“ትልቅ አሰልጣኝ የመሆን ህልም አለኝ” ሀፍቶም ኪሮስ

ባለፈው ሳምንት በጀመርነው የጀማሪ አሰልጣኞች ዓምዳችን ከፋሲል ከነማ የአሰልጣኞች ቡድን አባል ሙሉቀን አቡሀይ ጋር ቆይታ ማድረጋችን ይታወሳል። ለዛሬ ደግሞ ላለፉት ዓመታት በወልዋሎ የአሰልጣኞች ቡድን ቆይታ የነበረውና በዋና አሰልጣኝነት ዘንድሮ አዲስ ፈተና ከጀመረው ሀፍቶም ኪሮስ ጋር ቆይታ አድርገናል። ሀፍቶም ስለ አሰልጣኝነት ቆይታው፣ ስለ እቅዱ እና ስለፈተናዎቹ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ከአሰልጣኝነት ሕይወት በፊት የነበረው ቆይታ

እግር ኳስን በትልቅ ደረጃ አልተጫወትኩም። በሰፈር እና ከዛ አለፍ ብለው ባሉት ደረጃዎች ነው የተጫወትኩት። ዩንቨርስቲ ገብቼ በስፖርት ሳይንስ ተመርቄ ከወጣሁ በኃላ ነው ይበልጥ ወደ አሰልጣኝነት የተጠጋሁት።

ወደ አሰልጣኝነት የገባበት አጋጣሚ

ከዩኒቨርሲቲ ተመርቄ ከወጣሁ በኃላ ከሌሎች ጓደኞቼ በእግር ኳሱ ላይ ለውጥ ለማምጣት እንቅስቃሴ ጀምረን ነበር። በሴቶች እና በወንዶች በሁለቱም ጾታ ወደ ማሰልጠኑ ገባን። 2003 በተዘጋጀው የዓዲግራት ውድድርም በሴቶች ዋንጫ ወሰድን በወንዶች ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ። ከዚ ነው የሚጀምረው የአሰልጣኝነት ሕይወቴ። ከዛ በኃላ ደግሞ በኮማንደር ኪዳነ የሚሰለጥን ከተማችንን የወከለ የሴቶች ቡድን ነበር፤ ከነሱ ጋር ተቀላቅዬ ዋና አሰልጣኙን ማገዝ ጀመርኩ ማለት ነው። ከዛ በኃላ ኮማንደር ኪዳነ ወደ ወንዶች ቡድን ሲሸጋገር እኔ የሴቶች ቡድን ማሰልጠን ጀመርኩ። በ2004 ደግሞ ከቡድኑ ጋር ዋንጫ አነሳሁ፤ 2006 ደግሞ ወደ ወልዋሎ ዋናው ቡድን አደግኩ።

ወደ ወልዋሎ ዋናው ቡድን ያደገበት ሁኔታ

መጀመርያ በከተማችን እግር ኳስ እንቅስቃሴ ጥሩ የሚባል ሚና ነበረኝ። ከዛ በኃላ ደግሞ በሴቶች እግር ኳስ በክልል ደረጃ የዋንጫ ባለቤትም ነበርኩ። በ2005 ደግሞ እኔና ኮማንደር ኪዳነ ወልዋሎ ሁለተኛ ቡድን ይዘን ጥሩ ሥራዎች ሰርተናል። ኮማንደር ወደ ዋናው ቡድን በሄደበት ጊዜም ሁለተኛው ቡድን ይዤ ጥሩ ቆይታ ነበረኝ። ከዛ ውጭም በክልል ደረጃ የአሰልጣኝ ሕይወት አረፋይነ ምክትል ሆኜ ሰርቻለው ከ17 ዕድሜ በታች ቡድን ይዤም ጥሩ ውጤት አምጥቻለው። እነዚህ የጠቀስኳቸው ወደ ዋናው ቡድን እንዳድግ መንደርደርያ ሆነውኛል።

የዋናው ቡድን ቆይታ እና ፈተናዎቹ

በወልዋሎ ውስጥ ለመስራት የሚያበረታቱ ብዙ ነገሮች አሉ፤ በአንፃሩ ደግሞ ብዙ ፈተናዎች ነበሩ። እምብዛም የስራ ድርሻ ሳይኖርህ እና አቅምህን ሳታሳይ ከኃላፊነትህ እንድትነሳ የሚቀሰቅሱ ብዙ ናቸው። በየዓመቱ ተመሳሳይ ችግሮች ነበሩ። ከሁሉም አሰልጣኞች አሪፍ የትምህርት ግዜ ነበረኝ። በትላልቅ አሰልጣኞች ስር ነው የሰራሁት። በሚልዮን፣ እንድርያስ፣ ብርሀኔ ገ/እግዚአብሔር፣ ጌታቸው ዳዊት፣ ፀጋዬ ኪ/ማርያም እና ዮሐንስ ሳህሌ ስር ነው የሰራሁት። ከሁሉም ጋር አሪፍ ቆይታ ነበረኝ።

ከወልዋሎ የተለያየበት ምክንያት

የሚና መቀያየር ስለመጣ ነው ፤ ሌላ ምንም ምክንያት የለውም። ላለፉት ዓመታት በምክትል አሰልጣኝነት ስስራ ነበር በዚ ዓመት ግን ሌላ የአሰልጣኞች ቡድን መገንባት ስለፈለጉ ወደ ቡድን መሪነት እንደምያዘዋውሩኝ ነገሩኝ እኔም ፍቃደኛ ስላልነበርኩ ከቡድኑ ጋር ተለያየው። ከሁሉም ጋር በሰላም ነው የተለያየሁት። ምክንያቱም የጠቀስኩት ነው፤ ሌላ ነገር የለውም።

ስለ ወቅታዊ ሁኔታው

በዚህ ሰዓት በብሔራዊ ሊግ የትግራይ ውሃ ሥራ እግር ኳስ ክለብ እያሰለጠንኩ ነው። ጥሩ ዓመት ነው ያሳለፍኩት፤ ምድባችንን እስከመምራት ደርሰን ነበር። ከአመራሩ፣ ከኮሚቴው እና ከመላው የቡድን አባላት ተባብረን ጥሩ ቡድን ሰርተናል። በቀጣይም ይህን የተሳካ ስራ ለማስቀጠል እንሰራለን።

የሚያምንበት የአጨዋወት መንገድ

በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ቶሎ ቶሎ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል የሚደርስ ቡድን ደስ ይለኛል። ከኳስ ውጭ በፈጣን እንቅስቃሴዎች ‘Press’ የምያደርግ እና ሲያጠቃ ደግሞ ቅድም እንዳልኩህ በፈጣን ሽግግር ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል የሚደርስ ቡድን መስራት እፈልጋለው።

ስለ እቅዱ

በአጠቃላይ ትልቅ አሰልጣኝ የመሆን ህልም አለኝ። ለሀገሬ እግር ኳስ አንድ ነገር ማበርከት እፈልጋለው። በሀገራችን እግርኳስ እድገት ለማግኘት ከባድ ነው፤ እኔም አቅሜን አሳድጌ ጥሩ አሰልጣኝ ለመሆን ነው የማልመው።

በመጨረሻ …

መጨረሻ ላይ በእግር ኳስ ሕይወቴ ላይ አስተዋፅኦ ለነበራቸው ላመስግን። ለወልዋሎ እግርኳስ ክለብ፣ ለሁሉም የስፖርት ኮሚሽን የነበሩ ለእነ ማሩና ኮማንደር ኪዳነ ለወልዋሎ ደጋፊ እና ከኔ ጋር ለሰሩ ሁሉም ተጫዋቾች እና ባለሞያዎች ማመስገን እፈልጋለው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ