“ኅዳር አንድ ይጀመራል የተባለው ነገር ፌዴሬሽኑ በፍፁም የማያውቀው ነው” ባህሩ ጥላሁን የፌዴሬሽኑ ፅ/ቤት ኃላፊ

በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2013 የውድድር ዘመን ኅዳር አንድ ይጀመራል የሚሉ መረጃዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡ በርካታ የሀገራችን እግር ኳስ ተከታዮችም ይህ ጉዳይ እውነት ነው ወይ በማለት ወደ ሶከር ኢትዮጵያ ጥያቄውን አቅርበዋል፡፡ እኛም እየተባለ ያለው ነገር እውነት ነው ወይ በማለት ለፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ማምሻውን ጥያቄ አቅርበንላቸው ምላሹን በተከታዩ ሀሳብ ገልፀውልናል፡፡

“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለመንግሥት ውድድር እንደገና በሚጀምርበት ሁኔታ ላይ መልስ እየጠበቀ ነው ያለው። ሰነዶች አዘጋጅቶ እነዛም ሰነዶች በክለቦች እንዲታይ ተደርጓል። ቀጣይ የሚሰሩ ሥራዎች አሉ። ፍቃዱን በተመለከተ ከጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተወጣጡ ሙያተኞች ሄደው የሚመለከቷቸው ሜዳዎች ይኖራሉ። ይሄ ሁሉ ባልተደረገበት፤ መንግሥት ፍቃድ ባልሰጠበት ሁኔታ ህዳር አንድ ይጀመራል የተባለው ነገር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፍፁም የማያውቀው ጉዳይ ነው፡፡”

ማስታወሻ

በአንዳንድ ማኅበራዊ ገፆች ላይ ኅዳር አንድ ይጀመራል የሚለው መረጃ ከሶከር ኢትዮጵያ እንደወጣ ተደርጎ ሲገለፅ (ምንጭ – ሶከር ኢትዮጵያ እየተባለ ሲጠቀስ) ተመልክተናል። በዚህ አጋጣሚ በሶከር ኢትዮጵያ በኩል ይህን መሰል ዜና አለመሰራጨቱን ለመግለፅ እንወዳለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ