“ወደ ፊት ትልቅ ተጫዋች የመሆን ህልም አለኝ” ተስፈኛው አጥቂ ፋሲል ማረው

የኳስ ዕይታውና ፍጥነቱ ለመስመር አጥቂነት ምቹ የሆነው፤ በፋሲል ከነማ የታዳጊ ቡድን ውስጥ በተለይ ዘንድሮ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ፈሲል ማረው የዛሬው ተስፈኛ አምዳችን እንግዳ ነው።

ትውልዱና እድገቱ ጎንደር ከተማ ልዩ ስሙ ቀበሌ 06 (አቦ ሠፈር) ነው። በውጭ ሀገር በሚደገፍ ከ13 ዓመት በታች በፕሮጀክት ታቅፎ መጫወት የጀመረው ይህ ተስፈኛ ወጣት ዳሽን ቢራ ታዳጊ ቡድንን በመቀላቀል የእግርኳስ ህይወቱን በክለብ ደረጃ ለመጀመር ቢነሳም በገባበት ዓመት የዳሽን ቢራ እግርኳስ ክለብ ሊፈርስ ችሏል። ሆኖም ከዓመት በኃላ ወደ ፋሲል ከ20 ዓመት በታች ቡድን በመቀላቀል ያለፉትን ሁለት ዓመታት እያገለገለ ይገኛል። ከመስመር እየተነሳ በፍጥነት የሚያስቆጥራቸው ጎሎች እና ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ሌላው መለያዎቹ ናቸው። ለዚህም ማሳያ በዚህ ዓመት በ4ኛ ሳምንት ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ጎፋ በሚገኘው ኢትዮ ኤሌትሪክ ሜዳ ላይ ተገኝተን ያስቆጠረውን ጎል በዚህ መልኩ ፅፈነው ነበር።

“የኳስ ንክኪው ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ጀምሮ አንድም ሳይቋረጥ ከመስመር ወደ መሐል ሰብረው በመግባት የወደፊት የፋሲል ከነማ ተስፈኛ ተጫዋች መሆን እንደሚችል የተመለከትነው ፋሲል ማረው ተከላካዮች እና ግብጠባቂውን እንዲሁም በድጋሚ ተከላካይ በማለፍ አስደናቂ ጎል በ25ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።”

እድገቱን ጠብቆ መሄድ ከቻለ ነገ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል ብለን ተስፋ የጣልንበት ይህ የመስመር አጥቂ የዛሬ እንግዳችን አድርገነዋል።

” እንደማንኛው ተጫዋች በሠፈር ውስጥ ለምለም በምትባል ሜዳ ነው መጫወት የጀመርኩት። ቤተሰቦቼ በተለይ ወንድሜ እግርኳስ ተጫዋች እንድሆን የሚያደርግልኝ ድጋፍ እግርኳስ ተጫዋችነትን ገፍቼ እንድሄድ ምክንያት ሆኖኛል። በአሰልጣኝ መሳፍንት በሚሰለጥን ፕሮጀክት በ13 ዓመቴ ጀምሬ በኃላ ከዳሽን ቢራ ጋር እየሰራሁ ባለሁበት ወቅት ዳሽን ክለቡ መፍረሱ ሲሰማ ወደ ትምህርት አምርቼ ነበር። በኃላ ከሁለት ዓመት በፊት አሰልጣኝ ግርማይ ኪሮስ ወደሚያሰለጥነው የፋሲል ከነማ ቡድንን በመቀላቀል እየተጫወትኩ እገኛለው። አምና ትንሽ ክፍተቶች ነበሩብኝ ዘንድሮ አሰልጣኜ በሚሰጠኝ ስልጠና ጥሩ መሻሻል እያሳየሁ ነው። ከ20 ዓመት በታች የዘንድሮ ውድድር ላይ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ሦስት ጎል አስቆጥሬ ጥሩ የውድድር ዓመት ጅማሮ ባደርግም የኮሮና ወረርሽኝ መጥቶ ውድድሩ ሊቋረጥ ችሏል። አሁንም ልምምዴን በጥሩ ሁኔታ እየሰራው ሲሆን በቀጣይም ራሴን በማሻሻል ጠንክሬ ሠርቼ ትልቅ ተጫዋች የመሆን ህልሜን አሳካለው። በቀጣይ ዓመት ፋሲል ከነማ ዋና ቡድኑን እቀላቀላለው ብዬ ተስፋ አደርጋለው። አሳዳጊ ክለቤን ፋሲልንም በምችለው መጠን ደረጃ ከፍ ለማድረግ እና ለማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ። ዳሽን ቢራ እያለ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አይቼ ማድነቅ የጀመርኩት እና አሁን ከክለብ አልፎ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የሆነው አማኑኤል ገ/ሚካኤል በጣም አድናቂ ነኝ፤ እንደርሱ ለመሆንም አስባለው”።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ