“ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው” የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተስፈኛ አብርሐም ጌታቸው

በቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን ተቀይሮ በመግባት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያሳየ ያለው አብርሐም ጌታቸው የዛሬው ተስፈኛ አምዳችን እንግዳ ነው።

በኪነጥበቡ ካልሆነ በእግርኳሱ እምብዛም ሥሟ ከማይጠራው ፈረንሳይ ለጋሲዎን አካባቢ የተወለው የዛሬው ተስፈኛ አምዳችን እንግዳ አብርሀም ጌታቸው እንደማንኛውም ታዳጊ በሠፈር የጀመረው የእግርኳስ ጅማሮው በኃላም በ2009 በሐረር ሲቲ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ተቀላቅሎ መጫወት ጀምሯል። በመቀጠል በ2010 በኢትዮ ኤሌክትሪክ ተስፋ ቡድን ከተጫወተ በኃላ ነው። አሁን ወደሚገኝበት ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2011 ተስፋ ቡድኑን ተቀላቅሎ ጥሩ ቆይታ አድርጓል። በዋናው ቡድን እና በተስፋ ቡድን እየተመላለሰ ከ2012 ጀምሮ እየተጫወተ ይገኛል። ጠንክሮ ከሰራ ትልቅ ተጫዋች መሆን እንደሚችል ፍንጭ የሰጠበት ጨዋታ በተለይ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን በሰፊ የጎል ልዩነት 6-2 ባሸነፈበት ጨዋታ በሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅሆቭ በተሰጡት ዕድል ተቀይሮ በመግባት አስገራሚ እንቅስቃሴ በማድረግ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ አቡበከር ሳኒ ላስቆጠራት ስድስተኛ ጎል የእርሱ ድርሻ ከፍተኛ ነበር። ሶከር ኢትዮጵያም በወቅቱ የጨዋታውን ሪፖርት በገለፀችበት ፁሑፏ ይህን አጋርታ ነበር።

“በመልሶ ማጥቃት ከጎል ጀምሮ የሄዱት ፈረሰኞቹ በቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተስፋ ቡድን ዘንድሮ ያደገው እና እየተቀየረ በመግባት መጫወት የጀመረው ወጣቱ ተስፈኛ አብርሐም ጌታቸው በ89ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ለገባው አቡበከር ሳኒ አቀብሎት በግንባር በመግጨት ስድስተኛ እና የማሳረጊያውን ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 6-2 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።” ብላ ነበር። የወቅቱ ዓለማቀፋዊ በሽታ መጣ እንጂ አብርሃም እየተሰጠው ያለውን እድል በመጠቀም ጥሩ ነገር ማሳየት ችሎ ነበር። ወደፊት ብዙ ዕድሎች የሚጠብቁት ይህ ወጣት ተጫዋች የዛሬው የተስፈኞች እንግዳችን ሆኖ ይህን ነግሮናል።

“ተወልጄ ያደኩት ፈረንሳይ ለጋሲዎን ነው። እንዳጋጣሚ በሰፈሬ ብዙ አቅም ያላቸው ተጫዋቾችም ቢኖሩም በትልቅ ደረጃ የተጫወትኩ የመጀመርያው ያደርገኛል መሰለኝ፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ። ብዙ የአካባቢ ሰዎችም በእኔ እዚህ መድረስ ደስተኛ ናቸው። በ2008 ጥበብ በራስ ካሳ በሚባል ቡድን እየተጫወትኩ ጓደኛዬ ሐረር ሲቲ ይጫወት ስለ ነበረ ለአሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ይነግረውና ይምጣ ልየው ይላል። እኔም ሄጄ መሐል ባልገባ ብቻ ስጫወት አይቶኝ መርጦኝ በ2009 ሐረር ሲቲ ገብቻለው። ብዙም ሳይቆይ ሐረር ሲቲ በመፍረሱ ምክንያት ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአሰልጣኝ ኃይሉ ጋር ለአንድ ከሰራው በኃላ በ2010 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ መጥቻለው። ዓምና ጥሩ ቆይታ ነበረኘ ዘንድሮ ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ ዋናው ቡድን አድጌያለው።

“በሐረር ሲቲ እና በኤሌክትሪክ የመሐል ሜዳ ተከላካይ ሆኜ ነበር የተጫወትኩት ጊዮርጊስ መጥቼ ደግሞ የተከላካይ አማካይ ሆኜ እየተጫወትኩ እገኛለው። ከሲዳማ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ ከጎል ጀምሮ እየገፋሁ ሄጄ ለአቡበከር ሳኒ ከመስመር አሻግሬለት ያስቆጠረው ጎል። ለእኔ የእግርኳስ ህይወቴ ትልቅ መነሻ እና የበለጠ እንድሰራ የተነቃቃሁበት ጨዋታ ነው። በጥሩ መነሳሳት በቀጣይ የበለጠ ለመስራት እያሰብኩ የኮረና በሽታ መጥቶ ሊጉ ሊቋረጥ ችሏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በጣም የምወደው እንደ እናት አባት ያሳደገኝ ክለብ ነው። የተሰጠኝን እድል ከዚህ በበለጠ መጠቀም እፈልጋለው። አሁንም አልተቀመጥኩም በግሌ እየሰራው ነው። በኮሮና ሊጉ መቋረጡ የሚጎዳው ነገር ቢኖርም በብዙ ነገር ራሴን ለማስተካከል ጥሩ ጊዜ አግኝቼበታለው። እንደ ፈጣሪ ፍቃድ በቀጣይ ዓመት ከጊዮርጊስ ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ እሞክራለው።

“ምንተሰኖት አዳነ ለእኔ በጣም አርዓያዬ የሆነ የማከብረው ተጫዋች ነው። በጣም ትልቅ ስብዕና ያለው ለታዳጊዎች ትምህርት መስጠት የሚችል ትልቅ ተጫዋች ነው። ሌላው እንደርሱ ብጫወት ብሆን ብዬ የምመኘው ከምጫወትበት ቦታ አንፃር ደግሞ ሀይደር ሸረፋ ነው።

” የመሰለፍ እድል አላገኝም ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ሁልጊዜ ምንተስኖት ምን ይለናል መሰለህ ‘የእናተ ጨዋታቹ ልምምዳችሁ ነው። ልምምድ ላይ ጥሩ ከሆናችሁ ወደ ጨዋታ የማትገቡበት ምክንያት የለም።’ ይለናል። እርግጥ ነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ነው። በአንዴ ሰብሮ ለመውጣት ሊከብድ ይችላል። ይህ ግን አያሳስበኝም። ዘንድሮ ለእኔ የጠቀመኝ ወደ ዋናው ቡድንም እንድገባ ያስቻለኝ ልምምዴን በደንብ መስራት እና አሰልጣኜ የሚነግረኝን እና ተጫዋቾች የሚመክሩኝ በደንብ መስማት ነው። እኔ በግሌ ሁሉም ነገር በጊዜው ይሆናል ብዬ አምናለው። መቅደም የሚገባውን ነገር ማስቀደም ነው ከእኔ የሚጠበቀው። አሁን የማስበው በእግርኳሱ መድረስ የሚገባኝ ቦታ ለመድረስ መስራት ብቻ ነው። ለእኔ እዚህ ደረጃ እንድደርስ የረዳኝ መጀመርያ ፈጣሪዬ ነው እና እርሱን አመሰግናለው። በመቀጠል እናቴን በጣም አመሰግናለው። አባትም እናትም ሆና ተቸግራ በብዙ መከራ ነው ያሳደገችኝ እና እርሷን ከልቤ አመሰግናለው። ከታች ከፕሮጀክት ጀምሮ ያሰለጠነኝ ሰላምታው ምዳው (አቡሌ)፣ እስማኤል አቡበከር፣ መኮንን፣ ኃይሉ፣ አሳምነው ገብረወልድን በጣም ማመስገን እፈልጋለው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: