ለቀድሞ ድንቅ ተጫዋች የእውቅና መርሐግብር ሊካሄድ ነው

ለቀድሞ ለኢትዮጵያ ቡና እና ለብሔራዊ ቡድን ረዥም ዓመታት ተጫውቶ ላሳለፈው አሸናፊ በጋሻው የእውቅና እና የምስጋና ፕሮግራም ሊዘጋጅ ነው።

ከሰባዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ከእስከ ዘጠናዎቹ መግቢያ ድረስ ለአንድ ኢትዮጵያ ቡና ማልያ ለአስራ አራት ዓመታት በታማኝነት ያገለገለው እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከታዳጊ እስከ ዋና ቡድን ድረስ መጫወት ለቻለው ሁለገቡ ተጫዋች አሸናፊ በጋሻው የእውቅና መርሐግብር ሊዘጋጅ ነው።

በዋናነት በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማኀበር በአስተባባሪነት የተሳተፈበት እና የአሸናፊ በጋሻው ወዳጆች በተካፈሉበት በዚህ ፕሮግራም ላይ አሸናፊ በተጫዋችነት ዘመኑ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ጥሎት ያለፈውን በጎ አሻራ በማሰብ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፆኦ የእውቅና እና ምስጋና መርሐግብር ነሐሴ ወር መጀመርያ ላይ በአንድ በተመረጠ ሆቴል ውስጥ ለማዘጋጀት የተዋቀረው ኮሚቴ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

በዚህ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ የእግርኳስ ቤተሰቦች ይታደማሉ፣ አሸናፊ በተጫዋችነት ዘመኑ ያሳለፋቸው ነገሮች ይዳሰሳሉ፣ ለአሸናፊ በጋሻው ከፍተኛ የሆነ የእውቅና ሽልማት ይበረከትለታል ተብሎ ይጠበቃል።

የቀድሞ ባለ ታሪክ እግርኳስ ተጫዋቾቻችን የምንዘክርበት፣ እውቅና እና ምስጋና የምናቀርብበት ባህላችን ባልዳበረበት በዚህ ወቅት ለዚህ ስመጥር የቀድሞ ድንቅ ተጫዋች የታሰበውን ዓላማ ለሚያዘጋጁት አካለት ምስጋና የሚገባ ሲሆን በቀጣይ መሰል የሆኑ ተመሳሳይ ዝግጅቶች እንዲዘጋጁ የሚኖረው አርዓያነት የጎላ ነው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ