ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ አስር – ክፍል ሦስት

ጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ምዕራፍ አስር ላይ ደርሷል። ይህ ምእራፍ በእግርኳስ ታክቲክ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ካገኙ የአጨዋወት አቀራረቦች አንዱ የሆነው ካቴናቺዮን ከስር መሠረቱ ጀምሮ ያለፈባቸውን መንገዶች ይመለከታል። የዛሬው መሰናዶም ካለፈው ሳምንት የቀጠለ ነው።


ደማቅ የማለዳ ጮራ ያረፈበት ባህር ላይ ለአሳ ማጥመድ የሚውሉ ጀልባዎች ተደርድረዋል፡፡ በታይርሄኒያን ባህረ-ገብ መሬት ላይ አዕምሮው በሐሳብ የተወጠረና እንቅልፍ እምቢ ያለው የእግርኳስ አሰልጣኝ በጠዋት አካባቢውን እየቃኘ ይራመዳል፡፡ ሰውየው በወፎቹ ጩኸትና የመርከብ ማቆሚያው አካባቢ ያለው የነጋዴዎች ውጣውረድ መሃል የዝግታ እርምጃውን ቀጥሏል፡፡ በጉዞው በየትኛው መንገድ ከቡድኑ ተጫዋቾች ምርጡን ብቃት ሊያገኝ እንደሚችል ደግሞ ደጋግሞ ራሱን ይጠይቃል፡፡ ደካማ የሆነው እና የሚችለውን ያህል ቢጥር ለውጥ አላሳይ ያለውን የተከላካይ ክፍል እንዴት ባለ ብልሃት ማጠናከር እንደሚኖርበት ያወጣል-ያወርዳል፡፡ ወደቡን እያለፈም አዕምሮው የቡድኑ ችግር ምን እንደሆነ መልሶ መላልሶ ያሰላስላል፡፡ በመሃል ቀልቡ አንድ ጀልባ ላይ ያርፋል፡፡ አሳ አጥማጁ ማጥመጃ መረቡን ወደ ባህሩ ሲጥል ይመለከታል፤ ከዚያም መረቡ ብዙ አሳዎች ይዞ ሲወጣ ያያል፤ ሌላኛው የመጠባበቂያ መረብም እንዲሁ በአሳዎች ተሞልቶ ከውሃ ውስጥ ሲወጣ ያስተውላል፡፡ እናም ይህ አስተውሎቱ የእርሱ “አገኘሁት!” ቅጽበት ሆነለት፡፡ ከቀዳሚው መረብ ጥቂት አሳዎች ተንሸራተው ወደ ውሃ ውስጥ ሲመለሱ አይቷል፤ ነገርግን እነዚህ አሳዎች ከሁለተኛው መረብ ሊያመልጡ አልቻሉም፡፡ ከዚህ ምልከታው የእርሱ ቡድን ይሻሻል ዘንድ ምን እንደሚያስፈልገው ተገንዝቧል፡፡ ከዋናው የተከላካይ ክፍል ጀርባ የሚያፈተልኩ አጥቂዎችን የሚቆጣጠር ደጋፊ ተከላካይ ሊኖረው እንደሚገባ አመነ፡፡ ይህ አሰልጣኝ ጂፖ ቪያኒ ይባላል፤ ቡድኑ ደግሞ ሳለርኒታና ተብሎ ይጠራል፤ የአሰልጣኙ ታክቲካዊ ግኝት ደግሞ -ካቴናቺዮ-፡፡

እንግዲህ ይህ ተረክ ቪያኒ ራሱ የሚያቀርበው ነው፡፡ ግልጽ ያልሆነና የተሰወረ ምስጢር ያነገበ ትርክት ቢመስልም ቅሉ ማራኪ ዳራ መያዙ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በጣም የተጋነነ የፈጠራ ታሪክ ያለው እንዲመስል ተደርጎ ቀርቧል፡፡ በጣልያን ካቴናቺዮ እንዴት እንደተጀመረ የሚቀርቡ መላ-ምቶች ብዙ ቢሆኑም የጂፖ ቪያኒ የ”ካቴናቺዮ ጀማሪ ነኝ!” ይገባኛል ባይነት ጠንካራ መሰረት ያለው ይመስላል፡፡ ከእርሱ በፊት ይህን የአጨዋወት ሥርዓት በተግባር ላይ ያዋሉ ወገኖች መኖራቸው አጠራጣሪ ባይሆንም በመደበኛነት እንዲሁም በላቀ ስኬታማነት የተገበረው ጂፖ ቪያኒ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም፡፡ ምንም እንኳ የሲውዘርላንድ ታሪካዊ ተጽዕኖ በጣልያን እግርኳስ  እድገት ላይ የራሱን አሻራ ትቶ ማለፉ ባያከራክርም ምናልባት ቪያኒ ከካርል ራፕን አነሳሽነት ውጪ አድጎም ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ምሳሌዎችን እናነሳ፦ ቪቶሪዮ ፖዞ ለዙሪኩ ክለብ ግራስሆፐርስ ተጠባባቂ ቡድን ለሁለት ዓመታት ያህል ተጫውቷል፡፡ የመጀመሪያው የጣልያን ብሄራዊ ቡድን አምበል ፍራንዝ ካሊ የተማረው በሉዛን ከተማ ነው፡፡ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች መካከል በሰሜን ጣልያን ትልልቅ ቡድኖችን ገንብተው በነበሩ ክለቦች ውስጥ ቢያንስ አንድ ሲውዘርላንዳዊ ስደተኛ ተጫዋች ማግኘት የተለመደ ነበር፡፡ በተለይ በጄኔዋ፣ ቶሪኖና ኢንተርናዚዮናሌ የሲውዝ ተወላጆቹ ተጫዋቾች መኖር የጥንካሬ መገለጫ ተደርጎ ሲወሰድ ከርሟል፡፡

የካቴናቺዮ ሐሳብ ጥንስስ በባህር ዳርቻ ጉዞው ወቅት የተጀመረ ሆነም አልሆነ የሜዳ ላይ ክፍተቶቹን አይቶ፣ ተገቢውን እርምትና ማስተካከያ ለማድረግ የመጀመሪያ ተነሳሽነትን ወስዶ እጅግ ፍሬያማ ፖሊሲ በመቅረጽ የተጋጣሚን ጥቃት ለመከላከል “የደካሞች መብት”ን በመተግበር ቪያኒ ፈር-ቀዳጅ ነው፡፡ ከጁቬንቱስ ጋር ሁለት የስኩዴቶ ድል የተቀዳጀው እና ሐሳባዊ ከሆኑ አማካዮች (Half-Backs) አንደኛው አልቤርቶ ፒቺኒ ወደኋላ አፈግፍጎ የተጋጣሚዎችን የመሃል አጥቂ በቅርብ ርቀት እየተከታተለ ይጫወት ጀመር፡፡ በ<WM> ፎርሜሽን (3-2-2-3) ከሶስቱ ተከላካዮች አንደኛው ሆኖ የመሃለኛውን ሥፍራ በመያዝ እንደ ጠራጊ ተከላካይ (Sweeper) ሆኖ ሲጫወት የተፈጠረው የአሰላለፍ መዋቅር ቀዳሚውን የቪቶሪዮ ፖዞ ሜትዶ (Methodo) ተክቶ በጣልያን የወደፊቱ ኗሪና ዘላቂ (Default) ፎርሜሽን ለመሆን ቀርቦ ነበር፡፡ ያኔ ቪያኒ የእርሱ ቡድን እጅግ ወደኋላ ተስቦ እንዲከላከል፣ ተጋጣሚዎቹ ደግሞ ነቅለው ወጥተው እንዲያጠቁ ይጋብዛል፡፡ ተጋጣሚዎች ለማጥቃቱ ሒደት ሲሉ ከኋላ መስመሮች ተጨማሪ ተጫዋቾችን ሲያሳትፉ ለመልሶ-ማጥቃት ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ የቡድኑ መዋቅራዊ ቅርጽ የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ከቪያኒ ግኝት ጀርባ ያለው ንድፈ-ሐሳባዊ እሳቤ በ1907 በኸርበርት ቻፕማን ይሰለጥን በነበረው ኖርዛምፕተን ከታየው የአጨዋወት መርህ እምብዛም የተራራቀ አይደለም፡፡

ካቴናቺዮ በጂፖ ቪያኒ ስም ቪያኒማ (Vianema) ተብሎ ከተሰየመው የሳለርኒታና ክለብ መለያ ታክቲክ በቀጥታ የተወሰደ ግኝት አይደለም፡፡ ይህን የአጨዋወት ሥልት በመተግበር ሳለርኒታና በ1947 ወደ ከፍተኛው ሊግ የመሻገር ዕድገት ቢያገኝም ዝቅተኛ ግምት የሚሰጠው ቡድን ነበር፡፡ በሶስት ምድቦች ተከፍሎ በተካሄደው የሁለተኛ ዲቪዚዮኖች ውድድር ከሁሉም ቡድኖች ምርጡን የመከላከል ሪከርድ ይዘው ሴሪኤውን ቢቀላቀሉም አንድም ከሜዳቸው ወጪ ያካሄዱትን ጨዋታ ማሸነፍ ሳይችሉ በመጡበት ዓመት ወደ ነበሩበት ሊግ ሊወርዱ ችለዋል፡፡

በእርግጥ ቪያኒ በሳለርኒታና ያሳየው አንጻራዊ ስኬት ካቴናቺዮ በጣልያን የአንድ ዘመን የአጨዋወት ዘዴ (Fashion) እንዲሆን በር ከፍቷል፡፡ ታክቲኩ በመላ ሃገሪቱ በተለያዩ መንገዶች መተግበር ጀምሯል፡፡ የቀድሞው የጋዜታ ዴላ ስፖርት ዋና አዘጋጅ ሎዶቪኮ ማርዴይ ” እግርኳስ በተናጠል ተጫዋቾች ብቃት ላይ ተመሥርቶ በሚደረግ የአንድ-ለ-አንድ ፍልሚያ የሚወሰን ከሆነ ትናንሽ ቡድኖች ህልውናቸው አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ተረዱ፡፡” ይላል፡፡የእግርኳስ ጸሃፊው ማስረዳቱን ቀጥሏል-

” ስለዚህ W-M (3-2-2-3)ን እየተገበሩ ከተከላካይ ክፍላቸው ኋላ ሌላ ትርፍ ተከላካይ (Spare-Man) የሚያገኙባቸውን ሽግሽጎች ማድረግ ጀመሩ፡፡ ብዙውን ጊዜ አንደኛውን የመስመር አማካይ (Wingers) ወደኋላ በመሳብና የመስመር ተከላካዩን(Full-Back) ደግሞ ከተከላካዮች ጀርባ በማሰለፍ የመከላከል ሲሷቸውን እያጠናከሩ መጡ፡፡ ሽግሽጎቹ ያለ በቂ ዝግጅት የተወሰዱ ግብታዊ ማሻሻያዎች እንጂ በጥልቁ የታሰበባቸው (Systematic) መፍትሄዎች አልነበሩም፡፡ ብዙዎች በአስተያየቴ ላይስማሙ ይችላሉ፥ ነገርግን እኔ ይህን የምልበት በቂ ምክንያት አለኝ፡፡ በወቅቱ ይህን አጨዋወት የሚከተሉት ትንንሾቹ ቡድኖች ብቻ ነበሩ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በኋላ ክፍላቸው ብቻ ላይ ያተኩራሉ፤ የመስመር ተከላካዩ በጥልቀት ወደኋላ የመመለስ አዝማሚያ ቢያሳይ እንኳ የእርሱን የግል እንቅስቃሴ በተለየ ልታስተውሉ አትችሉም፤ ምክንያቱም አጠቃላይ ቡድኑ እየተከላከለ ነውና፡፡” በማለት ሐሳቡን ሊያብራራ ይሞክራል፡፡

የአዲሱ አጨዋወት ስልት ዋነኛ አቀንቃኝ ትሪየስቲናን ለፈጣን ለውጥ ያበቃው ኔሪዮ ሮኮ ነበር፡፡ ሮኮ ኤሲ-ሚላንንም ሁለት የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ አሸናፊ እንዲሆን አስችሏል፡፡ ይሁን እንጂ አሰልጣኙ በእግርኳስ አጨዋወት ዘይቤ ዙሪያ የነበረውን አመለካከት የሞረደለት እምብዛም ስም በሌለው የትውልድ ከተማው ክለብ ያደረገው ቆይታ ነው፡፡ ትሪየስቲና የውል ስምምነት ሳያቀርብለት በፊት በአያቱ ልኳንዳ ቤት ተቀጥሮ ሥጋ ቆራጭ ሆኖ ሰርቷል፡፡ ከዚያ በፊት በፓዶቫ እና ናፖሊ ብዙም እውቅና ያልነበረው የተጫዋችነት ዘመን አሳልፏል፡፡ በወቅቱ በጣልያን አሰልጣኝ ለመሆን የግድ ለብሄራዊ ቡድን መጫወት ያስፈልግ ስለነበር በእነዚህ ክለቦች የነበረው ቆይታ ይህን እድል እንዲያገኝ አግዞታል፡፡  የተጫዋችነት ጊዜውን ካገባደደ በኋላ እጅጉን ወደሚወዳት ከተማው ተመለሰ፡፡ ሮኮ በቴሌቪዥን ቀርቦ ሲናገር የሃገሬውን ባህል ይወክላል፤ በቱባው የትሪየስቴ ቋንቋ ዘዬ ያወራል፤ ይህን ተከትሎም በ1948 የዴሞክራት ክርስቲያን ማህበር አማካሪ ሆነ፡፡ ከሁሉ በላይ ግን በከተማዋ ትንሽና ተወዳጅ በሆነው የእግርኳስ ክለብ ያሳካው ትልቅ ስኬት በትሪየስቲና ስሙ በታሪክ ውስጥ በደማቁ እንዲጻፍ አደረገ፡፡

በ1947 ሮኮ ሲቀጠር ትሪየስቲና ምስቅልቅል ውስጥ ይገኝ ነበር፡፡ ያን ዓመት በሴሪኤው በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ተቀምጦ ጨረሰ፡፡ በከተማዋ የብሪታኒያና አሜሪካ ወታደሮች ስለነበሩ ትሪየስቲና በሜዳው አንድም ጨዋታ ማድረግ ሳይችል የውድድር ዘመኑ በመጠናቀቁ ለክለቡ ደካማ ውጤት ማስመዝገብ በምክንያትነት ተጠቀሰ፡፡ ከመውረድ የተረፈውም ይህ ችግር በይግባኝነት ቀርቦ ነው፡፡ ለሁሉም ጨዋታዎቻቸው ረዣዥም ርቀቶችን እንዲጓዙ ባይገደዱ ኖሮ ምናልባትም ትሪስቲየና ከዚያ የተሻለ አቋም ያሳይ እንደነበር ብዙዎች ያምናሉ፡፡ በኒሊዮ ሮኮ የመጀመሪያ ዓመት ቆይታ ክለቡ በሜዳው አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ከሌላ አንድ ቡድን ጋር ተዳብሎ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ጨረሰ፡፡ ይህ ውጤት ለአሰልጣኙ እጅግ በጣም ጥሩ ጅምር ሆነለት፡፡ በቀጣዮቹ ሁለት ተከታታይ የውድድር ዘመናት የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ስምንተኛ ሆኖ አጠናቀቀ፤ ይህም ትሪስቲየናን ለመሰሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለተጋረጡባቸው ክለቦች የከፋ የሚባል አልነበረም፡፡ ሮኮ ከቦርዱ ጋር ባለመስማማት ሲለያይ ቤላ ጉትማን ተተካ፤ ከዚያም የቡድኑ ደረጃ ወዲያውኑ ወደ 15ኛ አሽቆለቆለ፡፡

እስከዚህ ጊዜ ድረስ እንኳ ካቴናቺዮ የትንንሽ ቡድኖች ታክቲክ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ ትልልቅ ቡድኖች ካቴናቺዮ ዋንጫዎችን ለማሸነፍ እንደሚያስችላቸው ማሰብ የጀመሩት በአልፍሬዶ ፎኒ ሥር የሚሰለጥነው ኢንተርናዚዮናሌ ይህንን የጨዋታ ሲስተም መጠቀም ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ አሰልጣኙ የቀኝ መስመር አማካዩን (Right-Winger) ጂኖ አርማኖ ወደኋላ ስቦ የተጋጣሚው ግራ አማካይ (Left-Winger) ላይ የአንድ-ለ-አንድ ክትትል (Man-Mark) እንዲያደርግ አዘዘው፡፡ የቀኝ መስመር ተከላካዩ (Right-Back) ኢቫኖ ብላሰን ደግሞ ጠራጊ ተከላካይ (Sweeper) ሆኖ ይጫወት ጀመር፡፡ ከዚህ አንጻር ጂኖ አርማኖ በጣልያን የመጀመሪያው <ቶማንቲ(Returner)>
ለመሆን በቃ፡፡ ቶማንቲ ከመስመር አማካይነት እየተነሱ ወደኋላ በማፈግፈግ የተከላካይ ክፍላቸውን ለሚያግዙ ተጫዋቾች የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡

በዚያ ዘመን ኢቫኖ ብላሰን ፈር-ቀዳጁና ታላቁ “ሊቤሮ” መሆን ችሏል፡፡ በ1950 ብላሰን ትረስቲናን ለቆ ኢንተርናዚዮናሌን ከመቀላቀሉ በፊት ገልጃጃ የመስመር ተከላካይ ነበር፡፡ በአዲሱ የሊቤሮነት ሚናው ግን በረዥሙ ወደፊት በሚልካቸው ኳሶችና በማያወላውል አቋሙ ስመጥር ሊሆን ቻለ፡፡ የጨዋታ ማስጀመሪያ ፊሽካ ከመነፋቱ በፊት ሜዳው ላይ ምልክት ያኖርና ለተጋጣሚ ቡድን የፊት መስመር ተሰላፊዎች ከዚያች ድንበር ማለፍ እንደሌለባቸው ያስጠነቅቃቸዋል፤ ትዕዛዙን ሳያከብሩ ቢቀሩ ደግሞ ቅልጥም-ቅልጥማቸውን እንደሚመታቸው ይነግራቸዋል፡፡ ” በጊዜው ጥቂት ሰዎች ብላሰን ድንቁ ሊቤሮ እንዳልነበረ ሊያስቡ ይችላሉ፡፡  በእርግጥ እርሱ ኳስ እግሩ ሥር በደረሰች ቅጽበት ወደፊትም ሆነ ወደላይ እንዲያጎናት የሚጠበቅበት እና አሰልቺውን የእግርኳስ ሥራ የሚሰራ ነው፡፡ ለዚያም ይመስላል ኳስን በተለመደው የንክኪ ሒደት ከመቀባበል ይልቅ ከግብ ክልል የማራቅ ሥራ በመሥራታቸው በወቅቱ ሊቤሮዎች <Battitore Liberos(Free-Hitters)> ተብለው ይጠሩ የነበሩት፡፡” ሲል ማራዴይ ተናግሯል፡፡

በ1952-53 ኢንተር በሰላሳ አራት ጨዋታዎች አርባ ስድስት ግቦች ብቻ አስቆጠረ፡፡ ይህም ጁቬንቱስ ካስቆጠረው በሃያ ሰባት ያነሰ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሃያ አራት ግቦች ብቻ ስለተቆጠረበት ከጁቬንቱስ በልጦ ዋንጫውን ማሸነፍ ችሏል፡፡ (ከዚህ ዓውድ አንጻር ንጽጽሩን ስናየው ቀደም ባለው የውደድር ዘመን ጁቬንቱስ ዘጠና ስምንት ግቦች አስቆጥሮና ሰላሳ አራት ጎሎች አስተናግዶ የሊጉን ድል ተቀዳጅቷል፡፡) የሁለቱን ክለቦች የአጨዋወት ዘይቤ አሰመልክቶ ጂያኒ ብሬራ ” ኢንተር ይከላከላል፤ ከዚያ ብላሰን በድንገት ያልተጠበቀ ጠንካራ ምት ይመታል፡፡ ከእርሱ ወደ ሰባ ሜትር ገደማ በሚጠጋ ርቀትና ማናቸውም የቡድን አጋሮቹ በማይገኙበት እንዲሁም ተጫዋቾቹ ሊጠቀሙ የሚችሉበት ክፍት ቦታዎች የሌሉበት ወረዳ ላይ የሚልከው ኳስ እንዲሁ መክኖ ይቀራል፡፡” ይላል የኢንተርን ጉዞ ሲገልጽ፡፡ በ1952-53 የውድድር ዘመን ኢንተር ስምንት ጨዋታዎችን 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፏል፤ አራት ጊዜ ደግሞ 0-0 አቻ ተለያይቷል፡፡ ” በብዙኃን መገናኛዎች የኢንተር አጨዋወት ላይ የሚወርደው ውርጅብኝ በረታ፤ ትችቱም ከባድ ሆነ፡፡ ተቺዎች ክለቡ ቦኒቶ ሎሬንዚ፣ ናካ ስኮግለንድና ስቴቫን ናየርስን ያካተተ በኮከቦች የተዋቀረ የፊት መስመር ቢኖረውም የሚጫወተው እግርኳስ እጅግ መከላከል ላይ ያተኮረና ማራኪ ይዘት የሌለው መሆኑን በምክንያትነት አነሱ፡፡ ይህ ሒደት ሥር ነቀል የአጨዋወት አብዮት አስነሳ፡፡ አስታውሱ- በእያንዳንዱ የውድድር ዘመን ሊጉን የሚያሸንፉ ቡድኖች እስከ መቶ የሚደርሱ ግቦች ያስቆጥሩ ነበር፡፡” በማለት ተናግሯል ማርዴይ፡፡

ብዙ ቡድኖች የተለያዩ የአጨዋወት ዘዴዎችን ለመተግበር ተነሳሱ፡፡ ለምሳሌ ያህል በተጫዋችነት ዘመኑ በቪቶሪዮ ፖዞ እምብዛም ዕምነት ያልተጣለበትና የመሃል-ተከላካይ አማካይ (Centre-Half) በነበረው በፉልቪዮ ቤርናርዲኒ የሚሰለጥነው ፊዮረንቲና በ1956 የሊጉን ዋንጫ አነሳ፡፡ ቤርናርዲኒ የተለያዩ የካቴናቺዮ ግኝቶችን መተግበር በመጀመር ቀደሚው ሆነ፤ የግራ መስመር አማካዩ (Left-Half) አርማንዶ ሴጋቶን በሊቤሮነት በማሰለፍ ጭምር አዳዲስ ግኝቶችን መሞከሩን ተያያዘው፡፡ የግራ መስመር አማካዩን (Left-Winger) ማውሪሊዮ ፕሪኒ ቶርናንቴ(Tornate) ሆኖ እንዲጫወት ኃላፊነት ተጣለበት፡፡ በግራ መስመር አጥቂነት (Inside-Left) የሚሰለፈው ሚግዌል አንሄል ሞንቶውሪ ደግሞ ማውሪሊዮ ፕሪኒ የለቀቀው ቦታ ላይ መጫወቱ ቡድኑ ከተለመደው የአጥቂዎች ቁጥር ውጪ ትርፍ የመሃል አጥቂ (Spare Centre-Forward) እንዲያገኝ አደረገው፡፡ ይህ ሽግሽግ ያልተለመደ ቢመስልም ለጣልያን እግርኳስ የታክቲክ መሰረት መጣሉ አያጠያይቅም፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡