5ኛው የኢትዮጵያ ቡና ቤተሰባዊ ሩጫን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ተሰጥቷል

በ12/12/12 የሚደረገውን 5ኛው “የቡና ቤተሰባዊ ሩጫ”ን በተመለከተ ዛሬ ከሰዓት በክለቡ የፅህፈት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ መግለጫ ተሰጥቷል።

ይጀመራል ተብሎ ከነበረው ሰዓት 35 ደቂቃዎችን አርፍዶ የተጀመረውን ጋዜጣዊ መግለጫ የክለቡ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ፣ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኧኝ፣ የደጋፊዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን እና ደጋፊዎች ማኅበር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ክፍሌ ሰጥተዋል። በቅድሚያም የክለቡ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ እና የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ስለ ቤተሰባዊ ሩጫው መጠነኛ ገለፃ አድርገዋል።

“ምንም እንኳን ኮቪድ-19 መጥቶ መደበኛ ሥራችንን ቢያስተጓጉለንም የክለባችን ደጋፊዎች ዓመታዊው ሩጫው ዘንድሮ እንዲደረግ ከፍታኛ ፍላጎት ነበራቸው። ምክንያቱም ደጋፊዎቻችን የክለቡ 12ኛ ተጫዋች ስለሆኑ በዚህ ዓመት የተከሰተውን አጋጣሚ(12/12/12) ማለፍ አልፈለጉም። እንደዚህ አይነት የቀን መገጣጠሞችም ከብዙ ዓመት አንድ ጊዜ ስለሆነ የሚከሰተው እኛም ነገሩን አጤነው። ግን ቀኑን አስበው ሩጫው ይደረግ የሚል ጥያቄ ያነሱት ደጋፊዎቻችን ናቸው። እኛም ይህንን በማሰብ አጋጣሚው እንዳያልፈን የተለያዩ ውይይቶችን ስናደርግ ነበር። በዚህም በስራ አስኪያጃችን አቶ ገዛኸኝ የሚመራ ኮሚቴ አዋቅረን ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል። በዋናነት ደግሞ ኮሚቴው ደጋፊዎቻችን በቨርቹዋል የሚወዳደሩበትን ነገር ሲሰራ ቆይቷል።” በማለት የዘንድሮ ውድድር ቀጣይነት እንዲኖረው እና በኮቪድ ምክንያት እንዳይቋረጥ የነበረውን የደጋፊዎች ፍላጎት አስረድተዋል።

ከፕሬዝዳንቱ በመቀጠል የክለቡ ሥራ አስኪያጅ እና 5ኛውን የክለቡን የቤተሰብ ሩጫ ለማከናወን የተዋቀረውን ኮሚቴ ሲመራ የነበረው አቶ ገዛኸኝ መድረኩን በመረከብ በቦታው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛዎች ማብራሪያ ሰጥቷል።

“እንደሚታወቀው የኮቪድ ወረርሽኝ የዓለም ትላልቅ ውድድሮችን አሰርዟል። እኛም የዓለም አንዱ አካል ስለሆንን ውድድሩን እንደ ተለመደው ማድረግ አንችልም። ነገርግን ውድድሩ ቀን ተቆርጦለት ታስቦ እንዲውል ማድረግ እንችላለን በሚል ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል። የቡና ደጋፊ ደሞ ትክክለኛ 12ኛ ተጫዋች ስለሆነ ታሪካዊውን ቀን(12/12/12) ማሳለፍ አልፈለግንም። እንደሚታወቀው ውድድሮች ባለመኖራቸው ክለቡ በፋይናንስ ተጎድቷል። ስለዚህም ውድድሩ በተዘዋዋሪ ለክለቡ የገቢ ማሰባሰቢያም ነው። ይህ ቤተሰባዊ ሩጫ ከሌሎቹ የሚለየው በጋራ ሆነን የምንሮጥበት አደለም። ግን በሃገራችን የተደነገገውን አዋጅ ሳንጥስ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ለማድረግ አስበናል። በታሰበው እድቅድም መሰረት ታስቦ በሚውለው ይህ ታሪካዊ የክለቡ የሩጫ መርሃ ግብር ላይ 40 ሺ ደጋፊዎች እንዲሳተፉ እናደርጋለን። ሩጫው እንደ መደበኛ ሩጫ የሚሮጥበት ስላልሆነ ለ40 ሺ ደጋፊዎቻችን ሜዳልያ አናዘጋጅም። ግን በይዘቱ ለየት ያለ የምስክር ወረቀት(ሰርተፊኬት) ለደጋፊዎቻችን እንሰጣለን። በሰርተፊኬቱ ላይም የሚመዘገቡት የሩጫው ተሳታፊ ደጋፊዎቻችን ስማቸው በዳታ ቤዝ እንዲቀመጥ እናደርጋለን።”ብለዋል። አቶ ገዛኸኝ ጨምረውም ኮሚቴው ከተዋቀረበት ጊዜ ጀምሮ ሩጫው ታስቦ የሚውልበትን ቀን የመወሰን፣ የሚለበስ ማሊያ የማዘጋጀት፣ የሰርተፊኬት አዘገጃጀቶችን እና የአፍ ጭምብል የማዘጋጀት ሥራዎችን እንዳከናወነ ጠቁመዋል።

ከሁለቱ አካላት ማብራሪያ በመቀጠል በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው መልሶች እና ገለፃዎች ተደርገዋል።

ታስቦ በሚውለው ሩጫ ክለቡ ለማግኘት ስላሰበው ገቢ?

“በ5ኛው የቡና የቤተሰብ ሩጫ ላይ ክለቡ ከወጪ ቀሪ 4 ሚሊዮን ብር ለማግኘት አቅዶ ነው እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው።” አቶ ገዛኸኝ

የከዚህ በፊቶቹ የክለቡ ዓመታዊ ሩጫዎች ጠቀሜታ?

“ከዚህ በፊት ያከናወናቸው 4 ዓመታዊ የቤተሰብ ሩጫዎች በሁለት መንገድ ጠቅመውናል። አንደኛው ክለቡን በፋይናንስ በማጠናከር ረገድ ነው። በተለይ የመጀመሪያዎቹ ሩጫዎች የክለባችንን ካምፕ ለመገምቢያ ረድቶናል። ሌሎቹም ለተለያዩ የክለቡ የመሰረተ ልማት ወጪዎች በሚገባ አገልግለዋል። ሁለተኛው ጠቀሜታ ደግሞ በደጋፊዎቻችን መካከል ቤተሰባዊ ስሜትን በመፍጠር ረገድ ነው። ስለዚህ በየአመቱ የምናደርጋቸው ሩጫዎች በሚገባ ጠቅመውናል” አቶ ገዛኸኝ

ከክለቡ የገቢ ምንጮች ጋር በተያያዘ…?

“የኢትዮጵያ ቡና የገቢ ምንጮች በዋናነት አራት ናቸው። እነሱም ክለቡ ከቡና ሴክተሩ ፣ ከማሊያ ሽያጭ፣ ከስፓንሰር እና ከሜዳ ገቢ የሚገኙ ናቸው። በተለይ የሜዳ ገቢን በተመለከተ ዘንድሮ ጥሩ ጥቅሞችን እያገኘን ነበር። በተለይ የሜዳ ገቢያችንን እራሳችን መቆጣጠር ከጀመርን አንስቶ ጥሩ ገንዘብ እያገኘን ነበር። በሜዳችን ካደረግናቸው 8 ጨዋታዎች እንኳን 5.5 ሚሊዮን ብር በጠቅላላ አግኝተናል። እንደውም በትንሹ በየጨዋታው 7 እና 8 መቶ ሺ ብሮችን ስናገኝ ነበር። ነገር ግን ውድድሩ ተቋረጠ። መጀመሪያ ላይ እኛ እንደውም ከሜዳ ገቢ 12 ሚሊዮን ብር ለማግኘት አቅደን ነበር ስንቀሳቀስ የነበረው። ግን ውድደሩ ተቋረጠ። ከሜዳ ገቢ ውጪ ከቡና አቅራቢዎች እና ላኪዎች ከ12-14 ሚሊዮን ብር እናገኛለን። ከስፓንሰራችንም (ሀበሻ ቢራ) በዓመት ከ25-28 ሚሊዮን ብር እናገኛለን። ሀበሻ ቢራ እንደውም በተጨማሪነት በዓመት ውስጥ አራት ፕሮግራሞችን ካዘጋጀን 2 ሚሊዮን ብር(ለአንዱ ፕሮግራም 500 ሺ ብር) ሊሰጠን ተስማምተናል። ስፓንሰራችን ቀጣይም አብሮን እንዲሆን ውይይቶችን እያደረግን እንገኛለን። በጎ ነገሮችም ይኖራሉ ብለን እናስባለን። አሁን የሚደረገው ሩጫ ላይም ሀበሻ ቢራ አብሮን አለ። የወደፊቱን ግን እየተነጋገርን ነው። በቀጣይ የሚያሳስበን ገቢያችንን እንዴት ከስፖንሰር እናገኛለን የሚለው ነው። በተለይ ውድድር ይኑር አይኑር ሳይታወቅ አጋሮችን መፈለግ ከባድ ነው። ነገርግን በግሌ ከቡና ሴክተሩ የምናገኘው ገቢ የሚቀንስብን አይመስለኝም።” መቶ አለቃ ፍቃደ

የሩጫ ማሊያ ሽያጭን በተመለከተ…?

“የቡና ቤተሰቦች 12/12/12ን እንደ በዓል አይተን ነው የምናከብረው። የሚገርመው ሩጫው ታስቦ ይውላል ቢባልም የማሊያ ፍላጎቱ ግን በጣም ጨምሯል። እንደውም ከከዚህ ቀደሞቹ ዓመታዊ ሩጫዎች በበለጠ ደጋፊዎቻችን ማሊያውን ለመግዛት እየተሯሯጡ ነው። በጥቂት ቀናት ውስጥም ሽያጮችን እናጠናቅቃለን የሚል እምነት አለኝ። በዚህ አጋጣሚ ማሊያ ካለቀ በኋላ ፋላጎት እንደአዲስ እንዳይነሳ ደጋፊዎች ከአሁኑ ቢገዙ መልካም ነው።” አቶ ገዛኸኝ

ታስቦ በሚውለው የሩጫ ቀን የሚከናወኑ ሥራዎች?

“እንዳልነው ሁሉም ደጋፊዎች ተሰብስበው ባይሮጡም የተለያዩ ስራዎችን በታሪካዊቷ ቀን ለማከናወን አቅደናል። በዚህም በእለቱ ደጋፊዎቻችን የአረንጓዴ አሻራቸውን እንዲያኖሩ እናደርጋለን። በዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ቦታ እንዲፈቀድልን ንግግር እያደረግን ነው። በተጨማሪም ደጋፊዎቻችን በእለቱ የደም ልገሳ እንዲያደርጉ ከደም ባንክ ጋር ውይይት እያደረግን ነው። ከዚህ ውጪ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የምስኪኖቸን ቤት የማደስ እና አቅመ ደካሞቸን የማገዝ መርሃ ግብሮችን እናደርጋለን።” አቶ ገዛኸኝ

ቀጣይ የክለቡ ዓመታዊ ሩጫን በተመለከተ…?

“ክለቡ ከሚያከናውናቸው ፕሮግራሞች በተለየ ይህ ዓመታዊ ሩጫ ለእኛ በጣም ነው የተሳካልን። እቅዳችንም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሩጫውን ተሳታፊዎች ወደ 100 ሺ ከፍ ማድረግ ነው። ዘንድሮ ይህንን ማድረግ ባንችልም በቅርብ ጊዜ የተሳታፊዎቹን ቁጥር አሳድገን ለማከናወን እናስባለን።” መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ

12/12/12 የሚውልበት ቀን ማክሰኞ ቢሆንም ደጋፊዎች በያሉበት ክለባቸውን እያሰቡ የበዓሉ አንድ አካል እንዲሆኑ እና የታሰቡትን በጎ ስራዎች እንዲሰሩ ጥሪ ቀርቧል። ከጥያቄ እና መልስ በኋላም ለደጋፊዎቹ የተዘጋጁት የመሮጫ ማሊያ፣ ማስክ እና ሰርተፍኬት በቦታው ለተገኙ ጋዜጠኞች ይፋ ሆኗል።

*ከክለቡ የዝውውር ሁኔታ ጋር ተያይዞ በቦታው የተነሱ ማብራሪያዎችን ከቆይታ በኋላ ይዘን እንቀርባለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: