ስለ ታዲዮስ ጌታቸው ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

ጠንካራ ግብ ጠባቂዎች በተፈጠሩበት ዘመን የተገኘው እና በጣም ብልጥና ንቁ አንደሆነ የሚነገርለት፤ ብዙ መጫወት እየቻለ ሳይታሰብ የእጅ ጓንቱን ያወለቀው የዘጠናዎቹ ድንቅ ግብጠባቂ ታዲዮስ ጌታቸው ማነው?

አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስን ቁጭ አድርገው ይመክሩታል። ” አንተ በጣም ጎበዝ ከፍተኛ ልምድ ያለህ የሚሰጡህን ስልጠናዎች ቶሎ የመቀበል ችሎታ ያለህ ግብጠባቂ ነህ። በዚህ ሁኔታህ ወደፊት የግብጠባቂ አሰልጣኝ የመሆን ዕድልህ ሰፊ ይመስለኛል። ለምንድነው እነዚህን ልጆች የማታሰለጥነው ? ለአንተም ልምድ ይሆንሀል።” በማለት። ‘እሺ’ ብሎ ምክሩን የተቀበለው ደሳለኝ ታዲዮስ ጌታቸው እና ፀጋዬ ዜናን ማሰልጠን ይጀምራል። በዚህም አጋጣሚ በብልጠቱ የሚሰጡትን ነገሮች ቶሎ በመቀበል ፈጣን የሚባለው ታዲዮስ ጌታቸው የደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ አልጋ ወራሽ ሆኖ በዋናው ቡድን በፈረሰኞቹ ቤት ዋና ግብ ጠባቂ በመሆን ከዘጠናዎቹ መጀመርያ ጀምሮ ማገልገል ጀምሯል።

ታዲዮስ ትውልድ እና ዕድገቱ ሳር ቤት 08 ቀበሌ አካባቢ ነው። ተወልዶ ባደገበት ሾላ ሜዳ ላይ እግርኳስን እየተጫወተ ባለበት ሰዓት እንደአጋጣሚ ሆኖ አንድ ግብ ጠባቂ ይቀርባቸውና አንተ ግባልን ብለውት የተጀመረው የግጠባቂነት ህይወቱ በኃላ አብረውት በትምህርት ቤት ይጫወቱ የነበሩት ጓደኞቹ ኤልያስ እና ዜናው ገፋፍተውት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ “ሲ” ቡድን ለሙከራ እንዲሄድ ያደርጉታል። በወቅቱም የነበረው የታዳጊዎች አሰልጣኝ በታዲዮስ በብት ተደንቆ በ1984 ለቅዱስ ጊዮርጊስ “ሲ” ቡድን እንዲጫወት ይመረጣል። የመሬትም ሆነ የአየር ላይ ኳስ የመቆጣጠር አቅሙ ከፍተኛ እንደሆነ የሚነገርለት ታድዮስ ለስድስት ዓመት በ”ሲ” እና በ”ቢ” ቡድን ውስጥ ከብዙ ድሎች ጋር በሚገባ እየተገራ ማደግ ችሏል።

ከ1989 ጀምሮ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የቻለው ታዲዮስ እንዳጋጣሚ ሆኖ በዚህ ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ ወርዶ የነበረበት ጊዜ በመሆኑ ክለቡን ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ በተደረገው ጥረት ውስጥ ምንም ዓይነት ሽንፈት ሳያስተናግድ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንዲወጣ ካደረጉ ግብ ጠባቂዎች አንዱ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስን በአምበልነት በተለያየ ጊዜ መምራት የቻለውን ታዲዮስ አብረውት ከተጫወቱት ተጫዋቾች ውስጥ ሳምሶን ሙልጌታ (ፍሌክስ) ስለ ታዲዮስ እንዲህ ሲል ይናገራል። “ታዲዮስ ብዙ አቅሞች የነበሩት ግብ ጠባቂ ነው። በእግር መጫወት እና ቡድን መምራት ይችላል። በእርግጠኝነት የምትተማመንበት ግብ ጠባቂ ነው። ይህ ማለት አንተ ተከላካይ ሆነህ እንደ ታዲዮስ ዓይነት ግብ ጠባቂ ከኋላህ ካለህ ምንም የምትፈራው ነገር የለም። በራስ መተማመንህን ይጨምርልሀል። በአየር ላይም ሆነ በመሬት የተመቱ ጠንካራ ኳሶችን የሚያድንበት አቅሙ እና ሲፈነጠር በጣም ኃይለኛ የሆነ በአጠቃላይ ታዲዮስ ሙሉ የምትለው ግብ ጠባቂ ነበር። ባህሪውም የተሰማውን በግልፅ የሚናገር መልካም ባህሪ የነበረው ነው ተጫዋች ነው ።”

በቅዱስ ጊዮርጊስ ከታዳጊ ቡድን እስከዋናው ቡድን ድረስ ለ13 ዓመት ከተጫወተ በኃላ በ1997 ብዙም የመሰለፍ ዕድል በለማግኘቱ እና በተለያዩ ምክንያቶች በተፈጠረው ውዝግብ ክለቡ ለስድስት ወራት በቅጣት አግዶት መቆየቱ ይታወሳል። በመጨረሻም የታዲዮስ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ እህል ውሃ አብቅቶ ከአሳዳጊው ክለቡ ጋር ተለያይቷል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው የዋናው ቡድን ቆይታውም ሦስት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳት ችሏል። ከክለቡ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት በ1998 ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሊያመራ ችሏል። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ጥሩ የሚባል የውድድር ጊዜ እያሳለፈ በሚገኝበት ሰዓት ሳይታሰብ የሸገር ደርቢ ሊደረግ ቀናት ሲቀረው ወደ አሜሪካ መሔዱ በብዙ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ዘንድ በርካታ መላ ምቶች እና ውዥምብሮች እንዲፈጠር አድርጓል።

ታዲዮስን በማሰልጠን ጥሩ ግብ ጠባቂ እንዲሆን ያስቻለው አንጋፋው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ ታዲዮስን እንዲህ ይገልፀዋል ” በጣም ጠንክሮ ልምምዱን የሚሰራ ዲሲፕሊንድ የሆነ ግብ ጠባቂ ነው። የአንድ ግብ ጠባቂ መገለጫ መሆን ያለበት አብረውት ከሚጫወቱት ተጫዋቾች ጋር ያለው ግንኙነት ጥሩ መሆን ነው። ታዲዮስ በዚህ ረገድ ጥሩ የሚባል አቅም ነበረው። ጨዋታን አይቶ ቀድሞ የማንበብ ችሎታ ያለው ፣ ደፋር ፣ የማይፈራ ፣ ታይሚንግ አጠባበቁ እና የመስፈንጠር አቅሙ ከፍተኛ የነበረ ግብ ጠባቂ ነው። እያደረ እየበሰለ የሚሄድ ሆኖ ሳለ ፣ ብዙ መጫወት እየቻለ በአጭ አቋርጦት ሄደ እንጂ ጎበዝ ግብ ጠባቂ ነው።”

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ1989 ጀምሮ ከታዳጊ ቡድን አንስቶ በወጣት እና በዋናው ቡድን መጫወት የቻለው ታዲዮስ የ1994 እና 1998 የሴካፋ ዋንጫዎችን ማንሳት የቻለ ነው። ብዙ የመጫወት አቅሙ እያለው ሳይጠበቅ ወደ አሜሪካ የሄደው ታዲዮስ ከሀገሩ ከወጣ አሁን አስራ አራት ዓመት ሆኖታል። በዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከቦች አምዳችን እንግዳ አድርገነው በአጠቃላይ ያለውን ሀሳብ እንዲህ አካፍሎናል።

“በቅዱስ ጊዮርጊስ ከታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን በነበረኝ ቆይታ እጅግ ብዙ ስኬቶች ያገኘሁበት አስደሳች ቆይታ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ታች ወርዶ እርሱን ለመመለስ አንድም ጨዋታ ሳንሸነፍ ወደ ፕሪምየር ሊግ የመለሰንበት እና በ1995 የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያነሳንበት አጋጣሚ በእግርኳስ ህይወቴ መቼም የማልረሳው አስደሳች ጊዜ ነበር።

“በ1997 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ትንሽ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። ብዙም እሰጥ አገባዎች እና አለመግባባቶች ተፈጥረው ነበር። የመሰለፍ ዕድልም ያጣሁበት ጊዜ ነበር። ምክንያቱን አሁን ብዙም ማንሳት አልፈልግም። መሐል ላይ እየተጫወትኩኝ ባለበት ሰዓት ለስድስት ወር ተቀጥቼ ነበር። በዚህም በጣም ከፍቶኝ ነበር። በመጨረሻም በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስላልፈለኩ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተለያይቼ ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርቻለው።

” ኢትዮጵያ ቡና በነበረኝ ቆይታ ጥሩ ጊዜ አሳልፌአለው። ቡድኑም አሪፍ ስብስብ ነበር። እኔም በነበረኝ ጥሩ እንቅስቃሴ የተነሳ ከብሔራዊ ቡድን ለሁለት ዓመት ርቄ በድጋሚ ተመርጬ ለመጫወት ችያለው። እንደ አጋጣሚ ውድድሩ ሰኔ ወር አካባቢ ተቋርጦ ስለነበረ ወደ አሜሪካ ልሄድ ችያለው። እኔ ከሄድኩ በኃላ ብዙ ነገሮችን ሰምቻለው፤ ግርታዎችም ነበሩ። ውድድሩ ከተቋረጠ በኃላ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጨዋታ ነበረን። በዚህ ምክንያት ‘የቅዱስ ጊዮርጊስ ሰዎች ናቸው ወደ አሜሪካ የላኩት’ ተብሎ የግለሰብ ስም እየተጠራ ሲወራ ሰምቻለው። ግን የእኔ አሜሪካ መሄድ የፈጣሪ ፍቃድ ብቻ ነው። የማንም ሰው እጅ የለበትም። በአጋጣሚ የሆነ ነገር ነው። የግለሰብ ሰዎች ስም ሲጠራ ነበር። ስለዚህ በእኔ አሜሪካ መምጣት ማንም ሰው ተሳትፎ አላደረገም።

“እኔ በምጫወትበት ዘመን እጅግ ለመምረጥ የሚያስቸግሩ ጎበዝ ግብ ጠባቂዎች በሁሉም ክለቦች ዘንድ ነበሩ። የሚገርመው እኛ በነበርንበት ዘመን የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ የሚባል አልነበረም። እኛ ጋር ደሳለኝ ሲያቆም የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ የመጣው እንጂ ከታች ከሰፈር ጀምሮ ዋናው ቡድን እስክንገባ ድረስ አሰልጣኝ አልነበረንም። ሌላውም ክለብ ውስጥ ዋናው አሰልጣኝ ወይም ረዳቱ ካልሆነ በቀር የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ የለም። እኔ እንዳውም ደሳለኝ ካቆመ በኃላ እርሱ አሰልጥኖኝ ጥሩ ልምድ ማግኘት ችያለው እንጂ አሰልጣኝ የለንም። በራሳችን ጥረት በነበረን ከፍተኛ ፍላጎት ጠንክረን በመስራታችን የመጣ ነው። ከዚህ ውጪ በዛን ዘመን የነበርን ግብ ጠባቂዎች ከነበረን ተመሳሳይ አቋም አንፃር በክለብም በብሔራዊ ቡድንም ቋሚ ተሰላፊ ለመሆን እና ያገኘነውን ቦታ ለማስጠበቅ ስንል በምንሰራው ጠንካራ ልምምድ ብዙ ግብ ጠባቂዎች በዚያ ዘመን ልንወጣ ችለናል።

” ለመቆጣጠር የምቸገርባቸው በጣም ጥሩ የሚባሉ በግሌ የማደንቃቸው ጎበዝ አጥቂዎች ነበሩ። በተለይ ከእኔ ጋር አብረው የተጫወቱት አሸናፊ ሲሳይ እና ስንታየሁ ጌታቸው (ቆጬ) ጥሩ አቅም የነበራቸው አጥቂዎች ናቸው። ከኔ ክለብ ውጪ በብሔራዊ ቡድን አብሮኝ ረጅም ጊዜ የተጫወተው ዮርዳኖስ ዓባይ በጣም ጎበዝ እና የማደንቀው አጥቂ ነው። እነዚህ የኛ ዘመን ግብ ጠባቂዎችን የሚፈትኑ አጥቂዎች ነበሩ።

“አሁን ላሉት ለግብ ጠባቂዎች ከልምዴ መናገር የምፈልገው። አሁን በሁሉም ቡድን ውስጥ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ አለ ይሄ ጥሩ ነገር ነው። ግን ከዚህ በተጨማሪ ራሳቸው ግብ ጠባቂዎች የራሳቸውን ተነሳሽነት መፍጠር አለባቸው። ግብ ጠባቂበት ብዙውን ጊዜ በልምምድ ከምታደርጋቸው ነገሮች ባለፈ የራስህ ቅልጥፍና እና ንቃት የሚያስፈልገው በመሆኑ የራስ ጥረት ያስፈልገዋል። በአሁን ሰዓት አብዛኛዎቹ የሊጉ ቡድኖች ውስጥ የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂዎች በጣም በዝተዋል ፤ ይህ ነገር በዚህ ባይቀጥል ደስ ይለኛል። ይህ ይመስለኛል ኢትዮጵያውያን በረኞች የራሳቸውን አቋም እያስተካከሉ እንዳይሄዱ ያደረጋቸው። ሀገሬ በመጣሁነት ሰዓት ጨዋታዎችን የማየት ዕድሉ ነበረኝ። አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ጥሩ ግብ ጠባቂዎች እንዳሉ አይቻለው። የዛኑ ያህል ደግሞ አንዳንዶቹ ብዙ ችግር እንዳለባቸው አይቻለው። ይህ ድክመታቸውን በስራ ማሻሻል እና መለወጥ ይችላሉ ብዬ ነው የማስበው።

“ወደፊት ወደ ሀገሬ መጥቼ የመኖር ዕቅዱ አለኝ። ግን መጥቼ በምኖርበት ጊዜ ወደ ስፖርቱ ውስጥ የምገባ አይመስለኝም። ምንም ዓይነት እቅድ የለኝም። መጥቼ በሀገሬ መኖሬ አይቀርም። ግን የራሴን የሆነ ነገር ለመስራት ነው የማስበው ከስፖርቱ ውጭ ማለት ነው።”

“የቤተሰብ ህይወቴ እንግዲህ በ1998 ከሀገሬ ከወጣው በኃላ እስካሁን ኑሮዬን በአሜሪካ ካደረኩኝ 14 ዓመት ሆኖኛል። ባለ ትዳር ነኝ በከባለቤቴ ያገኘኋቸው ሁለት ልጆችም አሉኝ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: