ኢትዮጵያ ከካፍ የገንዘብ ድጋፍ ሊደረግላት ነው

ካፍ ትላንት ምሽት በስሩ ላሉ አባል ሃገራት የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሆነ አስታውቋል።

ትላንት የካፍ የኢመርጀንሲ ኮሚቴ አባላት በቪዲዮ ኮንፍረንስ ስብሰባ አድርገዋል። በስብሰባውም ኮሚቴዎቹ ለአባል ሃገራት ድንገተኛ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተው የገንዘብ መጠኑን አፅድቀው ወተዋል። በተለይ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የፋይናንስ አቅማቸው ለተዳከመ የአህጉሪቱ ፌደሬሽኖች በጠቅላላው 10.8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማከፋፈል ተስማምተዋል። በውሳኔውም መሰረት ከ54ቱ የካፍ አባል ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ አሁን በግልፅ ያልተቀመጠ የገንዘብ መጠን በቅርቡ እንደሚደርሳት ታውቋል።

የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድም ከካፍ ኦን ላይን ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ ፌደሬሽኖች ውድድሮቻቸውን በማቆማቸው በተፈጠረባቸው የገንዘብ አቅም ውስንነት እንደተቸገሩ ገልፀው በቀጣይ ግን ይህ የካፍ ድጋፍ ነገሮችን እንደሚያቀልላቸው ጠቁመዋል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ካፍ በአህጉሪቱ የክለብ ውድድሮች(ካፍ ቻምፒየንስ ሊግና ኮንፌደሬሽን ካፕ) ላይ እየተሳተፉ ለሚገኙ ክለቦች 3.5 ሚሊዮን ዶላር ለማከፋፈል መወሰኑ ይታወሳል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ