ሶከር ታክቲክ | የመጫወቻ አቅጣጫዎች

አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡


ታክቲካዊ ትንተና፦ በሉክ ጄጎ
ትርጉም- ደስታ ታደሰ

1) ሙሉው የሜዳ ክፍል (Whole Pitch)

ተጫዋቾች ሜዳ ላይ በጎንዮሽ እና በሜዳው ቁመት ከሚኖራቸው ጥግግት ባሻገር በጨዋታ ሽግግሮች ላይ ተጨማሪ ተፅዕኖ ከሚፈጥሩ ሁኔታዎች መካከል የመጫወቻ አቅጣጫዎች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ የመጫወቻ አቅጣጫዎች በተጫዋቾች መካከል ከሚፈጠር የአግድሞሽ ጥግግት ጋር ግንኙነት አላቸው፡፡ አልፎ አልፎ አንዳንድ ቡድኖች በጨዋታ ወቅት ሜዳውን በቁመትና በስፋት በመለጠጥ ሲጫወቱ ይታያሉ፡፡ይህ ታክቲካዊ የመጫወቻ አካሄድ አሉታዊ ጎኖች ይኖሩታል፡፡ የጎንዮሽና የቁመት ስፋቱ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ተጫዋቾች በርቀት የተበታተነ አቋቋም ይኖራቸውና የተጋጣሚ ቡድን የበዙ  ክፍተቶች ስለሚያገኝ ሽግግር ለመከወን ቀላል ይሆንለታል፡፡ ይሁን እንጂ ይህህ የአጨዋወት ሒደት መከተል የሚያስገኘው ጥቅምም አለ፡፡አጠቃላይ የሜዳውን ክፍል ክፍት የማድረግ ሥልት ኳስ እግሩ ሥር ላደረገ ተጫዋች በቂ ጊዜና የመቀባበያ አማራጭ መስመሮችን እንዲያጤን እድል ያስገኛል፤ ረዘም ላለ አንጻራዊ ደቂቃዎች የኳስን ቁጥጥር የበላይነት ለመውሰድም ይረዳል፡፡ ባየር ሚዩኒኮች ይህን መንገድ ከሚከተሉ ቡድኖች ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡


ምስል፦ ምንም እንኳ ኳሱ በግራው መስመር በሌሎች ተጫዋቾች የተያዘ ቢሆንም ምስሉ ፊሊፕ ላህም እና አርየን ሮበን በተቃራኒው የቀኝ መስመር ወደፊት ተጠግተው ቡድናቸው ከእነርሱ ሊያገኝ የሚገባውን የሜዳ ስፋት ሲያስገኙ ያሳያል፡፡

2) በመሃለኛው የሜዳ ክፍል (…Centrally)

ይኼኛው አቀራረብ መሃለኛውን የሜዳ ክፍል መርጦ ከመጫወት ጋር ይያያዛል፡፡ ለምሳሌ፦ የላይብዚሽ ቡድን በመሃለኛው ክፍል በርከት ባሉ ተጫዋቾች ሲጫወት እናያለን፡፡ እነርሱ ኳስን ቢቀሙ እንኳ ውጤታማ የመልሶ-መጫን ሽግግር (Counter-Press) ለማድረግ በቂ ተጫዋቾች ይኖራቸዋል፡፡

በእርግጥ ይህኛውንም የመጫወቻ አቅጣጫ ስንመርጥ ሽግግሮች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖዎች ሊፈጥርብን እንደሚችል መገንዘቡ አስፈላጊ ይሆናል፤ ስለዚህም ከአጨዋወት ሥርዓቱ ጎን ለጎን በቂ ትኩረት ልንሰጠው የሚጠበቅብን ጉዳይ መኖሩን ልናስተውል ይገባል፡፡ ይህን ዘዴ የሚተገብሩ ቡድኖች ኳስ ከተቀሙ ተቃራኒ ቡድን በሁለቱም ክንፎች ሰፊ ክፍተቶች ማግኘቱ እሙን ነው፡፡ ስለዚህም ጥሩ ሽግግር ለመከወን እንዲችል ይሆናል፡፡

ከዚህ በታች ባለው ምስል እንደምናየው በርንሌዮች በመሃለኛው የሜዳ ክፍል ላይ አመዝነው ይጫታሉ፤ ይህን ሲያደርጉ ኳስ ሊነጠቁ ይችላሉ፡፡ ሮቤርቶ ፌርሚኒሆ ኳሷን ሲያገኝ በግራና በቀኝ ሰይዱ ማኔ እና መሐመድ ሳላ በየመስመሮቻቸው ነፃ ሆነው የመቀባበያ አማራጮች ይፈጥሩለታል፡፡ ይህም ሽግግሩ የሚኖረውን የመሳካት እድል ከፍ ያደርገዋል፡፡ ሊቨርፑሎች ኳስ የነጠቁት በሜዳው ስፋት ቢሆን ኖሮ መጫወት የሚችሉት ወደ መሃል ብቻ ይሆን ነበር፡፡ ስለዚህም ኳስን የተነጠቀ ቡድን መስመሩን እንደ መከላከያ መስመር በመጠቀም ወደ ውጪ ይገፋቸው ነበር፡፡ አር-ቢ- ላይብዚሾች በአጨዋወት ዘይቤያቸው ይህን ታክቲካዊ ችግር መከላከል ይችላሉ፡፡ ቀድመው በሚያደርጉት ሽግግር ይተማመናሉ፡፡በተጨማሪም በመሃል ሜዳ ላይ ብዙ ተጫዋቾች መያዛቸው በሽግግሩ ጊዜ በተጋጣሚዎቻቸው የሚደርስባቸውን ጫና ለመቋቋም ይረዳቸዋል፡፡

ምስል፦


3) በሜዳው ስፋት (Wide Areas)

አንዳንድ ቡድኖች በተጋጣሚ ቡድን ዙሪያም ማዶ-ለ-ማዶ ሆነው ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ ምናልባት ኳስ የመነጠቅ አጋጣሚ (Loss of Possession)  ቢፈጠር እንኳ በሜዳው ሙሉ ቁመት ባሉት የስፋት ገደብ መስመሮች ነው፡፡ ቀድሞ እንደተጠቀሰው ተጋጣሚ ቡድኖች መልሶ-ጫና የመፍጠር እንቅስቃሴ ቢያደርጉ እንኳ ከጎሉ ቋሚዎች እስከ ማዕዘን ምት መምቻ ድረስ ያሉት የስፋት መስመሮች (By-lines) በሽግግሩ ቅጽበት እንደ ተከላካይ ሆነው ሊያገልግሉ ይችላሉ፡፡ ከታች በቀረበው ምሳሌ መሰረት አያክሶች ካሉበት ቦታ ኳስ ቢቀሙ ኳስ በሚይዘው አልያም በሚነጥቀው የተጋጣሚ ቡድን (ቶተንሃም) ተጫዋች ዙሪያ በቁጥር የበዙ ተጫዋቾች ስለሚኖራቸው ተጋጣሚያቸውን (ቶትንሃምን) በፍጥንት ፕረስ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተጋጣሚዎቻቸውን በሜዳው የጎንዮሽ መስመሮች እንዲቆዩ በማስገደድ ቶትንሃሞች ሊጫወቱ የሚችሉበትን ስፋትና የመቀባበያ አማራጭ ማዕዘናትን ያሳንሱባቸዋል፡፡

ምስል፦


የቅብብሎች ፍጥነት፣ መጠን እና ርዝመት

ኳስ የማቀበል ፍጥነት፣ መጠንና የቅብብሎቹ ርዝመት ልኬት የመከላከል ሽግግር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ በተለይ ረጃጅምና ፈጣን የኳስ ቅብብሎች የተጋጣሚ የመከላከል አደረጃጀት ላይ መረጋጋት እንዳይፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ይህም የሆነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እነዚህ ፈጣንና ረዘም ያለ የርዝመት ልኬት ያላቸው ቅብብሎች የአንድን ጨዋታ የትኩረት ማዕከል በየሰኮንዶቹ የመቀያየር አቅም ስላላቸው ነው፡፡  እነዚህ ተለዋዋጭ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ባህርያት ኳስ የመነጠቅ አጋጣሚ የተፈጠረበት ተጫዋች በፍጥነት ኳሱን የማስመለስና በቁጥጥር ሥር የማድረግ አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት የሚኖረውን ጊዜ ኢምንት ያደርጉበታል፡፡ ከምሳሌው የምንረዳው በርከት ባሉ ተጫዋቾች በሜዳው ቁመት እና በፍጥነት መጫወት ቶሎ ኳስን መልሶ ለማግኘት አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡ በማርኮ ሮስ ሥር ሲሰለጥን የነበረው ሬድ ቡል ሳልዝበረግ የመሃል ተከላካዮቹ ቀጥተኛና ረጃጅም ኳሶችን ብዙ ተጫዋቾቻቸው ወደሚገኙበት ክልል እንደሚልኩ ከታች በምስሉ ተመልክቷል፡፡ ይህም አልፎ አልፎ በጥቂት ቅብብሎች ብቻ ወደፊት እንደሚሄዱ ያሳያል፡፡ ከታች የሳልዝበርግ ተጫዋቾች በሜዳው ስፋት የሚንቀሳቀሱበትን መስመር መመለከት ይቻላል፡፡ ኳስ የመነጠቅ ሁኔታ ቢገጥማቸው ብለው ከኳሱ ጀርባ በርካታ ተጫዋቾች እንዲኖራቸቸው ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች ብዙውን ጊዜ ወደ ፊት የሚሄዱና ኳስን መልሶ ለማግኘት የሚጥሩ ናቸው፡፡ ተጫዋቾቹ ኳስ በተቀሙበት ቅጽበት ወይ ተጋጣሚ ቡድን ላይ ፈጣን የመልሶ-መጫን እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፥ አልያም ከቡድን አጋሮቻቸው  ስኬታማ ቅብብሎች ይላክላቸውና ወደፊት መገስገሳቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ከመሃል ተከላካዮቹ በረጅሙ የተላከላቸውም ኳስ የዚሁ ታክቲክ አንዱ ዕቅድ ነው፡፡ በምስሉ ላይ የታጀሉ መስመሮች የማይታዩትም እያንዳንዱ ተጫዋች የተጠና እንቅስቃሴያዊ አቋቋም ስለሚይዝ ነው፡፡

በሌላ  በኩል እንደ ማንችስተር ሲቲ ያሉ ቡድኖች በአጫጭርና በተሳኩ ቅብብሎች ጨዋታቸውን ይመሰርታሉ፡፡ በዚህ ሥልት በተጋጣሚ ቡድን ኳስ የመነጠቅ አደጋው አናሳ ይሆናል፤ ቡድኑ በኳስ ቁጥጥር የተረጋጋ እንቅስቃሴ እያደረገ ግማሽ ሜዳ ላይ እንዲደርስ ያስችለዋል፡፡ ጓርዲዮላ እንደሚለው “ተጨማሪ ቅብብል” ወደ ማድረግም ያዘነብላሉ፡፡ በአብዛኛው ተጫዋቾች በሚንቀሳቀሱባቸው ተከታታይ መስመሮች የጨዋታ ግንባታ ሒደቱን ያቀላጥፋሉ፡፡ በእርግጥ ሲቲዎች ከሳልዝበረጎች ይልቅ ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል ለመጠጋት ረዘም ያለ ጊዜ ይወስድባቸዋል፡፡ይሁን እንጂ ሲቲዎች ኳስ የመነጠቅ አጋጣሚያቸው አናሳ ይሆናል፤ በተጫዋቾቹ እንዲሁም በየመጫወቻ ዲፓርትመንቱ መካከል የሚፈጠረው ክፍተት ጠበብ ያለ በመሆኑ  በሽግግር ጊዜ የመጠቃት ተጋላጭነታቸው ይቀንሳል፡፡ ይህም ለጨዋታ ዘይቤያቸው በጣም አስፈላጊ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ከታች በቀረበው ምሳሌ በሜዳው ቁመት ለመሃል አጥቂው ወይም ለአጥቂ አማካዩ ረጅምና ቀጥተኛ ኳስ ከማቀበል ይልቅ ሲቲዎች በአጫጭር ቅብብሎች ወደፊት መጓዝን ይመርጣሉ፡፡ እንደ ሳልዝበርግ ካሉት ክለቦች በተለየም የተጋጣሚ ክልል ለመድረስ በዛ ያለ ጊዜ የሚወስድባቸው ለዚህ ነው፡፡ አንዳንዴ የመሃል ተከላካዩ ቪንሰ ኮምፓኒ ለበረኛው ኤደርሰን ጥንቃቄ የታከለበትና የተሳካ የኋላ ቅብብሎች የሚከውነው ለዚህ ይመስላል፡፡ ይህንን የሚያደርገው ከፊቱ በቅርብ ርቀት የተከላካይ አማካዩ ካልተገኘ ነው፡፡ በዚያው ቅጽበት የጨዋታውን ቴምፖ ለመቀየር ሲጥሩ እናስተውላለን፡፡ ይህንን በመከወን የተከላካይ አማካዩን ነፃ ያደርጉታል፤ ወይም ሌላ የመሃል ተጫዋች ይመጣና ተመሳሳዩን ተግባር ይፈጽማል፡፡ ከዚያም ጥንቃቄ በታከለበትና በተሳኩ አጫጭር ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ይጠጋሉ፡፡

ምስል፦

 


የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ