አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ሊደረግለት ነው

በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አዘጋጅነት እየተካሄደ ባለው የስፖርት ሴክተር ዓመታዊ ጉባዔ ላይ የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ሊደረግለት እንደሆነ ተገልጿል።
በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አዘጋጅነት የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ያካተተ የስፖርት ሴክተር ዓመታዊ ጉባዔ ዛሬ እና ነገ እንደሚከናወን መገለፁ ይታወቃል። በጉባኤው ላይም የቀጣይ የሴክተሩ ስትራቴጂክ ዕቅድ፣ የ2012 ሪፖርት እና 2013 በጀት ዓመት ዕቅድ፣ የተሻሻለው የሀገር አቀፍ ስፖርት ማህበራት ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ፣ የኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ የተዘጋጀው የማገገሚያ ስትራቴጅክ ሰነድ እና የስፖርት ማህበራት መመዘኛ ስታንዳርድ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል።

በዛሬው ውሎም ኮሚሽኑ የአዲስ አበባ ስታዲየምን በ2013 ለማደስ ማቀዱን አስረድቷል። ንብረትነቱ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የሆነው ይህ አንጋፋ ስታዲየም ከካፍ በመጡ ገምጋሚዎች ለአህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ ውድድሮች ብቁ እንዳልሆነ መገለፁ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ ስፖርት ኮሚሽኑ 25 ሚሊዮን ብር ለእድሳት በማውጣት ስታዲየሙን የማብቃት ስራ በ2013 እንደሚሰራ ጠቁሟል። ኮሚሽኑ በገለፃው ወቅት ለእድሳቱ አስፈላጊ ነው የተባለውን 25 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሚኒስቴር መፍቀዱንም አያይዞ አስረድቷል።

ጥቅምት 23 ቀን 1940 የመሰረተ ድንጋይ የተጣለለት ይህ ዕድሜ ጠገብ ስታዲየም ሦስት የፍፃሜ ጨዋታዎችን ጨምሮ 31 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎችን እና በርካታ አሕጉራዊ ውድድሮችን ማስተናገዱ አይዘነጋም።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: