“በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ መሐል ለመጫወት እጓጓለሁ” ተስፈኛው አማካይ በየነ ባንጃ

በኢትዮጵያ እግርኳስ በቅርብ ጊዜያት ከታዩ ድንቅ ታዳጊ አማካዮች መሀል ይጠቀሳል፡፡ በአፍሮ ፂዮን ከ17 ዓመት በታች በመጫወት የጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ ዘልቆ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ቡና የተስፋ ቡድን ውስጥ እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባል በመሆን ተመርጦም ተጫውቷል፡፡ በውድድሩም አምበል ሆኖ ቡድኑን የመራ ሲሆን ከአማካይ ስፍራ እየተነሳ በሚያስቆጥራቸው አስገራሚ ግቦች የተነሳ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሚዲያዎች አወድሰውታል፡፡ በዛሬው የተስፈኛ አምዳችንም ታዳጊውን በየነ ባንጃውን ይዘንላችሁ ቀርበናል።

በርካታ ታዳጊ ልጆች ከየአካባቢው ወጥተው በክለብ ደረጃ ደምቀው የሚታዩበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም። ምንም እንኳን የሀገራችን እግርኳስ ካለበት ደረጃ ፈቅ ባይልም በግላቸው አንፀባራቂ እንቅስቃሴን የሚያሳዩ ተጫዋቾችን በየጊዜው እንመለከታለን። ከእነዚህም መሀል አንዱ በተለይ በታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ባደረገው እንቅስቃሴ በብዙሀኑ የስፖርት ቤተሰብ ዓይን ውስጥ የገባው በየነ ባንጃ ነው፡፡

ተወልዶ ያደገው እዚሁ አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ቢሆንም ለእግርኳሱ ከነበረው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ የታክሲ እየፈላለገ በመጓዝ ወደ ኮተቤ አካባቢ እየሄደ ጎዶሊያስ በሚባል የፕሮጀክት እግርኳስ ሥልጠና ውስጥ በመታቀፍ የመጫወት ህልሙን እውን ማድረግ ጀምሯል። ይሁን እና ለጥቂት ቀናት ብቻ በዚህ ቡድን ውስጥ ካሳለፈ በኃላ ከትውልድ ሠፈሩ ወደ ሥልጠና ቦታ ለመሄድ የትራንስፖርት የገንዘብ ችግር እየገጠመው በመምጣቱ ሥልጠናውን ለማቆም ተገደደ። ነገር ግን የዚህ ቡድን አሰልጣኝ ተጫዋቹ በነበረው የአጭር ጊዜ ቆይታ ተስፋ ያለው መሆኑን በመመልከቱ አፈላልጎ ቤተሰቡ ቤት ድረስ በመሄድ አግኝቶት ወደ ቡድኑ እንዲመለስ አደረገው። አብዛኞቹ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋቾች ከደሀው ማህበረሰብ መጥተው ትልቅ ደረጃ ላይ ሲደርሱ እየተመለከትን ሲሆን ይህም ታዳጊ ዳግም ወደ ልምምድ ከተመለሰ በኃላ በትልቅ ደረጃ ላይ ደርሶ መታየትን በማለን ጠንካራ ልምምዶችን በመስራት ራሱን ማጎልበቱን ቀጥሏል፡፡

በዚህ ቡድን ቆይታው ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን እያሳደገ በመምጣቱ 2009 ላይ ወደ አፍሮ ፂሆን ከ17 ዓመት በታች ቡድን ገብቶ በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ለሁለት ዓመታት ቡድኑን በአማካይ ስፍራ ላይ ከማገልገሉ በዘለለ በአምበልነትም ጭምር ቡድኑን መምራት ችሏል፡፡ 2010 ብዙዎች የሀገራችን ተመልካቾች እና በአፍሪካ ሚዲያዎች ዘንድ ይህ ተጫዋች በተደጋጋሚ ለመጠራት የበቃበት ዓመት ነበር፡፡ ዝዋይ ላይ በነበረው የ17 ዓመት በታች የማጠቃለያ ውድድር ላይ እያለ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ለኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለሴካፋ ዋንጫ ታንዛኒያ ላይ በተደረገው ጨዋታ ሊመርጠው ችሏል። ተጫዋቹ ምንም እንኳን የመጀመሪያው የብሔራዊ ቡድን ተሳትፎው ቢሆንም በውድድሩ ላይ ከአማካይ ስፍራ እየተነሳ ከአጥቂው ምንተስኖት እንድሪያስ በመቀጠል ለቡድኑ አስገራሚ ግቦችን እያስቆጠረ የቡድኑ ሁለተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆን ቻለ፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያን በአምበልነትም ጭምር እየመራ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ እንድታጠናቅቅ ይህ ታዳጊ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል።

ከ2011 ጀምሮ አፍሮ ፂዮንን ከለቀቀ በኃላ በኢትዮጵያ ቡና ከ20 ዓመት በታች ቡድንን በመቀላቀል እየተጫወተ የሚገኘው እና አሁንም በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ አስደናቂ አቅሙን ሲያሳየን የነበረው በየነ ባንጃው ስለእስካሁኑ የእግር ኳስ ህይወቱ ይህን ይላል።

“ከፕሮጀክት በኃላ ወደ አፍሮ ፂዮን ኮንስትራክሽን ነው የሄድኩት። የጎዶሊያስ አሰልጣኝ ከአሰልጣኙ ጋር ይግባባ ስለነበር ወደዛ ሄድኩኝ። በአፍሮ ፂዮን ሁለት ዓመት ተጫውቻለሁ። በቡድኑ የነበረኝም ጊዜ ደስ የሚል ነበር ከአፍሮ ፂዮን ከወጣው በኃላ አምና ወደ ኢትዮጵያ ቡና መጥቼ እየተጫወትኩኝ እገኛለሁ።

“እግር ኳስ ተጫዋች እንድሆን ያነሳሳኝ አጎቴ ነበር ፤ አምባቸው ይባላል። እሱ ኳስን በሠፈር ውስጥ ሲጫወት ሳይ ኳስ የመጫወት ፍላጎት በውስጤ አደረ። ተወልጄ ባደኩበት ሽሮሜዳ ደግሞ ታፈሰ ተስፋዬ ኢትዮጵያ ቡና ሲጫወት የሚያሳየውን እንቅስቃሴን ማየት ባልችልም እሰማ ነበር። ያንን እየሰማሁ ስላደኩም አጎቴ እና ታፈሰ ኳስ ተጫዋች እንድሆን መነሻ ሆነውኛል።

“በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። ልመረጥ የቻልኩት ዝዋይ ላይ በነበረው ውድድር አሰልጣኝ ተመስገን ዳና መረጦን ነው። እሱ ቡድን እንደውም ብዙ ርቀት ይጓዛል ብሎ የጠበቀ የለም። ብዙ ዝግጅትም አልነበረንም። የዕድሜ ምርመራ እየተባልን አዲስ አበባ ከአዲስ አበባ ሀዋሳ እየሄድን ቢያንስ አዲስ አበባ ውስጥ አምስት ቀን ብቻ ነው በሥርዓት የተዘጋጀነው። ነገር ግን እዛ ትንሽ ልምምድ ሰርተናል፡፡ ቡድኑ ውስጥ ሁሉም ተጫዋቾች የሀገር ስሜት ስላላቸው አብዛኛውም አዲስ ስለተመረጡ ከፍተኛ የመጫወት ፍላጎት የነበራቸው በመሆኑ አሪፍ ውጤት ይዘን ለመምጣት የቻልነው አድርገን ያው ዋንጫውን ብናጣም ሁለተኛ መሆናችን ለእኛ ትልቅ ክብር ነው። የመጀመሪያ ተሳትፏችን ስለሆነ ጥሩ ጊዜ ነበረን። ከ20 ዓመት በታችም አምና ተመርጬ ነበር። ከጅቡቲ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ተሳትፌ ነበር። ጅቡቲ በነበረው ሁለተኛ ጨዋታ ግን በፓስፖርት ችግር ሳልጫወት ቀረሁ። አሁንም የመጫወት ብዙ ጊዜ አለኝ ከሠራሁ ዕድሉን አሁንም አገኘዋለሁ።

“ሀገሬን በአምበልነት በመምራቴ ደስ ቢለኝም የሀገርን ኃላፊነት ይዞ መጫወት ደግሞ በጣም ይከብዳል። ግን ለሀገር ይህን ዕድል አግኝተህ ተጫውተህ ጥሩ ውጤት ስትይዝ በጣም በጣም ደስ የሚል ነገር ነው። እንደ ብሔራዊ ቡድን መመረጥ እና ጥሩ ውጤት እንደ ማምጣት ደግሞ በህይወት የሚያደስት ነገር የለም። ከፈጣሪ ጋር ለሀገሬ ከዚህ በላይ ብሰራ በጣም ደስ ይለኛል።

“ኢትዮጵያ ቡና ከገባው ሁለት ዓመቴ ነው፡፡በቡና ባለኝ ነገር ደስተኛ ነኝ። አሰልጣኞቹ ፣ ተጫዋቾቹ እና የቡድኑ መንፈስ ሁሉም ነገር አሪፍ ነው። የወደፊት ዕቅዴ ከቡና ጋር ጥሩ ነገር አሳልፌ ወደ ዋናው ቡድን በማደግ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አንስቼ ለኢትዮጵያ ቡና አሪፍ ነገር ሰርተው እንዳለፉ ተጫዋቾች ታሪክን ሰርቼ ማለፍን እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ ቡና በጣም ምርጥ ቡድን ነው፡፡ ደጋፊው እኛ ተስፋዎችን ያበረታታል። እኛ በሄድንበት ሁሉ አይዟችሁ ይለናል። ዋናው ቡድን አድጌ ለቡና በቻልኩት አቅም ሰርቼ ባልፍ ደስ ይለኛል። ደጋፊውም ‘አይዞህ በርታ’ ስለሚለኝ ጥሩ ነገርን ሰርቼ አልፋለሁ ብዬ አስባለሁ። በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ መሀል ለመጫወት እጓጓለሁ።

“ትልልቅ ተጫዋቾች የደረሱበት ለመድረስ ከአሰልጣኜ የሚሰጠኝን ልምምዶች በመስራት በግሌም አሁን በዚህ በተቋረጠበት ወቅት እየሰራሁኝ እገኛለሁ። ታላላቆቼ እና ለእግር ኳሱ ቅርብ ከሆኑት ሰዎች የምባለውን እየሰማሁ ትልልቅ ተጫዋቾች የደረሱበት ለመድረስ ምክርም እየሰማሁ እገኛለሁ።

“እኔ ዛሬ ላይ እዚህ ለመድረሴ ቤተሰቦቼን ማመስገን እፈልጋለሁ። ከጎኔ ሆነው አይዞህ እያሉ እዚህ አድርሰውኛል። ቶማስ ወልዴ የአፍሮ ፂዮን አሰልጣኝ ለእኔ ትልቅ ውለታ ውሎልኛል። ሌላ የማመሰግነው ትምህርት ቤት የተዋወቅኩት ጓደኛዬ ኤልያስን ነው። ሠፈሬ ጫካ ስለሆነ ትንሽ አምሽቼ ከልምምድ ስመጣ ‘እኔ ጋር ዕደር’ እያለ ብዙ አግዞኛል። እሱ ከጓደኛም በላይ ነው ፤ በጣም ላመሰግነው እፈልጋለሁ። ለእኔ እዚህ መድረስ ከቤተሰቦቼ ቀጥሎ አንደኛ ተጠቃሸ እሱ ነው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ