውም ጎል ሲያስቆጥርላቸው “መድኀኒቴ” እያሉ ይዘምሩለታል። ከእርሱ ጋር አብረው የተጫወቱ ሁሉ ጭምት፣ ስነ ምግባር የተላበሰ፣ ለቡድኑ መሰዋት የሚከፍል ፣ ፈጣን፣ ደፋር፣ አጥቂ ቢሆንም ቡድኑ ሲቸገር ወደ ኃላ ተመልሶ የሚያግዝ ተጫዋች ነው ይሉታል። ከአዳማ አስደሳች ጊዜያት በኃላ ከ1996 ጀምሮ ለሁለት ዓመት በኢትዮጵያ ቡና ተጫውቶ አሳልፏል። በሀገር ውስጥ ተጫውቶ ባሳለፈበት ዓመታት ምንም እንኳ በዋንጫ ያሸበረቀ፣ በኮከብ ሽልማት የታጀበ ጊዜን ባያሳልፍም ድንቅ እና ያልተዘመረለት ኮከብ ተጫዋች ነበር። ወደ የመን በማቅናት ለአምስት ለዓመታት ከኮብነት ክብርና ከዋንጫ ጋር የተሳካ ቆይታ አድርጎ ወደ ሀገሩ ተመልሷል።

እግሩ ኳስ ሲገባ አቅልሎ የሚጫወት እና አንድ ለአንድ ከሰው ጋር ከተገናኘ ቀንሶ ለማለፍ የማይቸገረው ይህ ፈጣን አጥቂ በድጋሚ በ2003 ወደ አዳማ ከተማ ተመልሶ ለአሳዳጊ ክለቡ ተጫውቷል። አዳማ ከተማ ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን ወርዶ በ2006 ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲመለስም የእርሱ አስተዋፆኦ ከፍተኛ ነበር። ለአዳማ እግርኳስ እድገት እንዳበረከተው አስተዋፆኦ የሚገባውን እውቅና ሳያገኝ በዚያኑ ዓመት መጫወት እየቻለ ባንዳንድ ምክንያቶች ያለ ፍላጎቱ እግርኳስን ለማቆም ተገዷል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡደን ደረጃ በታዳጊ፣ ወጣት እና በኦሊምፒክ ቡድን ቢጫወትም ዋናው ብሔራዊ ቡድን ማገልገያው ወቅት ወደ የመን አምርቷል።

“በእግርኳስ በተጫወትኩባቸው ክለቦች ሁሉ በግሌ ጥሩ ጊዜ ባሳልፍም በዋንጫ የታጀበ አለመሆኑ ያሳዝነኛል። በተለይ ኢትዮጵያ ቡና በገባሁበት ዓመት በ1996 ዋንጫ የምናነሳበት ሰፊ እድል ኖሮን አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጥሎ ሄደ፣ አሰልጣኝ ጥላሁን ቀጥሎ ይዞት ጥሩ መጓዝ ችለን የነበረ ቢሆንም በሚገርም ሁኔታ ዋንጫ ያጣንበት ጊዜ አረሳውም። አሁንም ድረስ መጫወት የምችልበት አቅም ቢኖረኝም እግርኳሱ በብዙ ነገር የተተበተበ መሆኑ አሸሽቶኛል። መጫወቱ ይቅርና ወደ አሰልጣኝነትቱ ጎራ ተቀላቅዬ አዳማ ከተማን ለማገልገል ተዘጋጅቼ ባለበት ወቅት ለምን እንደሆነ በማላቅበት ሁኔታ ሳይሳካ ቀርቷል። የወቅቱ ወረርሺኝ መጥቶ እንጂ የ “ሲ” ላይሰንስ መያዜ አይቀርም። ያወኩትን ያለኝን ልምድ በሚገባ ለትውልዱ ማስተላለፍ እፈልጋለው። ይገርምሀል ብዙ ነገሮችን ለመስራት አስባለው፤ እቅዶችም አሉኝ። ሆኖም አዳማ ቢሮ ያሉ ሰዎች እና አንዳንድ አሰልጣኞች የመንገዴ እንቅፋት ሆነዋል። አይቀርም አንድ ቀን ወደ እግርኳሱ እመለሳለው። ወንድ ልጄ ጥሩ እግርኳስ ተጫዋች እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለው። አሁን ጥሩ እድገት እያሳየ ነው የሚገኘው። ወደ ፊትም ትልቅ ተጫዋች እንዲሆን በምችለው ሁሉ አግዘዋለው።”

ብርሀኑ አሁን በአዳማ ከተማ እየኖረ ሲገኝ በጤና ስፖርት ጨዋታዎች ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አስገራሚ እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክሩለታል። ዓምና ከ17ዓመት በታች የታዳጊ ቡድኑን ተረክቦ እንደሚያሰለጥን ቃል ተገብቶለት አዲስ አበባ በመምጣት የታዳጊ ቡድኑን ጨዋታ እየተከታተለ የነበረ ቢሆንም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሳይሳካ ቀርቷል። ሶከር ኢትዮጵያ እንደ ብርሀኑ ያሉ በእግርኳሱ ከፍተኛ ስም እና ዝና ያተረፉ፣ በእግርኳሱ ተፈትነው ያለፉ ኮከቦች ወደ አሰልጣኝነቱ እንዲመጡ አልያም ልምዳቸውን እንዲያጋሩ መንገዶች እንዲመቻችላቸው መልዕክቷ ነው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ