የሴቶች ገፅ | ቆይታ ከኮከቧ ሴናፍ ዋቁማ ጋር…

በዛሬው የሴቶች ገፅ አምዳችን የአዳማ ከተማ እና የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ኮከብ ሴናፍ ዋቁማን እንግዳ አድርገናታል።

ነቀምት ላይ ተወልዳ ያደገችው ሴናፍ ከልጅነቷ ጀምሮ የኳስ ፍቅር እንዳደረባት ትናገራለች። በተለይ ተወልዳ ባደገችበት እና እስከ 8 ክፍል ድረስ በተማረችበት ነቀምት ከተማ ከወንዶች ጋር ኳስን አዘውትራ ትጫወት ነበር። ከዛም የ2ኛ ደረጃ ትምህርቷን እና የእግርኳስ ፍቅሯን ለመቀጠል ወደ አሰላ አመራች። እስከ 12ኛ ክፍል ድረስም በአሰላ ከተማ በመማር የቀለም ትምህርቷን አሳደገች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በዚሁ ከተማ(አሰላ) እየቀጠለች የተለያዩ የትምህርት ቤት የእግርኳስ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ ስታደርግ የነበረችው ተጫዋቿም በጥሩነሽ ዲባባ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ መልላዮች እይታ ውስጥ ገብታ ራሷን በእግርኳሱ ለማብቃት ወደ ተሻለ ደረጃ ተሸጋገረች።

ይህቺ ፈጣን እና ባለተሰጥኦ ወጣት በጥሩነሽ ዲባባ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ 4 ዓመታትን አሳላፋ 2009 ዓ/ም ላይ ደግሞ ወደ አዳማ ከተማ ጉዞዋን አደረገች። ተጫዋቿም የተሰረዘውን የዘንድሮ የውድድር ዘመንን ጨምሮ በአዳማ ቤት 4 የውድድር ዓመታትን አሳልፋለች። ሴናፍ አሁን ባለችበት አዳማ ከተማም የ2011 ዓ/ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግን ማሸነፍ ችላለች። ተጫዋቿ በዚሁ ዓመትም የሊጉ ምርጥ ተጫዋችነት በመመረጥ እና 21 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የኮከብነትን ህይወት “ሀ” ብላ ጀመረች።

የጥሩነሽ ዲባባ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ውስጥ እያለች ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንን እንድታገለግል በአሰልጣኝ አስራት አማካኝነት መመረጥ የቻለችው ይህቺ ኮከብ ከዛም በኋላ በአሰልጣኝ ቴዎድሮስ ጥሪ ከ20 ዓመት በታች እንዲሁም በአሰልጣኝ ሠላም እና ብርሃኑ አማካኝነት ደግሞ ወደ ዋናው የሴቶች ብሄራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) እንድትካተት ተደርጎ ሃገሯን አገልግላለች።

ሶከር ኢትዮጵያ ከዚህች የዘመናችን ኮከብ ተጫዋች ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ሊጉ ከተቋረጠ በኋላ ሴናፍ ጊዜዋን እንዴት እያሳለፈች ነው?

ሊጉ በኮቪድ-19 ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ አብዛኛውን ጊዜዬን ቤት ውስጥ ነው የማሳልፈው። በዋናነት ደግሞ ልምምዶችን የምሰራበትን መርሃ ግብር በግሌ አውጥቼ እየሰራሁ እገኛለው። ልምምድ ከሰራሁ በኋላ ደግሞ እራሴን ዘና የሚያደረጉ ፊልሞች እና የእግርኳስ ጨዋታዎችን በመመልከት ጊዜዬን አሳልፋለው። ከምንም በላይ ግን መጽሐፍትን አነባለው።

የእግርኳስ አርዓያሽ ማናት?

በልጅነቴ ብዙ ተጫዋቾችን በአርያነት የመመልከት እድሉን አላገኘሁም። አካዳሚ ከገባው በኋላ ግን በሃገራችን የሚገኙ ጎበዝ ተጫዋቾችን የማየት እድሉን አገኘሁ። በዚህም ብርቱካን ገብረክርስቶስ ለእኔ ምርጥ ተጫዋቼ ነበረች።

በግልሽ ምርጥ ጊዜ ያሳለፍሽበት ዓመት መቼ ነው?

በክለብ ደረጃ የረዘመ ህይወት የለኝም። ግን በዚህ አጭር ጊዜም ቢሆን በ2011 ዓ/ም አዳማ ላይ የነበረኝ ነገር ጥሩ ነበር። በዚህ ዓመት (2011) ከክለቤ ጋር ዋንጫ ያነሳሁበት እና በግሌ ኮከብ ተብዬ የተመረጥኩበት ዓመት ነበር። በተጨማሪም በውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪም ነበርኩ። ስለዚህ በ2011 እንደ ቡድንም ሆነ እንደ ተጫዋች መልካም ስኬት ያገኘሁበት ዓመት ነበር።

ሴናፍ ተጫዋች ባትሆን ምን ትሆን ነበር?
ይህ ከባድ ጥያቄ ነው። ግን ተጫዋች ባልሆን በቀለም ትምህርቴ የምገፋ ይመስለኛል። ቤት ውስጥም የሚገኙ ቤተሰቦቼ በቀለም ትምህርት የተሻለ ደረጃ ስለደረሱ እነሱን ተከትዬ ተመርቄ ሥራ የምሰራ ይመስለኛል።

አብሬያት ብጣመራት የምትያት የሃገራችን ተጫዋች አለች?

በዚህ ሰዓት ከሚገኙ ማንኛቸውም የሃገራችን አጥቂዎች ጋር ተጣምሬ ብጫወት ችግር የለብኝም። አብዛኞቹ ተጫዋቾች ጀግና ስለሆኑ ከሁሉም ጋር ብጣመር ጥሩ ነገር የምናመጣ ይመስለኛል።

በተቃራኒ ስትገጥሚው የሚከብድሽ ተከላካይ ይኖር ይሆን?

እውነት ለመናገር የሚከብደኝ ተጫዋች የለም። ግን በአንፃራዊነት የሃዋሳ ተከላካዮች ትንሽ ይፈትናሉ። እነሱም በተናጥል ሳይሆን እንደ ቡድን ያላቸው ቅንጅት ነው ትንሽ የሚፈትነው። ከዚህ ውጪ የሚከብደኝ የለም።

በእግርኳስ የተደሰትሽበት ጊዜ መቼ ነው?

አዳማ በ2011 ዓ/ም ዋንጫ ሲበላ በጣም ተደስቼ ነበር። ዓመቱም ቀድሜ እንደገለፅኩልክ በጣም ጥሩ ነበር። ግን የመጨረሻዋ ቀን ለእኔ በጣም ትለይ ነበር።

የተከፋሽበትስ ጊዜ?

የተከፋሁበት ጊዜ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የተፈጠረ ነው። እሱም ቡድናችን ባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ላይ የካሜሩን አቻውን አስተናግዶ ነጥብ የተጋራበት ጨዋታ በጣም አስከፍቶኝ ነበር።

በእግርኳስ የቅርብ ጓደኛሽ ማነው?

አሁን ላይ በእግርኳሱ ውስጥ ያለ የቅርብ ጓደኛ የለኝም። ይሄን ያህልም ሰው ስለማልቀርብ ኳስ ውስጥ ያለ የልብ ጓደኛ የለኝም። ወደፊት ግን ይኖረኛል ብዬ አስባለሁ።

ሴናፍ ምን የተለየ ባህሪ አላት?

ዝምተኛ መሆኔ ምናልባት የተለየ ከሆነ ይህ የተለየ ባህሪዬ ነው። ከሰዎች ጋር ቶሎ መግባባት አልችልም። አደለም ከማላቀው ጋር ከማቀው ሰው ጋርም ብዙም የማውራት ችሎታ የለኝም።

የግል ህይወትሽ ምን ይመስላል?

ለትዳር አልደረስኩም (እየሳቀች)። ከቤተሰብ ጋር ነው እየኖርኩ የምገኘው።

እግርኳስ ከመጫወት ውጪ የምታደርጊው የተለየ ነገር?

ይሄን ያህል የምሰራው የተለየ ነገር የለም። ብዙ ጊዜ የዕምነት ስፍራ እየሄድኩ ነው ጊዜዬን የማሳልፈው። በዚህም ደግሞ ደስተኛ ነኝ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ