የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ቆይታ ከአንተነህ ተስፋዬ ጋር…

በዛሬው የ”ዘመናችን ከዋክብት ገፅ” ላይ የሰበታ ከተማው ቀልጣፋ ተከላካይ አንተነህ ተስፋዬን እንግዳ አድርገነዋል።
በአርባምንጭ ከተማ ተወልዶ ያደገው “ልበ ሙሉው” የመሐል ተከላካይ ወደ እግርኳስ የገባበት መንገድ ለየት ያለ ስለመሆኑ ይነገራል። በርካታ ተጫዋቾች በፕሮጀክት እና አካዳሚ ጎልብተው ወደ ታላቅነት የሚንደረደሩ ሲሆን አንተነህ ግን ወደ ትልቅነት የመጣበት መንገድ ከዚህ የተለየ ነው። በሰፈር ውስጥ በሚደረጉ ግጥሚያዎች ላይ እየተሳተፈ ልጅነቱን ያሳለፈው ይህ ተከላካይ 2002 ላይ ነበር ሳያስበው እና ሳይዘጋጅ በአርባምንጭ ክለብ አመራሮች እና አሰልጣኞች እይታ ውስጥ ገብቶ የክለብን ህይወት ጀመረው።
አርባምንጭ ከተማ በብሄራዊ ሊግ(በአሁን አጠራሩ ከፍተኛ ሊግ) እየተወዳደረ ክለቡን የተቀላቀለው ይህ ተጫዋች ከክለቡ ጋር ለ2 ዓመታት በሁለተኛው የሃገሪቱ የሊግ እርከን ካሳለፈ በኋላ ክለቡን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማሳለፍ ችሏል። በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም ለአርባምንጭ ከተማ ለ4 ዓመታት ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ 2008 ዓ/ም ላይ ወደ ሌላኛው የደቡብ ክለብ(ሲዳማ ቡና) ተዘዋወረ። በሲዳማ ቡናም ለ2 ዓመታት የአቅሙን ከሰጠ በኋላ ወደ ምስራቂቱ የሃገሪቱ ክፍል(ድሬዳዋ) በማቅናት ለ2 ዓመታት ተጫውቷል። በዘንድሮ የውድድር ዘመን ደግሞ ፊርማውን ለውበቱ አባተ ሰበታ ከተማ በማኖር ሲጫወት ሰንብቷል።

ከ31 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ባለፈበት ስብስብ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የብሄራዊ ቡድን ጥሪ የቀረበለት አንተነህ በጊዜው የመጫወት እድል ሳያገኝ ቀርቷል። ተጫዋቹ ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በመቀጠል ብሄራዊ ቡድኑን በመሩት ፖርቹጋላዊ አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶም ጥሪ ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም የመጫወትን እድል ግን በድጋሜ አላገኘም ነበር። 2008 ዓ/ም ላይ ወደ ብሄራዊ ቡድን የመጡት አሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ ግን ለወጣቱ ተጫዋች የመሰለፍ እድል ሰጥተውት የብሄራዊ ቡድን ህይወቱን በጨዋታ “ሀ” ብሎ ጀምሯል። ከሩዋንዳ ጋር በተደረገ የወዳጅነት ጨዋታ ሃገሩን መወከል የጀመረው ተጫዋቹም እስካሁን በተከታታይ ብሄራዊ ቡድኑን ባሰለጠኑ አሰልጣኞች እየተመረጠ ሃገሩን እያገለገለ ይገኛል።

ሶከር ኢትዮጵያም ከዚህ ቀልጣፋ እና ደፋር የብሔራዊ ቡድን የኋላ ደጀን ጋር አዝናኝ ቆይታ አድርጋለች።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በኮቪድ-19 ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ አንተነህ ጊዜውን በምን እያሳለፈ ነው?

ሊጉ በኮሮና ምክንያት ከተቋረጠ ጀምሮ ብዙ ጊዜዬን ከቤተሰቤ ጋር ነው እያሳለፍኩ ያለሁት። በዋናነት ልምምዶችን በግሌ በመስራት ቀኔን እጀምራለሁ። ከልምምድም ስመለስም ከልጆቼ ጋር እየተጫወትን፣ ፊልም እያየን እና የቤት ውስጥ ስራዎችን እየሰራን ቀኑን እንገፋለን። ባለሙያ ባልሆንም የምችላቸውን የቤት ውስጥ ስራዎች እየሰራሁ ባለቤቴን አግዛታለሁ።

የእግር ኳስ አርዓያህ ማነው?

እውነት ለመናገር ልጅ እያለሁ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን የማየት እድሉን አላገኘሁም። በሊግ ደረጃም በአካባቢዬ የሚሳተፈው ብቸኛ ክለብ አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ነበር። ግን ከጨርቃጨርቅ በኋላ እኔ ታዳጊ እያለሁ በሊጉ የሚሳተፍ ክለብ አልነበረም። ከዚህ የተነሳ ብዙ ተጫዋቾችን የማየት እድሉን አላገኘሁም። ግን በአንድ ከተማ እና ሰፈር የተወለድነው የቅርብ ጓደኛዬ ቢያድግልኝ ኤሊያስ ወደ እግርኳስ እንድገባ እንደ ወንድም ይገፋፋኝ ነበር። እሱ ቀደም ብሎም ስለሆነ ወደ እግርኳሱ የገባው ፈለጉን እንድከተል ይመክረኝ ነበር። ከዚህ ውጪ ደጉ ደበበን እንደ አርኣያ እመለከተው ነበር። እሱ የደረሰበት ደረጃ መድረስ እፈልግ ነበር።

በግልህ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍክበት ዓመት?

በግሌ ጥሩ ጊዜ አሳለፍኩ የምለው አርባምንጭ እና ሲዳማ እያለሁ ነው። በተለይ 2003 ዓ/ም ላይ አርባምንጭን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስናሳልፍ በጣም ምርጥ ነበርኩ። ከዚህ በተጨማሪ 2009 ዓ/ም ላይ ሲዳማ ቡና የዋንጫ ተፎካካሪ የነበረበት ዓመት ላይ ጥሩ ነበርኩ።

አንተነህ እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን ምን ይሆን ነበር?

እግርኳስ ተጫዋች ባልሆን የመኪና ሹፌር የምሆን ይመስለኛል። ሹፍርና የአባቴ ሙያ ነበር። ከዚህ መነሻነት እሱን ተከትዬ ሹፌር የምሆን ይመስለኛል።

አብሬው ተጣምሬ መጫወት እፈልጋለሁ የምትለው ተጫዋች ማነው?

ከቢያድግልኝ ኤሊያስ ጋር ተጣምሬ መጫወት እፈልጋለሁ። ከእርሱ በይበልጥ ደግሞ በዚህ ሰዓት በብሄራዊ ቡድን የሚያጣምረኝን አስቻለው ታመነ በቋሚነት በክለብ ደረጃ ከዓመት እስከ ዓመት ተጣምሬ ብጫወት ደስ ይለኛል።

በተቃራኒ ስትገጥመው የሚከብድክ ተጫዋች ይኖር ይሆን?

በፍፁም የለም። እስካሁን በተጫወትኩባቸው ጨዋታዎች ይሄን ያህል የከበደኝ ተጫዋች የለም።

በዚህ ሰዓት ከሚገኙ የሃገራችን ተጫዋቾች ያንተ ምርጥ ማነው?

በዚህ ሰዓት ካሉ ተጨዋቾች መካከል ሽመልስ በቀለ ለእኔ ምርጡ ነው።

ከአሰልጣኞችስ?

ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ በዚህ ሰዓት ካሉ የሃገራችን አሰልጣኞች ለእኔ ምርጡ ነው። አብርሃም በአሁኑ ሰዓት ሃገራችን ላይ ከሚገኙ አሰልጣኞች ለየት ያለ ነው። በጣም ነው የማደንቀው።

በእግርኳስ በጣም የተደሰትክበት አጋጣሚ መቼ ነው?

በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ይሄን ያህል ለደስታ የሚያበቃ ክብር አላገኘሁም። ግን በደስታ ደረጃ የተወለድኩበትን እና ያደኩበትን ከተማ አርባምንጭ ወደ ፕሪምየር ሊግ ስናሳድግ (2003) በጣም ተደስቼ ነበር። ቀድሜም እንደገለፅኩት ሲዳማ ቡና የዋንጫ ተፎካካሪ የነበረበት ዓመት(2009) ላይ በአንፃራዊነት ተደስቼ ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ።

የተከፋህበትስ ጊዜ ይኖር ይሆን?

አዎ! በጣም የተናደድኩበት ጨዋታ አለ። እሱም ዘንድሮ ሰበታ እየተጫወትኩ የተፈጠረ ነው። በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ባህር ዳርን ገጥመን 3ለ2 የተሸነፍንበት ጨዋታ በጣም አበሳጭቶኛል። እኔም በጨዋታው ጥሩ አልነበርኩም።

በእግርኳሱ ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች የቅርብ ጓደኛክ ማነው?

ቢያድግልኝ ኤልያስ። ቀድሜ እንደገለፅኩልክ ወደ ኳስ እንድገባም ቢያድግልኝ ገፋፍቶኛል። አንድ አካባቢም ስለነበርን በጣም እንቀራረባለን። እንደውም ወንድሜ በለው።

አንተነህ ምግብ ላይ እንዴት ነው?

የምጠላው ምግብ የለም። ስፖርተኛ ስለሆንኩ ፓስታ እና ሩዝ አዘወትራለሁ። ግን እንጀራ ብዙ አልመገብም። በጣም የምወደው ምግብ ደግሞ ፎሶሰ ይባላል። ይህንን ምግብ ብዙ ሰው ላያቀው ይችላል። ግን አርባምንጭ ውስጥ በጣም ይወደዳል። እኔም ይህንን በበቆሎ የሚሰራ ምግብ መብላት ያስደስተኛል።

የግል ህይወትክየህ ምን ይመስላል?

ባለትዳር ነኝ። ሁለት ልጆችንም አፍርቻለሁ። አሁን ከባለቤቴ እና ከሁለት ልጆቼ ጋር ነው እየኖርኩ ያለሁት።

ሜዳ ውስጥ ኮስታራ እና ተናጋሪ ነህ። ከሜዳ ውጪ ያለህስ ባህሪህ ምን ይመስላል?

ከባህሪ ጋር በተያያዘ የተለየ ነገር የለኝም። ግን ሜዳ ላይ የሚታየው አንተነህ ከሜዳ ውጪ የለም። መሸነፍ ስለማሎድ ሜዳ ላይ እጮሃለው። አንዳንዴም እነጫነጫለሁ። ከቡድን አጋሮቼ ጋር ሁሉ ሳይቀር እጯጯሃለው። ግን ከሜዳ ውጪ ይህ ባህሪ ይጠፋል። ዝምተኛ ነኝ። ብዙ አላወራም።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ