የደጋፊዎች ገፅ | ከመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊ ማኅበር ፕሬዝዳንት የማነ ደስታ ጋር

ከዚህ ቀደም ከደጋፊዎች ጋር የተያያዙ ፅሁፎች ማቅረባችን ይታወሳል ለዛሬ ደግሞ ከመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊ ማኅበር ፕሬዝዳንት የማነ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ማኅበሩ ራሱን ለማሻሻል ምን ዓይነት ስራዎች እየሰራ ነው?

ማኅበራችን የረጅም እና የአጭር ጊዜ ዕቅዶች አሉት። እንቅስቃዎች ከማቋረጣቸው በፊት አመራር ላይ ለውጥ ለማድረግ እያሰብን ነበር። ሁሉንም ደጋፊዎቻችን ያሳተፉ ክፍት የደጋፊዎች ውይይት ለማድረግ ሁኔታዎች አጠናቀን ነበር ፤ መጀመርያ መቅደም ያለበት እሱ ነው ብለን ስላሰብን ማለት ነው። በመተዳደርያ ደንባችን አመራሩ በሦስት ዓመታት ይመረጣል ፤ ሆኖም አመራሩ ለደጋፊው የሚመጥን ስራ ካልሰራ በየትኛውም ጊዜ መቀየር አለበት ነው የምንለው። ምክንያቱም ማኅበሩ ለክለቡ አጋዥ እንዲሆን ከተፈለገ በዚህ መንገድ መሄድ ይጠበቅብናል። እኔ ወደ ፕሬዝዳንትነቱ ከመጣው አራት ወራት አስቆጥሪያለው ፤ ወደዚህ ስልጣን ከመጣሁ በኃላም ክለባችን በተሻለ መንገድ መለያ እንድያመጣ ትልቅ ጥረት በማድረግ ላይ ነን ፤ ይህም ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ደርሷል። ውል ተዋውለን ጊዜ ወስደን ስለ ጥራቱ እና ዲዛይኑ ተወያይተንበታል። ይህ ወደ ቦታው ከመጣው በኃላ በጋራ ያሳካነው ትልቅ ስራ ነው። በሰፊው ግን ቅድም ያልኩህ መላው ደጋፍያችን የሚገኝበት ውይይት ከተደረገ በኃላ የደጋፊያችንን ሀሳብ ተንተርሰን የምናሻሽላቸው ነገሮች ይኖራሉ።

ባለፈው ዓመታት ደጋፊ ማኅበሩ ምን አሳክቻለው ይላል?

የሚቀሩን ነገሮች ቢኖሩም እንደ ማኅበር ብዙ ነገር አሳክተናል። ክለቡ በሀገር ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ደጋፊ እንዲኖረው ማሕበሩ ትልቅ እገዛ አድርጓል። በተለይም ደግሞ በማኅበራዊ ጉዳዮች ያሳካናቸው ነገሮች ቀላል የሚባሉ አይደሉም። ይህም ክለቡ በማሕበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ከፍ እንዲል አድርጓል። በደም ልገሳ ፣ በህዝባዊ በዓላት ወቅት እገዛዎች በማድረግ ፣ በከተማ ፅዳት እና በሌሎች ብዙ ነገሮች ትልቅ ስራ ሰርተናል። በቂ ስራ ሰርተናል ብለን ባናስብም ብዙ ነገር አሳክተናል። በሸራተን በተደረገው ስብሰባ ሁሉም ክለቦች በአቀባበል እና በሌሎች ነገሮች በልዩ ሁኔታ አመስግነውናል። ደጋፍያችን ከሌሎች ክለቦች ጋር ያለውን ግንኙነት እንድያጠናክርም በተለያዩ መንገዶች ጥረት አድርገን አመርቂ ውጤት አምጥተናል። በተለይም በአንዳንድ ወሳኝ ጨዋታዎች ደጋፊያችን ያሳየው ፍፁም ጨዋነት ለዚህ ትልቅ ምስክር ነው።

ክለቡ እና ደጋፊ ማኅበሩ በጋራ የመስራት ችግር አለባቸው ተብሎ ለሚነሳው ጥያቄ ያለው ሀሳብ አለህ ?

የመረዳዳት ችግር የለብንም። ማኀበሩ ደጋፊው በሚፈልገው መጠን አልሰራም እንጂ ከክለቡ ጋር ይሄ ነው የሚባል ችግር የለበትም። በተለይም በአሁኑ አመራር በጣም በቅርበት እየሰራን ነው ፤ አሁን ለማካሄድ ያሰብነው ክፍት ውይይት ላይ ሀሳብ ስናቀርብላቸው በደስታ ነው ሀሳባችንን የተቀበሉት። ከማኅበሩ ጋር አብሮ ለመስራት ያለው ተነሳሽነት ጥሩ ነው ፤ የሚባለው ነገር ከእውነት የራቀ ነው። የክለባችን ቦርድ እየሰራው ላለው ነገርም እንደ ማኅበር ትልቅ አክብሮት አለን ፤ ሌሎች ክለቦች የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ በገቡበት ወቅት ክለባችን በተረጋጋ መንገድ መጓዙ ትልቅ ነገር ነው።

ስታዲየም ከሚገባው ደጋፊ አንፃር ዝቅተኛ ስለሆነው የተመዘገበ ደጋፊ ምን እየሰራችሁ ነው ?

በተደጋጋሚ ጊዜ ተናግረነዋል፤ በቀጣይ በምናደርገው ክፍት ውይይት ግን እንደ ትልቅ አጀንዳ የምናነሳው ጉዳይ ነው። ደጋፊው በተደራጀ መንገድ ተመዝግቦ ክለቡን የሚደግፍበት መንገድ እያመቻቸን ነው። ክለቡ የሚያመጣቸው ነገሮች በቅድምያ የምንሰጥበት መንገድ እያመቻቸን ቁጥሩን ከፍ እናደርገዋለን። ባጠቃላይ ግን ደጋፊ አመዘጋገብ ላይ ክፍተቶች ነበሩብን ይህንንም እናስተካክላለን ፤ ከማኅበራችን ጋር በጋራ ይህንን ችግር ለማስተካከል የሚፈልግ አካል ካለም በራችን ክፍት ነው።

ስለ ደጋፊው ዋነኛ የመልያ ጥያቄ ማሕበሩ ምን ዓይነት አቋም አለው ?

ደጋፊያችንን በሚመጥን ደረጃ መለያ መቅረብ እንዳለበት እናምናለን። ክለባችን በተለያዩ ደረጃዎች መለያ በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት የሚችል የደጋፊ አቅም አለው። ባለፉት ወራት የደጋፊያችን ፍላጎት ለማማሏትም ስራዎች እየሰራን ነው ፤ የክለባችን ቦርድም ይህን ነገር በመረዳት ስራዎች እየሰራ ነው። ከዚህ ቀደም መለያ መሸጥ ላይ የነበሩንን ክፍተቶች ከወጋገን ባንክ ጋር በመነጋገር ፈትተነዋል ፤ ተዓማኒነቱን በጠበቀ መልኩ የሚሰራ ስራ ነው ይህንን አስጠብቀን እንሄዳለን። አሁን ደግሞ አዲስ መለያ በማሰራት ላይ ነን ፤ ሂደቱን አጠናቀናል።

በመለያ ዙርያ በጥራት እና በብዛት የደጋፊውን ጥያቄ ለመመለስ እንደ ደጋፊ ማኅበር ምን እየሰራችሁ ነው ?

በተወካዮቻችን አማካኝነት የደጋፍያችንን ፍላጎት ለማሟላት ከክለባችን ጋር አብረን እየሰራን ነው። በጥራት ደረጃ ከሌሎች ክለቦች የሚሻል ወይም በነሱ ተመሳሳይ ጥራት ላይ ያለ መለያ ለማሰራት ተስማምተን ሂደቶች ጀምረናል።
ደጋፊያችንም የክለቡን ፋይናንስ ለማጠናከር ህጋዊውን መለያ በመግዛት የበኩሉን እንዲወጣ ለመግለፅ እንወዳለን። ከዚህ በፊት በሰፈር ወይም በግሩፕ ህጋዊ ያልሆኑ መለያዎች ይሰሩ ነበር። አሁን እሱ ነገር ይቀራል ብለን እናስባለን። በእኛ በኩልም እሱን ለመቅረፍ የሁሉ ደጋፊያችንን ፍላጎት የሚያሟላ ሙለያ በማሰራት ላይ ነን። ከዚህ ቀደም በግሩፕ የተሰሩት መለያዎችም በፋይናንስ እና በሜዳ ድምቀት ላይ እክል ፈጥረዋል። እንደ ማኅበርም ሁለት ግለሰቦች ተወክለን እየሰራን ነው። እኔና በሱራፌል ካሕሳይ ይህንን ስራ እየሰራን ነው።

ከመለያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከትጥቅ አምራቾች ጋር የመስራት ችግር አለበት ስለሚባለው ነገርስ ?

ከዚህ በፊት ኢሪያን ጨምሮ ከሌሎች አምራቾችም ጋር ለመስራት ጥረት አድርገን ነበር ፤ ነገር ግን ከገቢ አንፃር አዋጭ አይደለም። እንደ ማኅበርም በሂደቱ ተሳትፌ ነበር ፤ እንደ ደጋፊያችን ብዛት ግን በአሰራሩ ክለባችን ተጠቃሚ አይሆንም። ለጊዜው እንደ ክለብ ለማቅረብ ጥረት እናደርጋለን የተሻለ ነገር ከቀረበ ግን ክለባችን ዝግጁ እንደሆነ ነው እንደ ማኅበር የምናውቀው። በርግጥ እስካሁን ድረስ ይህን ማድረግ እንችን ነበር ግን ክለባችን በማርኬቲንግ ላይ አንዳንድ ክፍተቶች አሉበት ፤ በቅርቡ ይቀረፋል ብዬ ተስፋ አደርጋለው። እንደ ማኅበር ግን ይህ የስራ ድርሻችን አይደለም ፤ በቀጣይ ክለቡ ትኩረት አድርጎ ይሰራበታል ብዬ አስባለው።

ማኅበሩ ላይ የግልፅነት ችግሮች ይነሳሉ…

ደጋፊ ማኅበር ገንዘብ አግኝቶ አያቅም ባይ ነኝ። ከዚ በፊት የክልል መስተዳድር አራት መቶ ሺህ ብር ድጋፍ አድርጎልን ነበር፤ በሱም ስራዎች ሰርተንበታል። እንግዳ ክለቦች ሲመጡ በዛ ብር ነበር ስናስተናግዳቸው የነበረው። ሌላ ከራያ ቢራ ከአንድ ቢራ ላይ የተወሰነ ሳንቲም ለማኅበራችን ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተን ነበር፤ በዚ ሰዓት ከማኅበሩ ይልቅ ለክለቡ ቢሰጥ ብለን ለክለቡ ነው እየተሰጠ ያለው። ብዙ የሚስተካከሉ ነገሮች ነበሩብን፤ የደጋፊ ማኅበር ፅሕፈት ቤት ማስተካከል እና የሽያጭ ማእከል መክፈት አስበናል። እኔ ወደ ኃላፊነት ከመጣሁ በኃላ ምንም አይነት ገንዘብ አላንቀሳቀስንም፤ የተቀበልነው ገንዘብንም የለም። የሚወራው ነገር ከእውነት የራቀ ነው። ጥያቄ የሚያነሱት ወደ ማሕበሩ ቀርበው ቢያዩት ደስ ይለኛል። በአጠቃላይ ያለው ነገር ኦዲት እየተደረገ ነው፤ በቅርቡ ግልፅ ይሆናል። ባለፈው ዓመት የመጀመርያ ጨዋታዎች ራሳችን የትኬት ሽያጭ አድርገን ነበር። ካገኘነው አምስት ፐርሰንት የትኬት ሽያጭ ላካሄዱት አምስት ፐርሰንት ለማኅበሩ ገቢ ተደርጎ ነበር። ከዛ በኃላ ግን ያገኘነው ገንዘብ የለም። ስለ ክፍተቶቻችን ጥያቄ ከሚያቀርቡት ጋር በስብሰባው ላይ እንወያያለን።

ማኅበሩን ለማሻሻል ምን አቅዳችኃል?

በትልቁ ስለዚህ ጉዳይ ለመወያየት ውይይት እናዘጋጃለን። ከዛ የደጋፊው ፍላጎት መሰረት አድርገን ሥራዎች እንሰራለን። ቅድም የጠቀስኩልህ ከሽያጭ ማእከልም እናዘጋጃለን። ከማልያ ጋር በተያያዘ ያለው ጥያቄ ደግሞ በሰፊው ለመመለስ አሁን ሥራዎች ጀምረናል።

ከዚህ በፊት በህጋዊ ባልሆኑ ነጋዴዎች ክለቡ ከስሯል ተብሎ ስለሚነሳ ጥያቄ ?

መጀመርያ እኛ ብቁ ማልያ አቅርበን ገበያውን ለማሸነፍ እንሰራለን። ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ነጋዴዎቹን በህግ ለመጠየቅ እንሰራለን። በማልያው ዲዛይንም ህጋዊ መብት ወስደን ይህንን የሚጥሱ ህጋዊ ያልሆኑ ነጋዴዎችን ጠበቃ አቁመን በፍርድ ቤት እንከሳቸዋለን። በዚህ የማያወላውል አቋም ይዘን ሽያጭ እናካሂዳለን።

በስታዲየም ፀጥታ ዙርያ ያሳካችሁትን ስኬት ለማስቀጠል ምን አይነት ሥራዎች ለመስራት አስባችኋል?

ለዚህ ደጋፊያችን ትልቅ ሚና ነበረው፤ በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለው። በስታዲየም ፀጥታ ለመጠበቅ በስነ-ምግባር ምስጉን የሆኑ እና ተሰሚነት ያላቸው ደጋፊዎች አማካኝነት ነው ይህን ትልቅ ስራ የሰራነው።

በመጨረሻ…

በብዙ ረገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለ ያለ ምስጉን ደጋፊ ነው ያለን። ደጋፊውን ለመግለፅ ቃላት የለኝም። ይህንን ትልቅ ደጋፊ በማገልገሌ ኩራት ይሰማኛል። ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት ክለብ ነው፤ ይህ ክለብ የማንም አይደለም የደጋፊው ነው። ደጋፊ ሸልም ብባል ከምሸልማቸው ደጋፊዎች አንዱ የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊን ነው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: