የዳኞች ገፅ | ፈላስፋው የቀድሞ ዳኛ ጋሽ ዓለም አሠፋ…

ከቀደሙት ዳኞች መካከል በአህጉራዊ ውድድሮች የሀገራችንን ስም በማስጠራት የሚጠቀሱት ባለ ግርማ ሞገሱ የፍልስፍና ሰው ኢንተርናሽናል ዳኛ ጋሽ ዓለም አሠፋ የዛሬው የዳኞች ገፅ እንግዳችን ነው።

በ1960 የመምርያ ዳኝነት ኮርስ ከወሰደ በኃላ የተለያዩ የተስፋ ቡድኖች ጨዋታዎችን በማጫወት የዳኝነት ህይወቱን የጀመረው ጋሽ ዓለም አሠፋ በተለያዩ ምክንያቶች አስመራ ከተማ ላይ ውድድሮች እየተቋረጡ መቀጠላቸው ፌደራል ዳኛ የመሆን ጊዜውን ቢያዘገይበትም ከ12 ዓመታት በኋላ በ1972 የፌደራል ዳኛ መሆን ቻለ። ትውልድ እና ዕድገቱ ኤርትራ አስመራ ከተማ የሆነው ጋሽ ዓለም የአሰብ ቡድን የክልል ሻምፒዮና ተሳታፊ በመሆኑ በዳኝነቱ በኩል አሰብን ወክሎ አዲስ አበባ በመምጣት ጅማ ከተማ ላይ ጅማ ከተማን ከወሎ ያጫወተበት አጋጣሚ ለቀጣይ የዳኝነት ህይወቱ መሠረት ጥሎለታል።

“ሰው የዘራውን ነው የሚያጭደው” የሚል የህይወት መመርያ ያለው ጋሽ ዓለም አሠፋ ኢንተርናሽናል ዳኛ ከሆነበት ከ1978-87 ባለው የዘጠኝ ዓመታት ቆይታው ውስጥ በአህጉራዊ ውድድሮችን ለመምራት ከመቻሉ ባሻገር በሀገር ውስጥ አሉ የሚባሉ ትልልቅ ጨዋታዎችን በመዳኘት በከፍተኛ ሁኔታ አገልግሏል። ዳኝነት ካቆመበት ጊዜ አንስቶ የጨዋታ ታዛቢ እና የዳኞች ኮሚቴ አባል በመሆን ሲሰራ ከቆየ በኃላ በተለያዩ እግርኳሱን ወደ ገንዘብ የሚቀይሩ የገበያ ጥናት ስራዎችን ሲሰራ ቆይቶ በአሁኑ ወቅት በግል የንግድ ዘርፍ በመግባት እየሰራ ይገኛል። 45 ዓመታትን በስፖርቱ የቆየው ጋሽ ዓለም በዳኝነት ህይወቱ ዙርያ በዛሬው የዳኞች ገፅ አምዳችን እንግዳ አድርገነዋል።

ትውልድ እና ዕድገትህ የት እንደሆነ በመጠየቅ ልጀምር ጋሽ ዓለም ?

“የተወለድኩት አስመራ ነው። ቤተሰቦቼ የራያ እና ማይጨው ቆቦ አካባቢ ሰዎች ናቸው። አባቴ የመኪና ሹፌር ስለነበር በስራ ምክንያት ወደ አስመራ መጥተው እየኖሩ ሳሉ እኔ ልወለድ ችያለው። በዚሁ በአስመራ ከተማ እግርኳሰን እየተጫወትኩ አደግኩ።”

እንዴት ነው ወደ ዳኝነቱ ልትገባ የቻልክበት መነሻ ምክንያት ምን ነበር ?

“እንደሚታወቀው አስመራ ላይ እምባሶይራ እና ሀማሴን የሚባሉ ትልልቅ ቡድኖች ነበሩ። ከእነርሱ ጋር ለመጫወት ወደ አስመራ እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ናሽናል ሲሚንት ፣ መብራት ኃይል ይመጡ ነበር። ታዲያ የእነርሱን ጨዋታ ለማየት ስታድየም ለመግባት አቅሙ ስሌለን በትቦ ስር እየገባን ሁሌ እየተደበደብን ጨዋታ እንመለከት ነበር። በአንድ ወቅት የዳኝነት ስልጠና መውሰድ የምትፈልጉ ከአዲስ አበባ የሚመጡ አሰልጣኞች ስላሉ እንድትመዘገቡ የሚል ማስታወቂያ ፌዴሬሽኑ ያወጣል። በዛን ጊዜ የአስራ አምስት ዓመት ልጅ ነበርኩ ፤ ስልጠናውን በአስራ አምስት ቀን አጠናቅቄ የመጀመርያ መምርያ የዳኝነት ኮርስን ወሰድኩ።”

የዳኝነት ኮርስ ለመውሰድስ ምክንያትህ ምን ነበር ?

“መጀመርያ ዳኛ እሆናለው የሚል ሀሳብ አልነበረኝም። ሆኖም እግርኳስ ተጫዋች የመሆን ፍላጎት ነበረኝ። ቅድም እንደነገርኩህ ከአዲስ አበባ የሚመጡ ቡድኖችን ጨዋታ ለማየት በተለዩ መንገዶች ስታድየም እገባ ነበር ፤ እግርኳስን በጣም እወድ ነበር። ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ እጫወታለው። ሜዳም ገብቼ ኳስ እመለከት ነበር። በተለይ በ1959 ኤርትራዊው ስዩም ታረቀኝ በየአፍሪካ እና የዓለም ዋንጫን ያጫወተ ትልቅ ዳኛ ነው ፤ እርሱን በጣም አደንቅ ስለነበር ወደ ዳኝነቱ ልገባ ችያለው።”

ዳኝነት ስትጀምር ለመጀመርያ ጊዜ ያጫወትከውን ጨዋታ ታስታውሳለህ?

“ትላልቅ የአስመራ ቡድኖች ከዋናው ቡድናቸው በመቀጠል ሁለተኛ ቡድን ነበራቸው ፤ ዛሬ የተስፋ ቡድን እንደሚባለው ማለት ነው። በጣም የሚገርመው አሁን ቀርቷል እንጂ ከዚህ ቀደም አንድ ጨዋታ ከመካሄዱ አስቀድሞ ማለትም ለምሳሌ ሀማሴን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ 10:00 የሚጫወቱ ከሆነ 08:00 ላይ የታዳጊዎቹ ጨዋታ ይካሄድ ነበር። ታዳጊዎቹን በብዙ ተመልካቾች መሐል ለማበረታታት እና ድፍረቱን አንዲያገኙ ለማነሳሳት ታስቦ ነው። አሁንም እንደዛን ጊዜ የታዳጊዎቹን ጨዋታ በተመልካች መሐል መካሄድ ያለበት መሆኑን ጠቁሜ ማለፍ እፈልጋለው። ምክንያቱም ለሀገራችን እግርኳስ ያለው ጠቀሜታ የጎላ በመሆኑ ነው። የብዙዎች ማይ ላህም እና ሰራይ የሚባሉ የታዳጊ ቡድኖች ጨዋታ አጫውቼ ዳኝነት ጀመርኩ። ከዚህ በኋላ ሦስት አራት ዓመት ተመሳሳይ ዕድሜ ላይ የሚገኙ የታዳጊ እና የፋብሪካ ውድድሮችን ስናጫውት ቆየን ልምድም እያገኘን እየበሰልን መጣን ፤ ገንዘብም እያገኘን መጣን። በመቀጠልም ደረጃችንን አሻሽለን ከፍ ወደሚሉ ጨዋታዎች ተሻግረናል።”

አስመራ የተለዩ ችግሮች በመፈጠራቸው ወደ ትውልድ ሀገርህ አምርተሀል። እዛስ ምንድን ነበር ትሰራ የነበረው ?

“በአስመራ ከተማ ነገ ረብሻ ሊፈጠር እንደ ዛሬ አባቴ ይዞኝ ወደ ቤተሰቦቼ ሀገር አላማጣም ኮረምም ወሰደኝ። አባቴ በዛን ጊዜ ከአስመራ ይዞኝ ባይወጣ ኖሮ ጦሩነቱም ከባድ ስለነበር አሁን ያለሁበት ደረጃም አልደርስም ነበር። አላማጣ ኮረም ሆኜ እግርኳስን በተከላካይነት እየተጫወትኩ ነበር። እንግዲህ አስመራ ጦርነት የነበረ በመሆኑ ውድድሮች በመቆማቸው እኔም ለሦስት ዓመት ከዳኝነቱ ተገልዬ ቆየሁ። የሚገርምህ አንድ ቀን አዲስ አበባ ሄጄ በዳኝነቱ ትልቅ ደረጃ እደርሳለው የሚል ፍላጎቱ ህልሙ ስለነበረኝ ጦርነቱ ሲበርድ በ1969 አሰብ ከተማ ገባሁኝ። በአንድ የነዳጅ ማድያ እየሰራው ባለበት ወቅት አስመራ ሳጫውት የሚያቁኝ ሰዎች ‘ይሄ እኮ በጣም ጎበዝ ዳኛ ነው’ እያሉ ያውሩ ነበር። ያው ዳኛ የመሆን ፍላጎቱ ስለነበረኝም የተለያዩ የመካናይዝድ ክፍለጦር ቡድኖች አቋቁመን እኔም የአሰብ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀኃፊ ሆኜ እየሰራው ዳኝነቱን ዳግም ጀመርኩ። አሁን ሳስበው በጣም ይገርመኛል። አሰብ እጅግ ከፍተኛ ሙቀት እንዳለ ይታወቃል። ስምንት ሰዓት አጫውቼ አስር ሰዓት በድጋሜ አጫውት ነበር። በዛ ከፍተኛ ሙቀት ሁለት ጨዋታ ማጫወት በጣም ከባድ ነበር። ዳኝነቱን በጣም እወደው ስለነበር እንዲህ ያሉ መስዕዋትነቶችን እከፍል ነበር።”

በመቀጠል ደግሞ የምትወደውን ዳኝነት ወደ ትልቅ ምዕራፍ የምታሸጋግርበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። ይህ አጋጣሚ ምን እንደሆነ አጫውተኝ…

“አሰብ ላይ ካጠናከርናቸው ቡድኖች ምርጥ 11 እየመረጥን ለክልል ውድድር አንድ ቡድን እንልክ ነበር። አሰብ የክልል ውድድር ሲሄድ ዳኛም አብሮ እንዲሄድ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፈቅዶ ስለነበረ እኔ በዳኝነቱ ተመርጬ በ1970 ከአዲስ አበባ ህዝብ ጋር ተዋወቅኩኝ። ከአሰብ ቡድን ውጪ ጨዋታ ተሰጠኝ ፤ ያንጊዜ ልጅነቱ አለ ሳጫውት ፍጥነት ነበረኝ። ከሮጥኩኝ ፈፅሞ አልያዝም ነበር። አንድ ሁለት ሦስተ ጨዋታ በአስገራሚ ፍጥነት እና ብቃት መራው በስታዲየሙ የነበረ ተመልካች ‘ማነው ይሄ የሚገርም ፍጥነት ያለው ? ‘ በማለት ወደደዱኝ ‘አሰብ… አሰብ’ እያሉ በመጮህ አድናቆታቸውን ቸሩኝ። በድጋሜ ተመድቤ በ1972 አዲስ አበባ መጣው። በቃ ህዝቡ ወደደኝ ‘ይመደብ ያጫውት ! ‘ እያለኝ አዲስ አበባ መመላለስ ጀመርኩ።”

ፌዴራል ዳኝነቱን መቼ እና እንዴት አገኘህ ?

“በ1972 ላይ ፌደራል ዳኛ ሆንኩኝ አዲስ አበባም እየተመላለስኩ ማጫወት ጀመርኩኝ። በዚሁ ዓመት ጅማ ለይ የፍፃሜ ጨዋታ አጫውቼ ምስጉን ዳኛ ተብዬም ሽልማት አግኝቻለው። በዳኝነት ዘመኔም የመጀመርያውን ሽልማት ያገኘሁት ያኔ ነው። በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ሳገኝ ጄነራል ተስፋዬ ቁሬ የሚባሉ የመንግስቱ ኃይለ ማርያም ሚዜ በወቅቱ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበሩ። ጠርተውኝ ‘አንተ ልጅ በጣም ትሮጣለህ ሰውም ወዶሀል ከአሰብ ወደ አዲስ አበባ መዘዋወር ትፈልጋለህ ?’ አሉኝ። እንኔም ‘እሺ’ አልኳቸው እና ብለው ቢሮ ጠሩኝ። ቢሮ ስሄድም ‘አደራህን እንዳታስነቅፈኝ በፖለቲካ ፣ በዘር ፣ በኃይማኖት ውስጥ እንዳትገባ አሉኝ። ያው ብዙ ጊዜ ከኤርትራ የሚመጡ ግለሰቦች የተለያዩ ነገሮችን ያነሱ ስለነበር አስጠነቀቁኝ። ‘እሺ’ ብዬ ከሦስት ዓመት በኃላ በ1976 ሙሉ ለሙሉ ኑሮዬን ጠቅልዬ አዲስ አበባ በማድረግ የአዲስ አበባ ዳኛ ሆንኩኝ። ለሁለት ዓመት ካጫወትኩ በኃላ ደግሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ መሆን ቻልኩ። ኢንተርናሽናል እስከ ሆንኩበት ጊዜ ድረስ ረዳትም ዋና ዳኛም በመሆን ደርቤ አገለገልኩኝ። በመጨረሻም ፊፋ ህግ ሲያወጣ አስካቆምኩበት ወቅት ድረስ በዋና ዳኝነት አገልግያለሁ።”

መቼ ነበር ኢንተርናሽናል ዳኛ የሆንከው ? በአፍሪካ መድረክስ መጀመርያ ያጫወትከው ጨዋታ ?

“በ1978 የኢንተርናሽናል ዳኝነት ማዕረግ አግኝቼ እስከ 1987 ድረስ በኢንተርናሽናል ዳኝነቱ ለተከታታይ ዓመታት አጫውቻለው። እንዲያውም በአዲስ አበባ ስታድየም የመጀመርያ ባጄን ደረቴ ላይ ያጠለቁልኝ ታለቁ የስፖርት ሰው እና የኢትዮጵያ ዳኝነትን የቀየሩት ፣ በዓለም እና በአፍሪካ ዋንጫ የሀገራቸውን ስም ከፍ አድርገው ያስጠሩት ፣ የወቅቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኤርትራዊው ተስፋዬ ገብረየሱስ ነበሩ። የመጀመርያ ኢንተርናሽናል ጨዋታዬ ደግሞ ጁቡቲ ላይ ነበር። በአፍሪከ ዋንጫ ማጣርያ ጁቡቲ እና ዩጋንዳን ነው ያጫወትኩት። ከዚህ በኃላ ካፍ አምኖብኝ ለቁጥር የሚታክቱ የተለያዩ የማጣርያ ጨዋታዎችን አጫውቻለው። በተለይ ግብፅ ሁለተኛ ቤቴ እስክትመስል ድረስ በጣም ተመላልሼ ብዙ ጨዋታ አጫውቻለው። ከጋሽ ተስፋዬ ቀጥሎ በግብፅ ብዙ ጨዋታዎችን አጫውቻለው። እንዲያውም እንደ ገዳቸው ነው የሚያዩኝ የነበረው። ከእነርሱ ጋር ምንም ነገር የለም ምክንያቱም ተጠንቅቄ ነው የማጫውተው ፤ በህግ በኩል ምንም ክፍተት የለም። እኔ አንድ ዕምነት አለኝ ለጊዮርጊስ ለቡና ፣ ለግብፅ ለታንዛንያ ለእከሌ ብዬ የኔን ዝና አሳልፌ መስጠት ማለት እንደ እንስሳነት ነው የምቆጥረው። የማይገባቸውን አልሰጥም የሚገባቸውን አልከለክልም። በጣም የሚገርምህ በሀገር ውስጥ ፖሊስ ፣ አየር ኃይል እኔ ካጫወትኳቸው አይሸነፉም። ግብፅም ሄጄ እንደዛው ነው። ዛማሊክ እና አል አህሊ ተሸንፈው አያውቁም። ምንም አድርጌ በገንዘብ ተነካክቼ አይደለም ገጠመኝ ነው። ገና ኤርፖርት ስደርስ ‘ያ ዓለም አሠፋ መጡ’ እያሉ መመለክ ጀምሬ ነበር። ብቻ ምን ልበልህ እጅግ ወሳኝ የሚባሉ የአፍሪካ፣ የዓለም፣ የኦሊምፒክ ፣ የክለቦች ማጣርያ ጨዋታዎችን በብዛት አጫውቻለው።”

ወደ ኢንተርናሽናል ዳኝነትህ እነመለሳለን ፤ በሀገር ውስጥም አሉ የሚባሉ ትልልቅ የሀገሪቱን ውድድሮች በብቃት መርተሀል። ለአንተ ከሀገር ውስጥ ካጫወትካቸው ጨዋታዎች ፈትኖኛል የምትለው የቱ ነው ?

“በሀገሪቷ ውስጥ ትልቅ ዳኞች ጭምር ማጫወት የሚፈሩትን እኔ ምንም ሳልፈራ በድፍረት እየተቀበልኩ አጫውቻለው። በአጠቃላይ ከ1976–83 ድረስ በሙሉ ማለት ይቻላል። ሀገሬም በእኔ ብቃት እያመነችብኝ እጅግ የሚፈትኑ በርካታ ጨዋታዎች ማጫወት ችያለው። እንደውም አንድ አጋጣሚዬን ላጫውትህ። በ1982 ምድር ጦር እና ኢትዮጵያ ቡና ለፍፃሜ ዋንጫ ተገናኝተዋል። አዲስ አበባ ስታድየም እንደዛ ዕለት ሞልቶ አያውቅም ፤ ውጪ ያለውን ተመልካች ብዛት ልነግርህ አልችልም። ጨዋታው ፈጣን ነበር ፤ ትንሽ ዝናብ ነገርም ነበር። ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ በሚስማር ተራ አቅጣጫ (በወቅቱ የጦሩ ደጋፊዎች የሚቀመጡበት ቦታ ነው) በለጠ ወዳጆ የምድር ጦር ግብጠባቂ ፤ ኳስ በእጁ ይዞ ከለጋ በኋላ ወደ ኃላ እየዞርኩ ሜዳውን እየተቆጣጠርኩ ድንገት ወደ መሐል ሜዳ እየደረስኩኝ ሳለሁ ሚልዮን በጋሻው በለጠን ምን ይበለው ምን አላውቅም ኳሱን ከጠለዘ በኃላ ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን አካባቢ ሚሊዮንን በእግሩ ሆዱን ሲመታው ተመለከትኩኝ። ፊሽካዬን ነፍቼ ጨዋታውን አስቁሜ ሚሊዮን ህክምና እንዲያገኝ አድርጌ ነገሩን አረጋጋሁ። የጦሩ ተጫዋቾች ሀገር ሠላም ነው ብለው ኳሱን አሻምቶ ጨዋታውን ያስጀምራል ብለው ነው የጠበቁት። እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ በስታድየሙ የነበሩት ደጋፊዎች ሁሉ ማንም ይህን አላሰበም አልጠበቀም። ‘ኳስ ያለችበት ሳይሆን ጥፋት የተሰራበት ቦታ ቅጣት ምት ይሰጣል’ ተብዬ የተማርኩትን ለመተግበር ኳሷን በእጄ ይዤ ፍፁም ቅጣት ምት ሰጠሁኝ። ጨዋታው የፍፃሜ ዋንጫ ነው። በርካታ ተመልካች አለ ፤ እንዳላየ ሆኜ ማለፍ እችላለው። ሆኖም ግን “ህግ ባይሰበር ይጣመማል” ብዬ ለቡና ፍፁም ቅጣት ምቱን ሰጠሁኝ። ከዚህ በኃላ ምን ልበልህ ስታድየም የነበረው ተመልካች በድንጋጤ ፀጥ አለ። ያልጠበቁት ስለሆነ ተጫዋቾቹ ከበቡኝ። ሙሉዓለም እጅጉ መጣና ‘ምንድን ነው የምትሰራው ጋሽ ዓለም ምንድነው? የምታደርገው’ እያለ እየጮህ ይናገራል። ብቻ በጭቅጭቅ ጨዋታው ሠላሳ ደቂቃ ተቋረጠ። ‘ህግ ለእኛ ብቻ ነው የሚሰራው ? ተደርጎ የማያውቅ ውሳኔ ነው የምትወስነው’ እያሉ የጦሩ አሰልጣኝ መሰለም ወደ ሜዳ ገብቶ አበደ። ‘ ምንድን ነው የምትሰራው ? ፔናልቲውን የምትሰጥ ከሆነ ሬሳህ ከዚህ ይወጣል’ ይለኛል። ‘ምንም ማድረግ አልችልም ሬሳዬ ሊወጣ ይችላል ህጉ ግን ይሄ ነው’ አልኩኝ። መጨረሻ ላይ በሚስማር በኩል የነበረ የጦሩ ደጋፊ ገንፍሎ ‘ዳኛ ሌባ !’ እያለ ይሳደብ ጀመር። ካታንጋ ያሉ የቡና ደጋፊዎች ደግሞ ‘ዓለም አንበሳ’ እያሉ ይጨፍራሉ። የወቅቱ የፖሊስ አዛሽ ጀኔራል ያዴታ ጉርሙ ወደ ሜዳ ገብተው ‘ይሄን ነገር በድጋሜ አጢነው ችግር እንዳይፈጠር’ ይሉኛል። አይህ ህግ ነው። የምከልሰው ነገር አይኖርም። ፔናልቲውን ብሽር የቡና ደጋፊዎች ደግሞ ዝም አይሉኝም። ህግ ህግ ነው አልኩኝ። እሺ ብለው ሜዳውን በልዩ ኃይል አስከብበው ፍፁም ቅጣት ምቱ ተመትቶ ጎል ይቆጠራል። በቀረው ደቂቃ ጨዋታውን በሙሉ ኃይሌ ተቆጣጥሬ ጨዋታው በዚህ ውጤት ይጠናቀቃል። ከዚህ በኋላ ደጋፊው የት እንደገባ አይታወቅም ፤ ኃይለኛ ረብሻ ተፈጠር ፣ ድብልቅልቅ አለ። እስከ ማታ ሁለት ሰዓት ድረስ ‘ሬሳህ ይወጣል’ እያሉ ይሳደባሉ። በፖሊስ ተከብቤ ማታ ሁለት ሰዓት ከዳኞች ክፍል ወጣሁኝ። ከጊዮን ሆቴል እስከ ለገሀር ያለው መንገድ የነበሩ መኪኖች የቀረ የለም ድቅቅ ነው ያሉት ፤ ዱቄት ሆነዋል። ይህን ሁኔታ ሁሌም አስታውሰዋለው።”

በኢንተርናሽናል ዳኝነት ዘመንህ የዓለም ፣ የአፍሪካ ዋንጫ እንዲሁም የክለቦች የፍፃሜ ጨዋታዎች አጫውተህ ታውቃለህ ?
“አላጫወትኩም። አጋጣሚ ሆኖ በ1987 የአፍሪካ ዋንጫ ማጫወት የሚችልበት ዕድሉ እያለ አሁን እንዲህ ነው አልልህም ፌዴሬሽን በነበሩ ሰዎች የተለያዩ ሴራዎች ተሰርተው ለአንድ ዓመት ኢትዮጵያውያን ዳኞች በካፍ በመታገዳቸው የአፍሪካ ዋንጫ የማጫወት ዕድሌ ተበላሽቷል። በዚህ በጣም ተከፍቼ ከዚህ በኃላ ዳኝነትን አልሰራም ብዬ ራሴን ከዳኝነት አገለልኩኝ። ሆኖም ዓለም ሁሉ ትኩረት ያደረገበት ለእኔም ትልቁ ጨዋታ የምለው ሰማንያ ሺህ ተመልካች በተገኘበት አፍሪካ ዋንጫ ለመግባት ዛምቢያ እና ዚምባብዌ ያደረጉትን ወሳኝ ጨዋታ አጫውቻለው። አስቀድሞ ይህን ጨዋታ ለማጫወት ተመድቤ የነበረ ቢሆንም የዛምቢያ ቡድን በአውሮፕላን አደጋ ሁሉም የቡድኑ አባላቱ ህይወታቸው አልፎ ካሉሺያ ቡዋሊያ ብቻ በመትረፉ ጨዋታው ተሰርዞ በድጋሜ ሊደረግ ሲል ራሴ ተመልሼ ተመደብኩ። የዛምቢያ ቡድን በጣም ነው የሚገርመው። ከዛ የሀዘን ስሜት ወጥተው በአስራ አምስት ቀን ዝግጅት ዚምባብዌን ገጥመው በደርሶ መልስ ውጤት አሸንፈው የአፍሪካ ዋንጫ የገቡበትን ጨዋታ አጫውቻለው። የሚገርምህ የተሸነፈው የዚምባብዌ የቡድን መሪ ‘ምንም የጎደለ ነገር የለም’ በማለት ተሸንፈውም ስካርፕ ሸልሞኛል ፤ እስካሁን ድረስ ስካርፑ አለ።”

በሀገር ውስጥ እና በአፍሪካ ትልልቅ ውድድሮች ላይ ሰርትሀል። ሆኖም የዓለም እና የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ባለማጫወትህ አሁን ላይ ሆነህ ስታስበው የምትቆጭበት ነገር አለ ?

“በፍፁም ፤ ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም። የዛምቢያ እና የዚምባብዌን ጨዋታ ካጫወትኩ በኃላ የአፍሪካ ዋንጫ እንደማጫውት ተነግሮኝ ከእኛ ፌዴሬሽን በኩል የተለየ አሻጥር ተሰርቶ ስሜ ሳይተላለፍ ቀርቶ አፍሪካ ዋንጫ የማጫወት ህልሜ ተጨናግፏል። አስበው የአፍሪካ ዋንጫ ለመግባት ወሳኝ ጨዋታ እንዳጫውት ካፍ ዕምነት ጥሎብኝ ነበር። ከፍ ያሉ ጨዋታዎችን የማጫወት ልምድ እያገኘው መጥቼም ነበር። ከዚህ በኋላ የአፍሪካ ዋንጫ ማጫወት ብቻ ነበር የሚቀረኝ። ሆኖም ከእኔ አቅም ውጪ በሆነ ምክንያት እኔ ብቻ አይደለሁም አስራ አንድ ኢትዮጵያውያን ዳኞች በዚህ ምክንያት ሳይሳካልን ቀርቷል። የአፍሪካ ዋንጫ ማጫወት ትልቁ ዕቅዴ ነበር። ይህ ማንም የሚመኘው ነው። አለመሳካቱ በኔ ስህተት እና እንዝህላልነት ወይም እኔ ሳጫውት ስህተት ኖሮብኝ ቢሆን ላዝን እችል ነበር።”

በዳኝነት ዘመንህ ያገኘሀቸው የኮከብነት ሽልማቶች አሉ?

“እጅግ በርካታ ሽልማቶችን በአዲስ አበባም በአስመራም አግኝቻለው። አንድ የሚገርመኝን ሽልማት ልንገርህ። በነበረኝ ብቃት ሰዉ የሚጠራኝ ከመጣሁበት ሀገር አሰብ በመነሳት ‘አሰብ’ በማለት ነበር። አንድ የአፋር ተወላጅ አሰብን የሚወዱ ኳስ ወዳጅ ሰው ናቸው ፤ መሐመድ ኢብራሒም ይባለሉ። ‘አሰብን ስሟን ከፍ አድርገህ በመልካም ስላስጠራህ አንተ ከዚህ በኋላ በእግርህ አትሄድም ! ‘ ብለው መኪና ገዝተው ቁልፍ ሰጥተውኛል። ይህ የሆነው በ1972 ነበር። አብሪያቸው ለማስታወሻ አዲስ አበባ ስታድየም ፎቶ ተነስቻለው።

ጋሽ ዓለም ቀይ ካርድ ላይ እንዴት ነህ ?
“(እየሳቀ) ያው ያልተገባ ጥፋት ካገኘው ለቀይ ካርድ አልራራም ፤ መስጠት ነው። ይሄን ሁሉም ያቀዋል ፤ ህግ ህግ ነው። በምንም መንገድ ህግ መፋለስ የለበትም። ስለዚህ ቀይ ካርድ የሚያሰጥ ከሆነ በቃ ምን ችግር አለው መምዘዝ ነው። በነገራችን ላይ ካርድ ለመስጠት አልቸኩልም ፤ አረጋግቼ ነው። በጣም የሚገርምህ እርሱም በሬዲዮ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ ያወራዋል። ሙልጌታ ወልደየስን ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ካርድ ከሜዳ ያስወጣሁት እኔ ነኝ። ከዛ በፊት ቀይ ካርድ አይቶ አያቅም። የምሽት ጨዋታ ነበር ፤ ቡና ከመድን። ምን ብሎት እ ደሆን አላውቅም ሙልጌታ ሲማታ አየሁት። ‘ጋሽ ዓለም ሰድቦኝ ነው’ አለ። በቀይ ካርድ አስወጣሁት እርሱም በጊዜው በጣም አለቀሰ።”

ዳኝነትን መቼ አቆምክ ? ከዛ በኃላ የነበረህ የእግርኳስ አገልግሎትስ ምን ይመስል ነበር ?

“ቅድም እንዳልኩሁ በፌዴሬሽኑ በነበረ ሴራ የአፍሪካ ዋንጫ የማጫወት ዕድሌ ሲጨናገፍ በጣም ተከፍቼ በ1987 መጨረሻ ራሴን ከዳኝነቱ አገለልኩኝ። ሆኖም ከእግርኳሱ ሳልርቅ በአቶ ፀኃዬ እና በኢንጂነር ግዛቸው ዘመን በጨዋታ ታዛቢነት እና የዳኞች ኮሚቴ አባል በመሆን እንዲሁም በማርኬቲንግ ክፍል ውስጥ ብዙ ዓመት ሰርቻለው። በኃላ ላይ ብዙ ደስ የማይሉ ነገሮች ሲመጡ ወደግል የንግድ ስራዬ ላይ አተኩሬ መስራት ጀምሬያለሁ።”

ለ45 ዓመታት በስፖርቱ የነበረህ ቆይታ እንዳለ ሆኖ በሃያ ሰባት ዓመት ጨዋታ በመራህባቸው የዳኝነት ዘመንህ ለጨዋታ ራስህን እንዴት ነበር የምታዘጋጀው ?

“የተለየ ዝግጅት ነው የማደርገው። በስነ-ልቦናው እና በአካል ብቃቱ በኩል ራሴን ለጨዋታ ዝግጁ ለማድረግ በጣም ነው የምሰራው። ሙያውን እወደው ስለነበር እና ብዙ ነገሬን የለወጠ ሙያ በመሆኑ በጣም የተለየ ዝግጅት አደርጋለው። እንዲያውም አንድ የገጠኘኝ ነገር ልንገርህ። የአካል ብቃት ፈተና የሚሰጥ ከሆነ እኔ ቀድሜ ለአስራ አምስት ቀናት አዳማ ራስ ሆቴል በራሴ ወጪ ገብቼ ዝግጅት አደርጋለው። በ1985 ይመስለኛል ጋሽ መንግስቱ ወርቁ በዚያን ሰዓት መብራት ኃይል ቡድንን እያሰለጠነ ለዝግጅት አዳማ ራስ ሆቴል ይመለከተኛል። ‘ምን ትሰራለህ ?’ አለኝ። ‘አይ የአካል ብቃት ፈተና ስላለብኝ እየተዘጋጀው ነው’ አልኩት። በኃላ ‘እንዴይ የሆቴል ፌዴሬሽኑ ነው የሚከፍልህ ?’ አለኝ። ‘ኧረ በጭራሽ በራሴ ወጪ ነው’ አሉኩት። በጣም ተገርሞ አድንቆኝ ሄደ። ይህ ብቻ አይደለም ራሴን ለመጠበቅ እሁድ ጨዋታ ካለ ከሐሙስ ጀምሮ ከሚስቴ ጋር አልጋ እንለይ ነበር ፤ አቋሜን ለመጠበቅ ብቻ። ዳኝነት በጣም የምወደው በከፍተኛ ፍላጎት የምሰራው ሙያ ስለሆነ አክብሬው ኖሪያለው ዳኝነቱም በበዙ መንገድ አስከብሮኛል ፤ ህይወቴን ቀይሮታል። ለደከምኩበት እና ለለፋሁበትም ዳኝነቱ ከፍሎኛል።”

እግርኳሱን በገበያ ትርፋማ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን እንዳደረክ አውቃለው። እስቲ ከብዙ በጥቂቱ የሰራሀቸውን ስራዎች አጫውተኝ…

” ‘ከመቀበል ይልቅ ብትሰጥ ይበልጣል።’ የሚል የህይወት ፍልስፍና አለኝ። በዚህ ምክንያት የሀገሬን እግርኳስ ለመቀየር የተለያዩ ስራዎችን ሰርቻለው። የኢትዮጵያ እግርኳስ የሚቀየረው በእኔ ዕምነት በቢዝነስ ነው። በአውሮፓ የሚገኙ ሀገሮች በሙሉ እግርኳሱን የቀየሩት፣ ማሳደግ የቻሉት እግርኳሱን ወደ ገንዘብ በመቀየር ነው። ክረስቲያኖ ሮናልዶን ከፍተኛ ሚሊዮን ዶላር አውጥተው ክለቦች የሚያስፈርሙት ሜዳ ላይ እንዲጫወትላቸው ብቻ አይደለም። ከመልያ ፣ ከቴሌቪዥን ጭያጭ ያወጡትን ገንዘብ በእጥፍ ለማስገባት ነው። ስለዚህ እግርኳስ ቢዝነስ ነው። ይህን ለመስራት ትልቅ ፕሮጀክት እስከ ሁለት መቶ ሚልዮን ብር ገቢ የሚያስገኝ አዘጋጅቼ ነበር። ኢትዮ ፉትቦል የሚል መፅሔት አዘጋጅቼ አቅርቤም ነበት። ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት አትችልም። ራሱ ፌዴሬሽኑ ምን እንደፈለገ አላውቅም። ጥሩ እየሄደ ተኮላሸ እና ተውኩት። በመቀጠል ደግሞ አዕምሮዬ ፈጣን ስለሆነም የመብራት ኃይል ፣ የጉና እና የሌሎች ክለቦች ኤጀንት ሆኜ ሰራሁኝ። ስፖንሰር ማገናኘት ፣ ክለቡን ወደ ገንዘብ የመቀየር ስራዎችን እና አቅጣጫ የማሳየት ሥራ ሰርቻለው በዚህም ስኬታማ ነበርኩኝ። የታዳጊ ፕሮጀክት ስራም ደብረ ማርቆስ ሰርቼ ነበር። ለምሳሌ ምንያህል ተሾመ እና አዳነ ግርማ የኔ ልጆች ነበሩ። በስፖርት ውስጥ ያልስራሁት ስራ የለም። በዓለም ዋንጫ በመስቀል አደባባይ እስክሪን ተክዬ ጨዋታን አሳይ ነበር። በአፍሪካ ዋንጫ ሀገራችን ስትገባ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፌ የተለያዩ ገንዘብ ማግኛ ሰነዶች አዘጋጅቼ በስታድየሙ ዙርያ የማስታወቂያ ስራዎችን በመስራት ብሔራዊ ቡድኑ በገንዘብ እንዲጠናከር አድርጌአለው። መጨረሻ ላይ ግን ለሰራሁትን ስራ ዕውቅና ሳይሰጡኝ ቀሩ ፤ በጣም አዘንኩኝ። አስኮ ፕሮጀክትን ሄጄ የአካባቢውን ማኅበረሰብ አነሳስቼ ልጆቹ ምግብ እንዲያገኙ እና የተለያዩ ሥራዎች እንዲሰሩ አድርጌአለው ፤ በፊት ታዳጊዎቹ ልምምድ ሠርተው የሚመገቡት የለም ነበር።”

ወደ ንግዱ ዓለም ገብተህ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራህ ትገኛለህ እስቲ በተወሰነ መልኩ አጫውተኝ…

“አዝማምያውን ሳይ በእግርኳሱ የሚያድግ ነገር የለም። ታዳጊ ፕሮጀክት ላይ ሰራሁ ፤ ለውጥ የለም። ለሀገሬ እኔ ካገለገልኩት ሀገሬ የሰጠችኝ ይበልጣል። ምንም ነገር አልነበረኝም። ለራሴ ፕሮፖዛል ሠርቼ ባንክ የተለያዩ ድርጅቶች መኪና ሰጡኝ። ለማመን የሚከብድ የንግድ ስራ ጀመርኩ። ትልቅ የዘይት ፋብሪካ ከፍቼ እየተንቀሳቀስኩ ቆየው። አሁን ደግሞ ፍሬሽ አሳ አከፋፍላለው ፣ ሚናሮል ህንፃ ላይ ትልቅ አሳ ቤት ከፍቼ እየሰራው እገኛለው።”

አሁን ላሉት እና ወደፊት ዳኛ ለመሆን ለሚያስቡ ያለህ መልዕክት ምንድን ነው ?

“አንድ ፍልስፍና አለኝ ‘አንድ ነገር ስትሰራ የምትወደውን ስራ’ የሚል። ለገንዘብ ብለህ የምትሰራው ህይወትህን ይዞ ሊጠፋ ይችላል። ስለዚህ የዳኝነት ሙያን ይውደዱት። የስፖርቱ አባት ነኝ ፤ 47 ዓመት በዚህ ሙያ ሰርቻለው። የምመክራቸው የሚወዱትን ይስሩ ብዬ ነው። እየጠላኸው ሌላ ነገር አስበህ የምትሰራ ከሆነ ይዞህ ይጠፋል። ከወደድከው ግን ትልቅ ደረጃ ትደርሳለህ። አሰብ በከፍተኛ ሙቀት በቀን ሁለት ጨዋታ ማጫወት ፣ ስሜን ክብሬን ጠብቄ ያለምንም ኮሽታ ይሄን ያህል ዓመት ተወድጄ ተከብሬ ያለሁት ዳኝነትን ወድጄው በመስራቴ ነው። ሰው የዘራውን ነው የሚጭደው። ስለዚህ መጀመርያ የዳኝነት ሙያን ይውደዱት። ለሙያው የሚያስፈልገውን መስዕዋትነት ይክፈሉ ፣ በደንብ መዘጋጀት በግል ልምምድ መስራትንም ልምድ ያድርጉ። ለለፉት፣ ላፈሰሱት ላብ ወደፊት የሚገባቸውን ዋጋ ያገኛሉ።”

የቤተሰብ ህይወትህ እንዴት ነው ?

“ባለቤቴን የዛሬ 15 ዓመት በካንሰር ህመም በህይወት አጥቻታለው። ከእርሷ የወለድኳቸው ሁለት ወንድ እና አንድ ሴት ልጆች አሉኝ ፤ ሦስቱም ኑሯቸው በአሜሪካ ነው። የመጀመርያ ልጄ 33 ዓመቱ ነው ብሩክ ይባላል። ሉሲ ሁለተኛ ልጄ ህፃን እያለች ፖስተር መስራቷ ይታወቃል አሁን 22 ዓመቷ ነው ፤ አግብታ ወልዳለች። የመጨረሻ ልጄ ፊሊሞን ደግሞ 20 ዓመቱ ነው።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ የተጫዋቾች መሀን አይደለችም። የአፍሪካ ዋንጫ ለመግባት ሌላ 31 ዓመት መጠበቅ የለብንም። የእግርኳሳችን መሠረታዊ ችግር የአደረጃጀት እና የሲስተም ችግር ነው። በቅርቡ በፉትቦል ፖዘቲቭ አስተሳሰብ ማምጣት አለብን። ምክንያቱም የፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባል በኃይላንድ ከተጣላ ፣ ተጫዋቾች ከተጫዋች፣ አሰልጣኝ ከአሰልጣኝ ጋር እየተጋጨ እንዴት ለውጥ ይመጣል። ‘ይህን አሉታዊ ነገር ለመቀየር የሚቻለው በፖዘቲቭ አስተሳሰብ ነው’። በሚል አንድ ፕሮጀክት ቀርጫለው። በቅርቡ ወደ ስራ የምገባ ይሆናል። በዳኝነት ዘመኔ እስካሁን ድረስ አብረውኝ ያሉ ሁለት ጓደኞቼን በጣም የማከብራቸው ሰለሞን ዓለምሰገድ እና ዳኝነትን ሳቆም መለያዬን አውልቄ ፣ ካርዴን ሰጥቼ ያስረከብኩት ተተኪዬን ኮሚሽነር ተስፋዬ ኦሜጋ በጣም አመሰግናለሁ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ