ፋሲል ከነማ የሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ውል ለማራዘም ተስማማ

ተጫዋቾቻቸውን የማቆየት ሥራን እየከወኑ የሚገኙት ዐጼዎቹ ከሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ሽመክት ጉግሳ እና በዛብህ መለዮ ጋር ውል ለማራዘም ስምምነትን ፈፀሙ፡፡

በሊጉ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ጠንካራ ስብስብን በመያዝ በፕሪምየር ሊጉ ጥሩ ቡድን ከገነቡ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ፋሲል ከነማ የአማካዩ ሱራፌል ዳኛቸውን ለሁለት ተጨማሪ አመት ለማቆየት መስማማቱ የሚታወቅ ሲሆን አሁን ደግሞ የመስመር አጥቂው ሽመክት ጉግሳ እና አማካዩ በዛብህ መለዮን ለማቆየት መስማማቱን በተለይ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ክለቡ ከሁለቱ ተጫዋቾች ጋር ጋር በጥቅማ ጥቅም እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ቅድመ ስምምነትን የፈፀሙ ሲሆን በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ በማምራትም ውላቸውን ያራዝማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በ2011 ደደቢት በመልቀቅ ወደ ዐፄዎቹ ቤት ያመራው እና ሁለት የውድድር ዓመታትን ቆይታ ያደረገው የቀድሞው የወላይታ ድቻ፣ አየር ኃይል እና ሀዋሳ ከተማ ተጫዋች ሽመክት ጉግሳ በጃኖ ለባሾቹ ቤት ድንቅ ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን አሁንም በክለቡ ቆይታው ዳግም ያንፀባርቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሌላው ውሉን ለማራዘም የተስማማው እና እንደ ሽመክት ሁሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ቆይታን ያደረገው አማካዩ በዛብህ መለዩ ወላይታ ድቻን ለቆ ፋሲልን ከተቀላቀለ በኃላ በወጥነት ለክለቡ ግልጋሎትን ሲሰጥ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ