5ኛው የቡና የቤተሰብ ሩጫ ዛሬ ታስቦ ውሏል

ለ5ኛ ጊዜ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ታጅቦ ታስቦ ውሏል።

ከ2008 ጀምሮ በየዓመቱ ሲከናወን የነበረው ይህ የቤተሰብ ሩጫ ዘንድሮ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መልኩን ቀይሮ ዛሬ ተከናውኗል። በተለይ ክለቡ ቀደም ብሎ ለማግኘት ያሰበውን ገቢ እንዳያጣ እንዲሁም ለደጋፊዎች የተሰጠውን 12 ቁጥር የሚወክል ታሪካዊውን ቀን (12-12-12) ላለማለፍ በታቀደ እቅድ ክለቡ 40 ሺ የመሮጫ ማሊያዎችን በመሸጥ መርሃ ግብሩን አዘጋጅቷል። በወረርሽኙ አስጊነት ምክንያት ደጋፊዎች በአካል ሳይሰባሰቡ ነገር ግን በልብ እና ሃሳብ አንድ ሆነው ያከናወኑት ይህ መርሃግብር የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ተከናውነውበት ታስቦ አልፏል።

በተለይ በዚህ ታሪካዊ ቀን መለያውን የገዙ 40 ሺ ደጋፊዎች በየአካባቢያቸው የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ እና የአቅመ ደካሞች የመደገፍ ሥራን ሲያከናውኑ ውለዋል። በተለይ በርከት ያሉ ደጋፊዎች በቀበና አካባቢ በሚገኝ ስፍራ ተሰባስበው የችግኝ ተከላ መርሃግብር ሲያከናውኑ ተስተውሏል። በተጨማሪም በርከት ያሉ የክለቡ ደጋፊዎች ስታደየም አካባቢ በሚገኘው የቀይ መስቀል ማኅበር ቅጥር ግቢ በመገኘት የደም ልገሳ አከናውነዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ከወጪ ቀሪ 4 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ባቀደው በዚህ ታሪካዊ ሩጫ ላይ የተሰበሰበው ገቢ ክለቡን በፋይናንስ ለማጠናከር እንደሚውል ተገልጿል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ