ይህንን ያውቁ ኖሯል? (፭) | የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ክለቦች…

ዕለተ ሐሙስ በምናቀርበው ይህንን ያውቁ ኖራል? አምዳችን ስለ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ክለቦች እውነታዎችን ስናቀርብ ቆይተናል። ዛሬም በሊጉ እና ክለቦች ዙርያ ያሉ እውነታዎችን በክፍል 5 ጥንቅራችን ይዘንላችሁ ቀርበናል።

1 – በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ21 ዓመታት ታሪክ ፎርፌን ጨምሮ 4353 ጨዋታዎች ተደርገዋል።

2 – በሊጉ ታሪክ ኤርትራዊያንን ሳይጨምር የውጪ ዜጋ ተጫዋች በመጠቀም ቀዳሚው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። በ1995 ክለቡን የተቀላቀለው ኬንያዊው ፍራንሲስ ቼንጂሊ ለሊጉ የመጀመርያ የውጪ ዜጋ ነው።

3 – በአሰልጣኝ ረገድ ደግሞ መብራት ኃይል ከሊጉ ክለቦች የመጀመርያው የውጪ ዜጋ አሰልጣኝ የቀጠረ ክለብ ነው። በ1995 ጣልያናዊው ጁሴፔ ፔትሬሊ የፕሪምየር ሊግ ክለብ ያሰለጠኑ የመጀመርያ የውጪ ዜጋ ናቸው።

4 – ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚያድጉ ክለቦች ላይ የተለያዩ ህጎች ሲወጡ ኖረዋል። ከነዚህም መካከል በ1992 የወጣው ከአንድ ክልል ከአንድ በላይ ክለቦች መሳተፍ አይችሉም የሚል ሲሆን በሁለተኛው የሊግ እርከን ጥሩ ጉዞ ሲያደርጉ የነበሩ ክለቦች በዚህ ሕግ ምክንያት ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደግ ሳይችሉ ኖረዋል። ሕጉ በ1997 ተሽሯል።

5 – የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአፍሪካ ውድድሮች ፎርማት ምክንያት እስከ ዘጠናዎቹ አጋማሽ ድረስ የነበረው ዋጋ በአንፃራዊነት ከፍ ያለ ነበር። ከ2004 (እ/ኤ/አ) በፊት በአፍሪካ 3 ውድድሮች የነበሩ በመሆናቸው ከቻምፒዮኑ (ቻምፒየንስ ሊግ) እና የጥሎ ማለፍ አሸናፊው (ካፍ ዊነርስ ካፕ) በተጨማሪ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ የሚያጠናቅቀው ቡድን ለካፍ ዋንጫ (Cup Cup) ውድድር ያልፍ ነበር። በዚህ ረገድ ውድድሩ ከመሰረዙ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ይህን ውድድር የተካፈለው በ1994 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና ነበር።

6 – በሊጉ ታሪክ ዝቅተኛ ቡድን የወረደበት ዓመት 1999 ዓ/ም ነው። በዚህ የውድድር ዘመን ላይ የተካፈሉት ሁሉም ክለቦች በ2000 ዓ/ም ላይ በተደረገው ውድድር እንዲካፈሉ በመደረጉ ምንም ወራጅ አልነበረም።

7- በአንድ የውድድር ዓመት በጠቅላላ ጥቂት ጎሎች የገቡበት ዓመት 1990 ዓ/ም ላይ ነው። በዚህ የውድድር ዘመን የተሳተፉት 8 ክለቦች በአጠቃላይ 188 ግቦችን ብቻ ነበር ያስቆጠሩት። ይህም በሊጉ ታሪክ ዝቅተኛ ግቦች የተቆጠሩበት ዓመት ሆኖ አልፏል።

8 – በተቃራኒው በአንድ የውድድር ዓመት በርካታ ጎሎች የተስተናገዱበት የውድድር ዘመን 2002 ዓ/ም ላይ ነው። በዚህ ዓመት በተደረጉ አጠቃላይ ጨዋታዎች ላይ ቡድኖች በድምሮ 669 ጎሎች ከመረብ አገናኝተዋል።

9 – በሊጉ ታሪክ ጥቂት ጨዋታዎችን ያደረገው ክለብ ፐልፕ እና ወረቀት ነው። ይህ ክለብ በ1990 በነበረው ብቸኛ ተሳትፎ 14 ጨዋታዎችን ብቻ በሊጉ አከናውኗል።

10 – በሊጉ ታሪክ በርካታ ክለቦች ያደጉበት እና የወረዱበት ዓመት 2000 ዓ/ም ላይ ነው። ሚድሮክ ሚሌኒየም ፕሪምየር ሊግ በሚል መጠሪያ የተደረገው የዚህ ዓመት የውድድር ዘመን በአጠቃላይ 25 ክለቦች ተሳትፈውበታል። በዚህም 11 ክለቦች ከታችኛው የሊግ እርከን አድገው በውድድሩ እንዲሳተፉ ሆነዋል። (ካደጉት 11 ክለቦች መካከል እህል ንግድ እና ደቡብ ፖሊስ ብቻ በውድድር ሲያደጉ ቀሪዎቹ 9 ቡድኖች በፌዴሬሽኑ አማካኝነት ያደጉ ነበሩ።) በተቃራኒው ውድድሩ ሲያበቃ 11 ክለቦች እንዲወርዱ ተደርጎ የ2001 የውድድር ዘመን በ16 ክለቦች መካከል ተከናውኗል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ