የሴቶች ገፅ | ቆይታ ከአረጋሽ ካልሳ ጋር…

በዛሬው የሴቶች ገፅ አምዳችን የመከላከያ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የሆነችው አረጋሽ ካልሳን ይዘን ቀርበናል።

በጋሞ ጎፋ ዞን ወይዳ ወረዳ ተወልዳ ያደገችው አረጋሽ እግርኳስን በተረጋጋ ስሜት ለመጫወት የሚያስችል ከባቢ ባይገጥማትም ውስጧን ብቻ አዳምጣ በልጅነቷ ኳስን ትጫወት እንደነበር ትናገራለች። የጨርቅ ኳሶችን በግሏ እና ከጓደኞቿ ጋር በመሆን እየሰራች እንደተጫወተችም ታስታውሳለች። በሰፈር ውስጥ እና በትምህርት ቤት ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግም ወደ ታላቅነት የምታደርገውን ጉዞ ‘ሀ’ ብላ ጀመረች። በቀጣይ የተወለደችበትን ወረዳ ወክላ በደረማሎ ከተማ ውድድር ስታደርግ ደግሞ ከአርባምንጭ በመጡ አሰልጣኞች ቀልብ ውስጥ ገብታ ወደ ፕሮጀክት ቡድን እንድትካተት ተደረገ። በአሰልጣኝ መኮንን መልማይነት አርባምንጭ በሚገኝ ፕሮጀክት እንድትካተት የሆነችው ተጫዋቿም አንድ ዓመት ከግማሽ በፕሮጀክቱ ታቅፋ ከቆየች በኋላ አርባምንጭን ወክላ ለክልል ውድድሮች ጨዋታ እንድታደርግ ምርጫ ደረሳት። ሃዋሳ ላይ ይህንን ውድድር ካደረገች በኋላም የኮፓ ኮካ ኮላ ውድድር ላይ ለመሳተፍ በተመሳሳይ ቡድን ተይዛ ወደ አዳማ አቀናች። በአዳማው ውድድር ላይ ድንቅ ብቃቷን ስታሳይ ደግሞ የኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ መልማዮች ዓይን ውስጥ ገባች። ከዛም ወደ አካዳሚው በመግባት ለ4 ዓመታት ቆይታ ካደረገች በኋላ ጉዞዋን ወደ መከላከያ አደረገች። በመከላከያም ዘንድሮን ጨምሮ ለሁለት ዓመታት ድንቅ ግልጋሎት እየሰጠች ነበር።

በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እያለች 2008 ላይ በአሰልጣኝ አሥራት አባተ አማካኝነት የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን እንድተቀላቀል የሆነችው አረጋሽ በጊዜው ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ጥሪ ቢደረግላትም በወቅቱ መጫወት አልቻለችም ነበር። ከዚያ በኋላ ግን በተለያዩ አሰልጣኞች በዋናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የእድሜ ቡድኖች ጥሪ እየቀረበላት ሃገሯን ወክላ መጫወት ቻለች።

ባለፉት ዓመታት ጥሩ እድገት እያሳየች የነበረችው ይህቺ የአስደናቂ ክህሎት ባለቤት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገችውን አጭር ቆይታ እንደሚከተለው እናቀርበዋለን።

የእግርኳስ አርዓያሽ ማነው/ናት?

በልጅነቴ የእግርኳስ አርዓያ አልነበረኝም። ምክንያቱም የተወለድኩት ገጠር አካባቢ ስለሆነ ኳስ የሚጫወቱ የሃገራችንንም ሆነ የውጪ ተጫዋቾች አላየሁም። ኳስን የመጫወት ፍላጎት ስለነበረኝ ብቻ ነው እግርኳስ ተጫዋች የሆንኩት።

ሊጉ ኮቪድ-19 ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ አረጋሽ ጊዜዋን በምን እያሳለፈች ነው?

እውነት ለመናገር ጊዜው መጥፎ ቢሆንም ችግሩ በውስጡ ይዟቸው የመጣቸው ጥሩ ነገሮች አሉ። ከምንም በላይ ደግሞ ችግሩ የቤተሰብ ጊዜን እንዲጨምር አድርጓል። ከዚህ መነሻነት እኔም ከቤተሰቦቼ ጋር ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው። በተጨማሪም በራሴ የልምምድ መርሐ-ግብሮችን አውጥቼ ስራዎችን እሰራለሁ። ከዚህ ውጪ ፊልም በማየት እና እረፍት በማድረግ ነው ጊዜዬን እያሳለፍኩ ያለሁት።በግልሽ ጥሩ ዓመት ያሳለፍሽበት ጊዜ መቼ ነው?

ምናልባት አካዳሚ እያለሁ። ከቡድኑ ጋር በዲቪዚዮን ዋንጫ ያነሳንበት ጊዜ ጥሩ ዓመት ነበረኝ። በግሌም የቡድኑ ኮከብ ተጫዋች ተብዬ ተመረጬ ነበር። እርግጥ እኔ ብቻ ሳልሆን ቡድኑ እራሱ ጥሩ ጊዜ ነበር ያሳለፈው።

አረጋሽ እግርኳስ ተጫዋች ባትሆን በምን ሙያ እናገኛት ነበር?

ከባድ ነው። ግን እግርኳስ ተጫዋች ባልሆን በሁለት ሙያ በአንዱ እገኝ ነበር። አንደኛው በቀለም ትምህርቴ ገፍቼ ትልቅ ደረጃ ደርሼ እገኝ ነበር። አልያም ደግሞ የንግዱን ዓለም ተቀላቅዬ ነጋዴ እሆን ነበር።

አብረሽ ተጣምረሽ መጫወት የምትፈልጊያት ተጫዋች አለች?

እውነት ለመናገር አብዛኞቹ የሃገራችን ተጫዋቾች አብረው ለመጫወት የሚመቹ ናቸው። አሁን ላይ ሆኜ ስም ባልጠራም ከሁሉም ጋር መጫወት ያስደስተኛል።

እሺ። በተቃራኒ ስትገጥሚያት የምትከብድሽ ተጫዋችስ ትኖር ይሆን?

በፍፁም። እስካሁን የከበደችኝ ተጫዋች የለችም።

በእግርኳስ የተደሰትሽበትን አጋጣሚ አውጊን እስኪ?

በእግርኳሱ ዘለግ ያለ ጉዞ ስላላደረኩ ብዙ አጋጣሚዎች የሉኝም። ግን ካሉት ውስጥ አካዳሚ የነበርኩባቸው ጊዜያት ያስደስቱኛል። በተለይ እዛ የነበረው የአብሮነት ጊዜ በጣም ደስ ይላል። ከምንን በላይ ደግሞ ዋንጫ ያገኘንበት እና እኔ ኮከብ ሆኜ የተመረጥኩበት ዓመት የተደሰትኩበት ጊዜ ነው። እንዳልኩህ ገናም ስለሆንኩ ይመስለኛል እንደዚህ አይነት የደስታ ክስተቶች ያላጋጠሙኝ። በፕሪምየር ሊጉ እንኳን ገና 2 ዓመት ብቻ ነው የተጫወትኩት። ወደፊት ግን ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ።

በእግርኳስ ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች የቅርብ ጓደኛሽ ወይንም ሚስጥረኛሽ ማነች/ው?

በእግርኳሱ ጥሩ ጥሩ ጓደኞች አፍርቼያለሁ። ግን በጣም ያቀረብኩት እና እንደ ሚስጥረኛ የማየው የለም። አላቅም ይህ ለምን እንደሆነ ግን ሚስጥረኛ የምለው ጓደኛ በእግርኳሱ የለኝም።

የግል ህይወትሽ ምን ይመስላል?

ለትዳር ገና ነኝ። ከቤተሰብ ጋር ነው እየኖርኩ ያለሁት።

አረጋሽ ምን የተለየ ባህሪ አላት? ብዙ ሰዎቸ የማያቁትን ባህሪሽን አጫውቺን?

አዲስ ከማገኘው ሰው ጋር በቶሎ ተላምዶ የመግባባት ችግር አለብኝ። ብዙ ሰዎችን ያልተረዱኝ ችግሬ ይሄ ነው። ከሰው ጋር በቀላሉ አልግባባም። በጣም ጊዜ ፈጅቼ ነው ከሰው ጋር የምግባባው። ግን ይህንን ባህሪዬን ተረድቶ ከመጣጥ ሰው ጋር በደንብ እቀራረባለሁ።

በመጨረሻ…?

በቅድሚያ እዚህ ደረጃ ያደረሰኝን ፈጣሪን ላመሰግን እፈልጋለው። በሁለተኛ ደረጃ ስወድቅ እያነሱ ስደክም እያበረቱኝ የነበሩትን ቤተሰቦቼን አመሰግናለሁ። በመቀጠል ከሃገሬ ወጥቼ በተሻለ የእግርኳስ ህይወቴን እንድጀምር ያደረጉኝን አሰልጣኝ አብዲ እና መኮንንን አመሰግናለሁ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: