“ከመጀመርያዎቹ ሴት ዳኞች አንዷ” ሰርካለም ከበደ

ፈር ቀዳጅ በመሆን ለብዙዎች ሴት ኢትዮጵያውያን ዳኞች መነሻ ከሆኑት ሴት ዳኞች መካከል አንዷ የሆነችው ሰርካለም ከበደ የዛሬ የዳኞች ገፅ እንግዳችን ናት።

አስቀድማ የሴት እግርኳስ ትጫወት የነበረች በመሆኗ ወደ ዳኝነቱ እንድትገባ ምክንያት ሆኗታል። ከመምርያ 1 የጀመረው የዳኝነት ህይወቷ እስከ ኢንተርናሽናል ዳኝነት ድረስ መዝለቅ ችሏል። ከሴት ውድድር አንስቶ በሀገሪቷ ከፍተኛ ግምት እስከሚሰጠው የወንዶች ፕሪምየር ሊግ ድረስ እጅግ ወሳኝ የሚባሉ ጨዋታዎችን ከወንድ ዳኞች ጋር በመሆን በብቃት መስራት ችላለች። ዳኝነትን ካቆመችበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በጨዋታ ታዛቢነት በአጠቃላይ ሀገሯን ያለፉትን ሠላሳ ዓመታት አገልግላለች፤ እያገለገለችም ትገኛለች። ቀልድ አዋቂ ተጫዋች እና ለተተኪ ዳኞች ልምዷን በማካፈል የምትታወቀው ሰርካለም የመጀመርያዋ የሴት ፌዴራል ዳኛ፣ የመጀመርያዋ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ እና የመጀመርያዋ የወንዶች ፕሪምየር ሊግ የጨዋታ ታዛቢ በመሆን ከሌሎች ሁለት እንስቶች ጋር በመሆን ፈር ቀዳጅ ነች። በሙያዋ እግርኳሱን ከማገልገሏ በተጓዳኝ ወደ እግርኳስ አስተዳደር (አመራር ብቅ በማለት የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽንን በስራ አስፈፃሚነት እያገለገለች ትገኛለች። የእግርኳስ ፍቅር በቤተሰባቸው ያገኘችው ሰርካለም አባቷ የስፖርት ጋዜጠኛ የነበሩ ሲሆኑ ወንድሟም አሰልጣኝ መኮንን ከበደ የተለያዩ ክለቦችን በማሰልጠን በአሁኑ ሰዓት የአዲስ አበባ ከተማ ዋና አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።

ስለ ራሷ ብዙ መናገር የማትፈልገው እና ስለ እርሷ ሌላ ሰው ቢመሰክርላት የምትፈልገው ሰርካልም በዛሬው የዳኞች ገፅ አምዳችን ናት።

ትውልድ እና እድገትሽ የት ነው?

አዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ ነው። በተለይ ወጣቶች ስፖርት ማዕከል (ወወክማ) የተለያዩ ስፖርቶችን እሰራ ነበር። በተለይ የጠረጴዛ ኳስ እና እግርኳስ ከልጅነቴ ጀምሮ በጣም እየተጫወትኩ ነው ያደኩት።

የተለያዩ ስፖርቶችን ከልጅነትሽ ጀምሮ እየተጫወትሽ ማደግሽን ገልፀሽልኛል። በእነዚህ ስፖርቶች ምን ያህል ርቀት ተጉዘሻል ?

በእግርኳሱም ሆነ በጠረንቤዛ ኳስ ረጅም ርቀት አልተጓዝኩም። በእግርኳስ በእኛ ጊዜ እንዳሁኑ ብዙ ክለቦች አልነበሩም። በሊግ ደረጃም የሚደረግ ውድድርም አልነበረም። በግላቸው የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች በወቅቱ ስለነበሩ በእነሱ ቡድን ውስጥ ታቅፌ እሰለጥን ነበር። እኔ የነበርኩት ቡድን ኢንስትራክተር አበራ ሀብቴ የሚያሰለጥኑት ሲሆን አዲስ አበባ ስታዲየም የአዲስ አበባ ሻምፒዮን፣ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን ውድድሮች ላይ እንጋበዝና የመክፈቻ ጨዋታ እናደርግ ነበር። ያው ዘጠኝ ቁጥር አጥቂ ነበርኩ።

ታዲያ በልጅነትሽ እግርኳስ ተጫዋች መሆንሽ ወደ ዳኝነቱ እንድትገቢ ምክንያት ሆኖኛል ትያለሽ?

አጋጣሚ ሆኖ ከእግርኳሱ በተጓዳኝ በአራት ኪሎ ወወክማ ውስጥ የጠረንቤዛ ኳስ ስፖርት እጫወት ነበር። በዚህ ግቢ ውስጥ የማቃቸው ሰዎች የዳኝነት ኮርስ ይስዱ ስለነበረ እኔን ገፋፍተው እንድወስድ አደረጉኝ። የስፖርቱም ፍቅር ስላለኝ አባቴ አቶ ከበደም የስፖርት ጋዜጠኛ ስለነበር በዚህ ተነሳስቼ ወደ ዳኝነቱ ልገባ ችያለው።

በወቅቱ ከአንቺ በፊት ወይም ከአንቺ ጋር የዳኝነት ኮርስ የወሰዱ ሴት ሰልጣኞች ነበሩ ?

ከእኔ በፊት አንድ ቅድስት የምትባል ሴት ዳኛ ነበረች፤ ብዙም በዳኝነቱ መዝለቅ አልቻለችም። እርሷ የመጀመርያዋ ሴት ዳኛ ሳትሆን አትቀርም። ከእርሷ በመቀጠል ከአዲስ አበባ ፅጌ ሲሳይ፣ ሊዲያ ታፈሰ እና እኔ እንዲሁም ትርሀስ፣ ተስፋነሽ ከሌላ ክልል በአንድ ዘመን የሴት ዳኝነትን የጀመርነው። እኛ በሴት ዳኞች ታሪክ የመጀመርያዎቹ ነን።

የመጀመርያ የዳኝነት ኮርስ የወሰድሽው መቼ ነው?

በ1987 መምርያ ሁለት የሚባለውን የመጀመርያውን የዳኝነት ኮርስ መውሰድ የጀመርኩት። ሆኖም በስልጠናው ብዙም አልቀጠልኩም በተለያዩ ምክንያቶች ወጣ ገባ ነበር የምለው። አጋጣሚ በዛን ወቅት ቅድም እንደነገርኩህ ጠረጴዛ ቴኒስ እጫወት ስለነበረ የማደላው ለዚህ ስፖርት ስለነበረ በዳኝነት ስልጠናው ውጤታማ አልሆንኩም። ግን ትክክለኛውን ኮርሱን በሚገባ ወስጄ ውጤታማ በመሆን ያጠናቀኩት በ1989 ነው። በወቅቱም ከእኔ ጋር ፅጌ ሲሳይ አብራኝ ነበረች።

በዚህ የጀመረው የዳኝነት ህይወትሽ ወደ ፌደራል ዳኝነት እንዴት ማደግ ቻልሽ ?

ያው በአዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ውድድሮች በብዛት ይካሄዱ ስለነበረ ብዙ ጨዋታዎችን እየተዟዟርኩ የወንዶችን ጨዋታ በመሐል፣ በረዳት ዳኝነትም እየሰራው ልምድ እያገኘው መጥቻለው። ትልቁ ቁምነገር አዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ ብዛት ያላቸው ውድድሮች በመኖራቸው ለእኛ የዳኝነት ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጎልኝ ብዙም ሳልቆይ በ1993 ፌደራል ዳኛ መሆን ችያለው።

በሴት የዳኞች ታሪክ የመጀመርያዎቹ የፌደራል ዳኝነትን ማዕረግ አግኝተሻል። ይህ የተለየ ስሜት አለው? በፌደራል ዳኝነት ያጫወትሽውን የመጀመርያ ጨዋታ ታስታውሽዋለሽ ?

ፌደራል ዳኛ ሳልሆን በጣም ብዙ ጨዋታ አጫውቻለው። አቶ ጌታቸው አበበ የሚያዘጋጀው የዞን አራት ውድድር፣ የቀበሌዎች ውድድር በየትምህርት ቤቱ ነበር። አሁን ላይ ሆኜ ይሄነው መጀመርያ ያጫወትኩት ለማለት አሁን ማስታወስ ይከብደኛል። ፌደራል ዳኛ ሆኜ ግን በ1993 የሴቶች የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ድሬደዋ ከተማ ላይ ተዘጋጅቶ የነበረውን ውድድር በዋና ዳኝነት በማጫወት ነው የጀመርነው።

ዕድገትሽ ፈጣን ነው። ብዙ ሒደት የሚጠይቀውን የኢትዮጵያ ዳኝነት አንቺ በአጭር ዓመታት ውስጥ ከመምርያ አንድ የጀመረው የዳኝነት ህይወትሽ እስከ ፌደራል ዳኝነት ደርሰሻል። በፌደራል ዳኝነቱም ብዙ ሳትቆይ ወደ ኢንተርናሽናል ዳኝነት አምርተሻል ?

አዎ ያው አስቀድሞ በእግርኳን እጫወት ስለነበረ እና ሌሎች ስፖርቶችን አዘወትር የነበረ መሆኑ የዳኝነት ህይወቴን እንዳይከብድብኝ አድርጎልኛል። እግርኳስን ተጫውተህ ወደ ዳኝነቱ የምትገባ ከሆነ ነገሮች በተወሰነ መልኩ እንዲቀሉህ ያደርጋል። በፌደራል ዳኝነቱም የቆየሁት ለሦስት ዓመት ነው። በ1996 ለመጀመርያ ጊዜ ሴት ረዳት ኢንተርናሽናል ዳኛ በመሆን ባለ ታሪክ ሆኛለው። ከዚህ ውጭ ከእኔ ጋር በዋና ኢንተርናሽናል ዳኝነት ሊዲያ ታፈሰ እና ፅጌ ሲሳይ ከመጀመርያዎቹ ሲጠቀሱ በኃላ ሌሎች ወደ ኢንተርናሽናል ዳኝነት ክብርነት መቀላቀል ችለዋል።

በኢንተርናሽናል ዳኝነት ምን ያህል ዓመት ዘለቅሽ? በአፍሪካ ዋንጫ የሴቶች ውድድር የማጫወት ዕድል አግኝተሻል?

ከ1996–2004 ለስምንት ዓመት በኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝነት ማገልገል ችያለው። የተለያዩ እከሌ ከከሌ ብዬ ለመግለፅ አሁን ቢቸግረኝም ከሊዲያ፣ ከፅጌ፣ ትርሀስ፣ ተስፋነሽ ጋር በመሆን ብዙ የዓለም፣ የኦሊምፒክ ፣ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎችን በአፍሪካ እየተዟዟርኩ አጫውቻለው። የመጀመርያ የሄድኩበት ሀገር ናይጄሪያ ከ ላይቤሪያ ጋር ያደረግኩት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ሲሆን የመጨረሻዬ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ላይ ነበር። ሆኖም በነዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ ባልፍም የአፍሪካ የሴቶች ዋንጫን የማጫወት ዕድሉን አላገኘውም።

የኢትዮጵያ ሴቶች ውድድርን በጥሩ ብቃት መርተሻል። ይህ እንዳለ ሆኖ በዋና ዳኝነት ፅጌ ሲሳይ የመጀመርያዋ የወንዶች ፕሪምየር ሊግ ያጫወተች ሴት ዳኛ ናት፤ ሊዲያ ታፈሰም ብትከተልም። ሆኖም በሴት ረዳት ዳኝነት የመጀመርያዋ የወንዶች ፕሪምየር ሊግ ያጫወትሽ ሴት ነሽ። ይህ የተለየ ስሜት ፈጥሮብሻል ?

እንደው ፌዴሬሽን የተቀመጠ መረጃ ካለ ማየት ይቻላል። በዓመት በትንሹ የወንዶች ፕሪምየር ሊግን ከ18 በላይ ጨዋታ እናጫውት ነበር። በሳምንት ሁለቴ ሦስቴ ነበር የምንሰራው። በጣም ወሳኝ ወሳኝ የሚባሉ ጨዋታዎችን አጫውተናል። ከብሔራዊ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ፣ ዘጠናዎቹ ውስጥ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በንግድ ባንክ መካከል የተካሄደውን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ አጫውቻለው። ብቻ ብዙ ውድድሮች ላይ ተካፍያለው። የመጀመርያውን የወንዶች ፕሪምየር ሊግ ያጫወትኩት በ1994 አየር ኃይል ከ አርባ ምንጭ ነበር።

ዳኝነትን መቼ አቆመሽ ወደ ኮምሽነርነት እንዴት ገባሽ እርሱን አጫውቺኝ ?

በ2004 ዳኝነት እንዳቆምኩ በዚሁ ዓመት የኮሚሽነርነት ስልጠናዎችን ወስጄ በዛው ወደ ዚህ አገልግሎት ገብቻለው። እስከ 2011 ድረስ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግን፣ የክልል ክለቦች ሻምፒዮን እና የአዲስ አበባ ውድድሮችን በጨዋታ ታዛቢነት እያገለገልኩኝ ቆይቼ አሁን ከመጀመርያዎቹ ሦስት የሴት የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ኮምሽነሮች መካከል አንዷ ሆኜ እየሰራው እገኛለው። ከእኔ ጋር የመጀመርያ ከሆኑት መካከል ሳራ ከበደ፣ ተስፋነሽ ናቸው። የመጀመርያውን በወንዶች ፕሪሚየር ሊግ የጨዋታ ታዛቢ ሆኜ የሰራሁት በ2011 አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ከ ወልዋሎ አዲግራት ጋር ያደረጉት ጨዋተ ነበር። ከዚህ ጀምሮ ውድድሩ ኮሮና ቫይረስ እስከተሰረዘበት ጊዜ ድረስ በዚሁ ሙያ እያገለገልኩ ነበር።

ሴት መሆን በራሱ በጣም ከባድ ነው። የተፈጥሮ ህግ፣ ከተፈጥሮም ህግ ውጭ አጉል ልማድ ባለበት ሀገር እግርኳስን ተጫውተሽ ዳኛ ሆነሽ አሁን ደግሞ በጨዋታ ታዛቢነት በአጠቃላይ ለ30 ዓመታት በላይ ብዙ ፈተናዎችን አልፈሽ በጥንካሬ የማገልገልሽ ሚስጢር ምንድነው ?

ከልጅነቴ ጀምሮ እግርኳስን ስጫወት አልፌያለው። አባቴ የስፖርት ጋዜጠኛ የነበረ ስለሆነ ልጅ ሆኜ ስታዲየም ይዞኝ ይገባ ነበር። የቡና ፣ ጊዮርጊስን፣ የመድንን ጨዋታ እያየው በልጅነት አይምሮዬ እየደገፍኩ እመለከት ነበር። ይህ በውስጤ የእግርኳሱ ፍቅር እንዲገባ አድርጎታል። ወደ ተጫዋችነት ከመጣው በኃላ ብዙም በተጫዋችነቱ እንድቀጥል የሚያደርጉ ነገሮች አልነበሩም። እንደ አሁኑ የተመቻቹ ነገሮች ቢኒሩ ኖሮ እውነት ነው የምልህ ኳስ ተጫዋችነቱን እቀጥል ነበር። በእግርኳሱ ባይሳካልኝም የእግርኳስ ፍቅር ስለነበረኝ በተጫዋችነት ያላሳካሁትን እስቲ በዳኝነቱ በኩሉ ማሳካት አለብኝ ብዬ በማሰብ ከ1989 የዳኝነት ኮርስ ከወሰድኩበት ጊዜ አንስቶ ከመምርያ አንድ፣ ሁለት በኃላም ፌደራል ዳኛ፣ ከኢንተርናሽናል ዳኝነት አስከ ጨዋታ ታዛቢነት ረጅም ዓመት እያገለገልኩ ነው። በዚህ የረጅም ዓመት የስኬት ጉዞ ውስጥ ብዙ ፈተናዎችን፣ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮችን ምን ልበልህ በቃ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፌአለው። ለኔ የጥንካሬዬ ሚስጥር በፍላጎት እግርኳስን በጣም እወደው የነበረ መሆኑ ነው። ለአንድ ለምትሰራው ነገር ፍላጎቱ ካለህ ምንም ፈተናዎች ቢኖርም ጠንክረህ እንድትሰራው ያደርግሀል። ይሄ በዳኝነቱ ይሄን ያህል ዓመት በጥንካሬ እንድሰራ አድርጎኛል። እንዲሁም ስታዲየም ገብቼ ጨዋታዎችን ስመለከከት የማያቸው ዳኞች ለምሳሌ ኢንስትራክተር ይግዛው ብዙ፣ ኃይለመላክ ተሰማን እነ ኪነጥበብ ሲያጫውቱ እያየን ነው ያደግነው። እነርሱ ሲያጫውቱ ስታይ እነርሱ የደረሱበት ለመድረስ ከፍተኛ ተነሳሽነት ይኖርሀል። እነዚህ ነገሮች የበለጠ እዚህ ድረስ ዘልቄ እንድሰራ ውጤታማ አድርጎኛል።

በዳኝነት ዘመንሽ ያገኘሽው የኮከብነት ሽልማቶች አሉ ?

አዎ በአዲስ አበባ ደረጃ በ1993 ኮከብ ዳኛ ሆኜ ተሸልሜያለው። የሚገርምህ ነገር በወቅቱ ከእኔ ጋር ባዓምላክ ተሰማ በረዳት ዳኝነት ሲሸለም እኔ በዋና ዳኝነት ተሸልሚያለው። በ2003 በኢትዮጵያ ደግሞ በወንዶች ፕሪምየር ሊግ ምስጉን ረዳት ዳኛ በመሆን ተሸልሜያለው። ከዚህ ውጭ በተለያዮ ጊዜያት በብዙ መድረኮች በዳኝነት ስላበረከትኩት አስተዋፆኦ የዕውቅና የምስጋና ሰርተፍኬቶች አግኝቻለው።

በዳኝነት ዘመንሽ አሳዛኝም ሆነ አስቂኝ ገጠመኝ አጋጥሞሻል ?

በዚህ ረገድ አስቂም አሳዛኝም ብዙም ገጠመኝ የለኝም ሆኖም አስተማሪ ከሆነ የተወሰነ ልናገር። ከሊዲያ ጋር ቡና ከፊንጫ ስናጫውት የጎሉ መረብ ተቀዶ የነበር። በእኔ ባለሁበት አቅጣጫ ኳሱ ሲመታ በጭበኩል በተቀደደው በኩል ኳሱ መረብ ውስጥ ይገባል። ሾልኮ የገባ ስላየሁት መቶ ፕርሰንት እርግጠኛ ነበርኩ ። ካለሁበት ቦታ ሳልንቀሳቀስ ምንም አይነት ምልክት አላሳየሁም የመልስ ምት ጎልም ነው አላልኩ ቆሜአለው። ሊዲያም ጠጋ ስትል የተቀደደው መረብ መሆኑን አይታ ሁላችንም ባንድ ላይ የመልስ ምት ብለን ያስጀመርንበት አጋጣሚ አረሳውም። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለ ነገር በመረጋጋት ካልሆነ ፈጥኜ ጎል ብለ።ኖሮ ብናፀድቅ እኔም እርሷንም፣ ቡድኖቹም ይጎዳሉ። እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከ ድሬደዋ ከተማ ሲጫወቱ እንደዚሁ እኔና ሊዲያ ነበርን። ወሰኑ ማዕዜ(ቀስቴ) የቡና ተጫዋች ነበር የዛን ጊዜ በኔ በኩሉ (በቡና የጥላፎቅ አቅጣጫ) ኳስ በግንባሩ የሚመታ አስመስሎ በእጁ በመንካቱ ምልክት አሳይቼ ፍፁም ቅጣት ምት እንዲሰጥ አደረኩኝ። የሚገርምህ ነገር በቡና አቅጣጫ ነው የነበርኩት ቡና ላይ ፔናልቲ አሰጥቼ ቀስቴ ሊናገረኝ ሲመጣ የቡና ደጋፊዎች ትክክል ናት ብለው እርሱን ተቃውመው ለኔ አጨብጭበው ድጋፍ የሰጡበት ሁኔታ የማረሳው ነው። ሌላው ቦትሱዋና እኔ ትራሀስ፣ ፅጌ እና ሊዲያሄደን ጨዋታውን አጫውተን ስንወጣ በኋላ የጨዋታው ኮሚሽነር እና ባለቤቷ የፊፋ አባል ነበር። ከተቀመጠበት ወርዶ በጨዋታው የነበረኝን የዳኝነት ብቃት አድንቆ በርቺ ወደፊት ትልቅ ዳኛ ትሆኛለሽ በማለት ሲያበረታታኝ ሊዲያ አይታ ግንባሬን የሳመችበት መንገድ ሁሌም አስታውሰዋለው። የሚገርምህ በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገር ለጨዋታ ስንወጣ በጣም ተናበን፣ ተያይተን በፍቅር በህብረት ነበር የምንሰራው። ከምንም በላይ ሀገራችን የወንዶች ጨዋታዎችን ብዙ ጊዜ ስለምንሰራ ወጥተን የሴት ጨዋታ ስናጫውት አይከብደንም ይቀለን ነበር።

ካለሽ የረጅም ዓመት ልምድ ለዚህ ዘመን በተለይ ለሴት ዳኞች የምታስተላልፊው መልዕክት

ያው የመጀመርያዎቹ በመሆኔ በጣም ደስታ ይሰማኛል።የዛኑ ያህል የመጀመርያ በመሆናችን ብዙ ነገር ተፈትነናል፣ ብዙ መከራዎችን አልፈናል። አሁን እንዳለው አይደለም። እኛ ገና ከመጀመርያ ኮርስ ጀምሮ የዳኝነትንህ፣ የጨዋታ ብዛት በጣም እናገኝ ነበር። በተለይ የአዲስ አበባ ዳኛ ስትሆን ጥሩ ነቱ ብዙ ጨዋታዎችን ታገኛለህ ይህ ደግሞ ከጨዋታ ጨዋታ እራስህን እያሻሻልክ ልምድ እያገኘህ ትሄዳለህ። አሁን ላይ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ዳኞች ይህን እድል ላያገኙ ይችላሉ። ሆኖም ኮሚሽነር ሆኜ ዳኞችን ሳገኝ እንደ እናት፣ ታላቅ እህት ሆኜ ነው የምቆጣው። እንዲስተካከሉ፣ ህግ በደንብ እንዲያውቁ እኔ የድስኩበት ደረጃ እንዲደርሱ ነው የምፈልገው። እኛ ሀገር ትንሽ በሙያተኛው በኩል መከባበር የለም። እኔ እውነት ነው የምልህ በጣም ነው የማከብራት በሴትነቷ ብዙ ፈተናዋችን አልፋ የዓለም ዋንጫ መድረሷ የሚያስደንቅ ነው። ዳኝነት በጣም አድካሚ ነው ሰባት ቀን እንቅልፍ አጥተህ የአካል ብቃት ፈተና ለማለፍ ብዙ ዝግጅት የሚጠይቅ ነው። እውነት ነው የምልህ እኔ እንኳን አሁን ዳኝነትን አቁሜ ድካሙ እና እንቅልፉ አልወጣልኝም። ልፋት አለው አይምሮ ይጨነቃል። ስህተት ላለመስራት ተሳቀህ ነው የምትሰራው ያሁሉ ህዝብ አንተላይ ነው አይኑን የሚጥለው ይህን በብቃት ለመወጣት ቆራጥነት ያስፈልጋል። ውስጥህ ንፁሁ፣ ታማኝ፣ እከሌን አቀዋለው እከሌን አላቀው ሳይል መስራት ያስፈልጋል። እኔ የወንድሜ የመኮንን ቡድንን ሁለቴ የዋንጫ ጨዋታ አጫውቸዋለው። እኔ ወንድሜ መሆኑን አላቀውም ስራዬ ላይ ነው ትኩረት የማደርገው። እንዲያውም አንድ ወሳኝ ጨዋታ የመኮንን ክለብ ሀዋሳ እንዳጫውት ተመድቤ ለዳኞች ኮሚቴ አላጫውትም የወንድሜ ቡድን ነው ስላቸው እኛ እናምንሻለን ነው ያሉኝ ኮሚቴዎቹ። ስለዚህ ህሊናህን አፅተህ ዳኝነትን ልትሰራ ይገባል። አሁን ላሉት ዳኞች እራሳቸውን ማሳደግ ይገባቸዋል። የአካል ብቃት ፈተናው ጨምሯል። ውድድሩም ጠንከር ያለ ፉክክር እየታየበት ነው። ዳኞች በዚህ ዘመን በዝተዋል ግን ጥራት ላይ ብዙ መስራት አለበት። በሀገራችን ብዙ ጥሩ ጥሩ ኢንስትራክተሮች አሉ የእነርሱን ትምህርት ምክር መቀበል፣ መስማት ያስፈልጋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: