ስለ አንዳርጋቸው ሰለሞን (ሸበላው) ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ታሪክ (በወጣት ቡድን) ባላት ብቸኛው ተሳትፎ ባለሪከርድ ነው። ሜዳ ውስጥ ለሚወደው ክለብ ሁሉን ነገር የሚሰጥ እንደሆነ ይነገርለታል። በየጨዋታዎቹ አናጋጋሪ ክስተት በመፍጠር የሚታወቀው የዘጠናዎቹ ድንቅ የመስመር ተከላካይ አንዳርጋቸው ሰለሞን (ሸበላው) ማነው?

ከወታደር አባቱ አዲስ አበባ ሜክሲኮ ከሚገኘው ጦር መሳርያ ግምዣ ቤት ግቢ ውስጥ ተወልዶ አድጓል። የአባቱ ህይወት ማለፉን ተከትሎ ከዚህ ካምፕ በመውጣት ዓለም ሠላም (ሦስት ቁጥር ማዞርያ) ቢኖርም በኃላ ላይ ለእግር ኳስ ህይወቱ መነሻ በሆነው መካኒሳ አካባቢ እንደኖረ ይታወቃል። ተጫዋች ለመሆን ያነሳሳው ምንም ምክንያት የሌለ እና በሠፈር ውስጥ በግሉ ለመዝናናት በመካኒሳ ታዳጊ ቡድን ይጫወት የነበረ ቢሆንም በ1988 ድንገት ሳያስበው ጓደኞቹ ቡና ቢ ሙከራ ለማድረግ ሲሄዱ የእነርሱን ትጥቅ ለመያዝ ሄዶ በዛው የቀረበት አጋጣሚ አስገራሚ ነው። ታሪኩ እንዲህ ነው። ጓደኞቹ እየሞከሩ እሱ የእነርሱን ትጥቅ ይዞ ቁጭ ብሎ ይመለከት ነበር። በዚህ ሰዓት አሁን የኢትዮጵያ ቡና የህክምና ባለሙያ የሆነው ሰለሞን ኃይሉ ለሙከራ ቡና መጥቶ አንዳርጋቸውን ቁጭ ብሎ ያየዋል። አስቀድሞ ሲጫወት ያውቀው ስለነበር “የእኔ ስም ሁለቴ ነው የተፃፈው ስሜ ሲጠራ አቤት በል።” ይለዋል። አንዳርጋቸውም ሰለሞን ተብሎ ሲጠራ እኔ ነኝ ብሎ ከሌሎች ሰዎች ቁምጣ ፣ መለያ እና ጫማ ተውሶ ገብቶ ይጫወታል። በወቅቱ የነበረው አሰልጣኝ መንግስቱ ቦጋለ በአንዳርጋቸው እንቅስቃሴ ተገርሞ ከ300 ተፈታኞች መካከል አንደኛ አድርጎ መርጦት ኢትዮጵያ ቡና ሊገባ ችሏል። እርሱን የጠቆመው ሰለሞን ሙከራውን ወድቆ ወደ ኪራይ ቤት ቢሄድም አሁን የቡና የህክምና ባለሙያ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በአንድነት ለቡና ደሙን የሰጠ፣ ለመለያው የተዋደቀ ጀግና ወታደራቸው አድርገው ይቆጥሩታል ፤ “ሸበላው” በሚል ቅፅል ስምም ይጠሩታል። ረዥም ዓመት ኢትዮጵያ ቡናን በመደገፍ የሚታወቀው ሳሙኤል ንጉሴ ስለ አንዳርጋቸውን በፌስቡክ ገፁ እንዲህ ገልፆታል። “በእግር ኳስ ሁሉንም አሟልተው ከያዙ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ከተክለ ቁመናው እስከ እግር ኳስ ችሎታው የመሀል ተከላካይ ፣ የቀኝ ተከላካይ ሆኖ መጫወት ይችላል። የእግር ኳስ ችሎታው በጣም እጅጉን ላቅ ያለ ነው። አንዳንዴም የመሀል ሜዳ ተጨዋቾች የሌላቸው ችሎታ አለው። በራስ መተማመኑ እጅግ ያስገርማል። ተከላካይ ሆኖ ከራሱ ሜዳ ክልል በቀላሉ ይወጣል። ኳስ ሲያስጥል ምርጫው ማጨናገፍ ሳይሆን ኳስን ሙሉ በሙሉ በራሱ ቁጥጥር ስር ማድረግ ነው። የፍፁም ቅጣት ምት አጠቃቀሙ አስገራሚ ነው።”

1992 እና 97 በሁለት አጋጣሚ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ቢለያይም እየተመለሰ በአጠቃላይ ለአስር ዓመታት ለቡና ሲጫወት የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ፣ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ እንዲሁም በሴካፋ የክለቦች ውድድር የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት ችሏል። ከኢትዮጵያ ቡና በ1999 ከተለያየ በኃላ ለመከላከያ ፣ ሐረር ሲቲ ፣ የመን ፣ መድን እና ድሬደዋ ከተማ ተጫውቶ አሳልፏል።

አብረውት ከተጫወቱ መካከል ድንቁ አማካይ አሸናፊ ግርማ ስለአንዳርጋቸው ሲናገር “አንድ ተከላካይ ሊያሟላቸው የሚገባውን ነገሮች በሚገባ ያሟላ እግር ኳስ ተጫዋች ነው። ኳስ መንጠቅ ባለበት ሰዓት ይነጥቃል። መጫወት ባለበት ሰዓት ይጫወታል። ከኋላ ተነስቶ ወደ ፊት እየሄደ ጎል ያገባል። የአየር ኳስም በጭንቅላት ይገጫል። ኳስ ሲጫወት ለአማካይ ይመቻል ፤ ቀለል አድርጎ ይጫወታል። እልኸኛ እና ለመለያውም ሟች የሆነ የመስመር ተከላካይ ነው።” ይለዋል

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከታዳጊ ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ለአስር ዓመታት ያህል መጫወት የቻለው አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ትልቅ ስፍራ በሚሰጠው ቡድን ውስጥ 1993 ላይ በአርጀንቲና በተካሄደው የዓለም ወጣቶች ዋንጫ ውድድር ላይ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ባለ ሪከርድ መሆን ችሏል። 1998 ላይም በሩዋንዳ በተካሄደው የሴካፋ ዋንጫ በሁሉም ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ ጥሩ ብቃቱን በማሳየት ዋንጫ ማንሳቱ ይታወቃል።

ያመነበትን በግልፅ የሚናገር መሆኑ ፣ ቀልደኛነቱ ፣ ቀይ ካርድ የሚመለከትበት ነውጠኛ ባህሪው ፣ የፍፁም ቅጣት ምት አጠቃቀሙ እና ጎል አስቆጥሮ ደስታውን የሚገልፅበት መንገድ የእርሱ መለያዎቹ ናቸው። በተለይ በአንድ ወቀት መብራት ኃይል ላይ ግብ አስቆጥሮ ከኪሱ ቦንብ ያወጣ መስሎ ደጋፊዎች ላይ በመወርወር ደስታውን የገለፀበት መንገድ በጊዜው የቀይ ካርድ ሰለባ አድርጎት እና ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶበት እንደነበር ይታወሳል። በ2002 እግሩ ላይ ባጋጠመው ጉዳት እግር ኳስን አቁሞ ኑሮውን በአሜሪካ በማድረግ ቤተሰብ መስርቶ ልጆች አፍርቶ እየኖረ ይገኛል። በዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከቦች አምዳችን ከዚህ ድንቅ ተከላካይ ጋር ያደረግነው ቆይታ እንዲህ ይቀርባል።

” እውነት ለመናገር በእግር ኳስ ህይወቴ አላሳካሁትም የምለው ነገር የለም። ከኢትዮጵያ ቡና ቢ ቡድን ጀምሮ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ በዋንጫ የታጀበ ጊዜን አሳልፌያለው። በአርጀቲና ዓለም ዋንጫም ባለ ሪከርድ ነኝ። የምፈልገውን ነገር ሁሉ አግኝቻለው ባልልም። ለእኔ በህዝብ በሚወደው እና የሀገሪቷ ታላቅ ክለብ በሆነው ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ፊት መጫወት ትልቅ ስኬት ነው። በእነዚህ ወርቅ ደጋፊ ፊት አይደለም ለአስር ዓመት ለአንድ ዓመት መጫወት በራሱ ኩራት ነው። ለኔ ስኬት ከክለብም በላይ ለሆነው ኢትዮጵያ ቡና እየተዘመረልህ መጫወት ነው።

“ጎል የማግባት አቅሜ የመጣው በልምምድ ነው። በዋናው ቡድን ደረጃ የመጀመርያ ጎሌ ኢትዮጵያ ቡና እያለው መብራት ኃይል በ1992 ፀጋዘአብ አስገዶም ላይ ከመሐል ሜዳ ተነስቼ የሚገርም ጎል ያስቆጠርኩት ነው። እንዲያውም በዚህ ጨዋታ አሰግድ አልገባም ነበር። ማታ ካምፕ ስገባ አዲስ መለያ በስጦታ ሰጥቶኛል። አሰግድን አመሰግናለው፤ ነፍሱንም ይማርልን። የመጨረሻ ጎሌም ቡና እያለው በ1996 በአንድ ሁለት ቅብብል አምስት ተጫዋቾችን በማለፍ ንግድ ባንክ ላይ ያስቆጠርኩት ጎል ነው። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ከዩጋንዳ ሁለት ለሁለት በተጠናቀቀው ጨዋታ ላይ አንድ ለጎል የሚሆን ኳስ አመቻችቼ ሳቀብል አንድ ጎል በማስቆጠር በዋናው ቡድን የመጀመርያ ጎሌን አግብቻለው ፥ የጨዋታውም ኮከብ ተብዬ ትንሿን መፅሐፍ ቅዱስ ተሸልሜ ነበር። አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው በእግር ኳስ ካገኘዋቸው ትልቁ ሽልማቶች አንዱ ነው። ፍፁም ቅጣት ምት የመምታት ልምድን ያገኘሁት መብራት ኃይል እያለው ነው። ማስተር ቴክኒሻን ጋሽ ሀጎስ ደስት ያስተማረኝ ነው ፤ እኔም የግብ ጠባቂዎችን አቋቋም በመመልከት ከዛን ጊዜ ጀምሮ ጥሩ መቺ መሆን ችያለው። በዓለም ወጣቶች ዋንጫ ካስቆጠርኳቸው ሁለት ጎሎች አንድ ጎል በፍፁም ቅጣት ምት ነው። ይህም ቢሆን በ1995 ከላይቤሪያ ጋር ሰንጫወት የሳትኩት አጋጣሚ በእግር ኳስ ብቸኛው አጋጣሚዬ ነው።

” ኳስን ይዤ ወደ ፊት የመሄዴ ሚስጥሩ የተገኘው ሠፈር ውስጥ እያለው እንደሚታወቀው መሐል ባልገባ እንጫወት ነበር። ይህ ያለ ታክቲካል ዲሲፒሊን በነፃነት ከምንጫወተው ጨዋታ ያዳበርኩት ይመሰልኛል። ቡና ስመጣ የቦታ ምርጫ አልነበረኝም። በአሰልጣኝ ምርጫ ነው ተከላካይ የሆንኩት። ሆኖም ሠፈር ውስጥ በነፃነት የመጫወቴ ምክንያት ይመስለኛል። በተለይ ኢትዮጵያ ቡና መሆኔ የመጫወት ነፃነት አግኝቼ በተደጋጋሚ ኳስን ይዤ ተከላካዮችን በማለፍ ጎል እስከ ማስቆጠር ደረጃ እንድደርስ አድርጎኛል። ቡና ቢ ለሁለት ዓመት ስቆይ ወደ ፊት ስሄድ ከእኔ ኳስ እየተነጠቁ ጎል ይገባብን ነበር። አሰልጣኝ መንግስቱም እኔ እንድሻሻል ቢመክረኝም የማልሰማ በመሆኔ በራሴ ፍቃድ ትቼ ወጥቼ ነበር። ሆኖም መንግስቱ አፈላልጎኝ ስህተቴን መቀነስ እንዴት እንዳለብኝ መክሮኝ እኔም ራሴን አሻሽዬ እዚህ ደረጃ ደርሻለው።

” ጎል አግብቼ በተለያዩ መንገዶች ደስታዬን ገልጫለው። አሁን ሳስታውሰው ይገርመኛል። ዳንስ ይሁን ምን እንደሆነ አይታወቅም ብቻ ጎል አግብቼ ስሜቴን እገልፅ ነበር። በዚህም ደስታ አገላለፄ እራሴን ለሌላው ገልጬ አሳይቻለው ብዬ አስባለው። ይህም ቢሆን መብራት ኃይል ላይ ቦንብ እንደ መወርወር አድርጌ ደስታዬን የገለፅኩበት መንገድ ታሪኩ ረጅም ነው። በ1992 ከቡና አመራሮች በነበረኝ ቅሬታ ኤልፓ ሄጄ ነበር። ሆኖም ወደ ቡና ለመመለስ ፈልጌ ኤልፓዎችን መልሱኝ ስላቸው ‘እንቢ’ አሉኝ። በዚህ ክርክር በቀለ (ኮረንቲ) ‘ቤቴንም ሸጬ ቢሆን ኤልፓ ይቀራል’ ቢልም እኔ ወደ ቡና ተመልሻለው። በዚህ ቅር የተሰኙት የኤልፓ ደጋፊዎች ከእነርሱ ጋር በነበረው ጨዋታ ተቃውሞ ሲያቀርቡ ጎሉን አስቆጥሬ ሄጄ እንደ ቦንብ መሰል ነገር ወረወርኩባቸው። ይህ ፍፁም ስህተት የሆነ ድርጊት ነው። በዕለቱም ይቅርታ የጠየኩበት ነገር ነው። አሁንም ቅር የተሰኘ ካለ በድጋሚ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

“በተደጋጋሚ ቀይ ካርድ የምመለከትበት ምክንያት የሚገርማው ከኢትዮጵያ ቡና ውጪ በክለብም በብሔራዊ ቡድን አንድም ቀይ ካርድ አይቼ አላውቅም። ነገር ግን ኢትዮጵያ ቡና ላይ በደል አለ ብዬ ስለማስብ አንዳንዴ ስሜታዊ ሆኜ እንዲሁም የዳኞች ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ እኔን ለቀይ ካርድ ተጋላጭ አድርጎኛል።

“የአርጀቲናው የዓለም ዋንጫ በእኔ የእግርኳስ ህይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነው። እግር ኳስ በአርጀንቲና ምንያህል ቦታ እንደሚሠጠው የተረዳንበት እና ብዙ ትምህርት ያገኘንበት አሪፍ ቆይታ ነው ያደረግነው። ለአንድ ወር በአርጀንቲና በነበረን ቆይታ ከህዝቡ ከፍተኛ ክብርን አግኝተናል። እኔም በጨዋታ እና በፍፁም ቅጣት ምት ሁለት ጎሎች አስጥሬያለው። ወደ ፊት አንድ ተጫዋች መጥቶ ሦስት ጎል እስኪያስቆጥር ድረስ ባለ ታሪክ ሆኜ እቀጥላለው።

” ሸበላው የሚለውን ቅፅል ስም ያወጡልኝ በሚስማር ተራ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ናቸው። ካዛም ሁሉም ተቀበለው እስካሁን ሸበላው የሚለው ስሜ ፀንቶ ሌላውም ተከትሎ ቤተሰቤ ሁሉ ሳይቀር ‘ሸበላው’ እያሉ ይጠሩኛል። እንግዲህ የሚወዱኝ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ያወጡልኝ ስም በመሆኑ ደስ ይለኛል። ያው ግሞ ሸበላ እኮ ነኝ ብዬ አስባለሁ (እየሳቀ)።

“ከሀገሬ ከወጣው በኃላ የለፉትን አስር ዓመታት የሀገሬን እግር ኳስ ባገኘሁት አጋጣሚ በማኀበራዊ ሚዲያ በደንብ ስከታተል ቆይቻለው። የእግር ኳሱን ዕድገት አያለው ፤ የሚያሳስበኝም ነገር አለ። በተለይ ተጫዋቾች ከእኛ ጊዜ በተሻለ የገንዘብ ተጠቃሚ መሆናቸው በጣም ነው ደስ የሚለኝ። ምክንያቱም የገንዘቡ መጠን ከማደጉ በላይ ደስ ያለኝ እግርኳስ እንደ ሙያ መቆጠሩ ነው። በእኛ ግዜ ኳስ ተጫዋችነት እንደ ሙያ ካለመቆጠሩ የተነሳ አስታውሳለው የአንድ ክለብ ፕሬዘዳንት ምን አለ ” እኛ አትራፊ አይደለንም። አደገኛ ቦዘኔ እንዳትሆኑ ነው የያዝናችሁ” በማለት የተናገረው ያሳዝናል። እኛ ደግሞ ‘ክለቡ ከፍሎ የሚያጫውተን ሙያ ስላለን ነው’ እንል ነበር። አሁን ላይ ሙያው ሙሉ ለሙሉ ተከበረ ባይባልም እውቅና አግኝቶ ከፍተኛ ብር ሲከፈል ሳይ ደስ ይለኛል። ሆኖም ግን ለተጫዋቾች እና ለአሰልጣኞች ነፃነት ያለመስጠት ላይ እንዲሁም አንዱ በአንዱ ሙያ ላይ ጣልቃ የመግባት ነገር አያለው። ይሄ ቢስተካከል ጥሩ ነው። ወደ ፊት ወደ ሀገሬ በመምጣት ልምዴን ለማካፈል የተለያዩ ኮርሶችን ወስጃለው ፤ አንድ ቀን ለእግርኳሱ አስተዋፆኦ አበረክታለው ብዬ አስባለው።

“ኑሮዬን በአሜሪካ ዳላስ ቴክሳስ ማድረግ ከጀመርኩ አስር ዓመት ሆኖኛል። ከባለቤቴ ሦስት ልጆች ወልጄ እየኖርኩ እገኛለው። የመጀመርያ ልጄ ብሩክ ገና በዘጠኝ ወሩ መራመድ ጀምሮ በአስራ አንድ ወሩ ነው ኳስ መምታት የጀመረው። እቤት ውስጥ አልፎ አልፎ መጫወት ጀምሮ ሦስት ዓመት ሲሞላው ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር እየተጫወተ ነው። በጣም እየተሻሻለ መጥቶ ጥሩ ችሎታ አለው። እኔም እየረዳሁት ነው። ግን በዚህ ሁኔታው የሚቀጥል ከሆነ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል ብዬ አምናለው። ትምህርት ቤት ከገባ በኃላ ሀሳቡን ካልቀየረ በቀር አሁን ያለበት ደረጃ በጣም ጥሩ ነው።

“መጨረሻም ሳልናገር ማለፍ የማልፈልገው ነገር ቢኖር እኔ ትልቅ ደረጃ እንድደርስ ትልቅ ምክንያት የሆነኝ አሰልጣኝ ሥዩም አባተ ነው። ነፍሱን ጌታ በአፀደ ገነት ያኑረው። እርሱ ለእኔ ትልቅ የኳስ አባቴ እና መምህሬ ነው። ከቢ ቡድን ያሳደገኝ በተለያዩ ምክንያቶች ሁለቴ ከቡና ስወጣ ሁለቴም የመለሰኝ እርሱ ነው። በአጠቃላይ በእግር ኳስ ህይወቴ ውስጥ ፈጣሪ የሰጠኝ ሥዩም አባተን በመሆኑ ሁሌም አመሠግነዋለው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ