በቤልጂየም ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች የሚሰጠው ስልጠና ዛሬ ከሰዓትም ቀጥሏል

በኳታር እና ቤልጂየም እግርኳስ ፌዴሬሽን የጋራ ትብብር የተዘጋጀው የኦንላይን ስልጠና ዛሬ ከሰዓት ለ2ኛ ጊዜ ሲሰጥ የሀገራችንም አሰልጣኞች በስልጠናው ላይ ተካፍለዋል።

በቤልጂየም የእግርኳስ እድገት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየተሰጠ ያለው ይህ የኦንላይን ስልጠና ሀሙስ ምሽት እንደተጀመረ ይታወቃል። ሀሙስ በነበረው ቆይታም በግብ ጠባቂዎች ላይ ያተኮተ ትምህርት በቤልጂየም የወጣት ቡድን አሰልጣኝ ፓትሪክ ክሪመርስ አማካኝነት ተሰጥቷል። በዚህ ስልጠና ላይም የኢትዮጵያ ወንዶች እና ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች እንዲሁም የኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች እንደተሳተፉ ታውቋል።

ስልጠናውን ያዘጋጁት አካላት በማስፈቀድ እየተሳተፉ የሚገኙት የሃገራችን አሰልጣኞች ዛሬ ከሰዓትም በ2ኛ ክፍል የስልጠና መርሃ ግብር ትምህርት ወስደዋል። በዛሬው የኦንላይን የትምህርት መርሃ ግብር ላይ ደግሞ ስለቤልጂየም ብሄራዊ ቡድን የስኬታማነት ጉዞ ላይ ያተኮረ ትምህርት ተሰጥቷል። በተለይ ቤልጂየም ወደ ታላቅነት ለመምጣት የተከተለቻቸውን መርሆች እና የስልጠና መንገዶች በተብራራ መንገድ ጋይ ቤከር እንደሰጡ ስልጠናውን የወሰዱት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

ይህንን ስልጠና የወሰዱ አብዛኞቹ የሃገራችን አሰልጣኞች ጥሩ ትምህርቶችን እንደቀሰሙ ተናግረዋል። በተለይ የሀሙሱን የግብ ጠባቂዎች ስልጠና የተከታተሉ የተለያዩ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ተመሳሳይ ስልጠናዎች በቀጣይነት እንዲመቻች መጠየቃቸውን ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ አያይዘው ገልፀዋል።

በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በአሰልጣኝ አምሳሉ ፋንታሁን እና ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ አስተባባሪነት እግር ኳስ እና ቴክኖሎጂ በሚል ርዕስ ለሃገራችን አሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ