“የዘመኑ ከዋክብት ገፅ” ከደስታ ደሙ ጋር…

በዛሬው ቆይታችን በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ከሚገኙ ተከላካዮች አንዱ ከሆነው ደስታ ደሙ ጋር ቆይታ አድርገናል።

በዚህ ወቅት በፕሪምየር ሊጉ ካሉት ምርጥ የመሀል ተከላካዮች አንዱ ነው። በመሐል ተከላካይነት እና በመስመር ተከላካይነት መጫወት የሚችለው እና ሲበዛ ቁጥብ መሆኑ የሚነገርለት ዝምተኛው ደስታ ደሙ እግርኳስ በጀመረባቸው ዓመታት የነበረው ተሰጥኦ እና የመጫወት ፍላጎት በቀጣይ ትልቅ ደረጃ እንደሚደርስ አመላካች ነበሩ። እንደ ብዙዎች ግምትም ተጫዋቹ አሳዳጊ ክለቡ ሙገር ሲሚንቶን ከለቀቀ በኋላ በደደቢት እና ወልዋሎ እንዲሁም ዘንድሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ያሳለፋቸው ድንቅ ዓመታት ምስክሮች ናቸው።

በ2005 በአዳማ በተደረገ ውድድር ጥሩ ብቃት በማሳየት በሙገር ሲሚንቶ መልማዮች ዓይን ውስጥ የገባው ይህ ተጫዋች ከቡድኑ ጋር እስከ ቆየበት 2008 ድረስ በታዳጊ ቡድን እና በዋናው ቡድን ምርጥ ብቃቱን አሳይቷል። በ2009 ወደ ደደቢት አምርቶ በሰማያዊዎቹ ቤት ለሁለት የውድድር ዓመታት ዓመታት በመሐል እና በመስመር ተከላካይነት በመጫወትም በ2012 ወደ ወልዋሎ በማቅናት በግሉ ምርጥ ዓመት አሳልፏል። በተቋረጠው የዘንድሮ የውድድር ዓመት ደግሞ ከቀዝቃዛው አጀማመር አንሰራርቶ ቀድሞ በሚታወቅበት የመስመር ተከላካይ ቦታ ላይ በፈረሰኞቹ ቤት ጥሩ ጊዜያት አሳልፏል።

በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በሦስት የዕድሜ እርከኖች የኢትዮጵያን ማልያ መልበስ የቻለው ደስታ በ2008 ከሀያ ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን መጫወት ጀምሮ በኋላም በኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማሳየት ከማሊ ጋር በነበረው ጨዋታም ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል።

የዋናው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መደበኛ ተመራጭ ለመሆንም ጊዜ ያልወሰደበት ደስታ ደሙ ጋር ያደረግነው ቆይታን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ወቅቱን የሚያሳልፍበት ሁኔታ

አብዛኛው ጊዜዬን ቤት ነው የማሳልፈው። በወረርሺኙ ምክንያት ጊዜው ብዙ እንቅስቃሴ እንድታደርግ ስለማይፈቅድ ቤቴ ውስጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ነው እያሳፍለኩ ያለሁት።

እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን

ከእግር ኳስ ውጭ አስቤ አላቅም። ግን ሹፌር የምሆን ይመስለኛል።

የማይረሳት ጎል

ብዙ የማልረሳቸው ጎሎች አሉኝ። ግን ደደቢት እያለሁ ሲዳማ ላይ ያስቆጠርኳት ግብ እና ሙገር እያለሁ ወልዲያ ላይ ከርቀት ያስቆጠርኳትን ግብ አልረሳቸውም።

በተቃራኒ ሲገጥመው የፈተነው ተጫዋች

ሊጋችን ላይ ብዙ አስቸጋሪ ፈጣን ተጫዋቾች አሉ። ግን ይህ ያኽል አስቸግሮኛል የምለው ተጫዋች የለም።

ከሱ ጋር ሲጣመር ምቾት የሚሰጠው ተጫዋች

ከማንኛውም ተጫዋች መጫወት እችላለሁ። ግን ይበልጥ ከአስቻለው ታመነ ጋር ስጣመር ምቾት ይሰማኛል።

ከእግርኳስ ውጭ የሚያዝናነው ነገር

ይህ ያዝናናኛል ማለት አልችልም። ብዙም ተመስጬ ጊዜዬን ማሳልፍበት ነገር የለም። ብዙ ግዜዬን ቤት ውስጥ ባሳልፍ ደስ ይለኛል።

በእግርኳስ የቅርብ ጓደኛው

በክለብ ውስጥ ያሉት ሁሉም እግባባቸዋለው።
ከሁሉም ጋር ቅርርብ አለኝ። በአሁኑ ሰዓት በጣም ቅርቡ ጓደኛዬ ግን ሄኖክ አዱኛ ነው።

አርዓያው

ኳስ ስጀምር ታዳጊ ላይ አርዓያዬ የነበሩ ብዙ አሉ። አሁን ግን መጀመርያ የመስመር ተከላካይ ስለነበርኩ ሥዩም ተስፋዬ ነው አርዓያዬ።

በእግር ኳስ ሕይወቱ በግሉ ምርጥ የሚለው ዓመቱ

ዘንድሮን ጨምሮ ብዙ ዓመታት አሉ። አንድ ምረጥ ካልከኝ ግን ባለፈው ዓመት ከወልዋሎ ጋር በግሌ ጥሩ ዓመት ነው ያሳለፍኩት።

የተደሰተበት እና ያዘነበት ወቅት

በ2008 ሙገር እያለሁ የመጨረሻ ሳምንት ላይ ከመከላከያ ጋር ጨዋታ ነበረን። ከመውረድ ለመትረፍ ማሸነፍ እና የሌሎች ውጤት መጠበቅ ነበረብን፤ ከዛ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግብ አስቆጠርን። በሌላ ሜዳ የነበረው ኤሌክትሪክ ከወላይታ ድቻ ጨዋታ ውጤት ነግረውን ተርፈናል ብለን ጨፈርን ሜዳውን እየዞርን ደስታችን ገለፅን። ከዛ በኃላ ስንሰማ ግን ባለቀ ሰዓት ግብ ተቆጥሮ እኛ ወረድን፤ ይህን አጋጣሚ አልረሳውም። የተደሰትኩበት ደሞ መጀመርያ ብሔራዊ ቡድን የተመረጥኩበት አጋጣሚ ነው።

ወደ ጨዋታ ሲገባ ምን የተለየ ልምድ አለው?

ብዙ ልምድ የለኝም። ግን ሁሌ ከጨዋታ በፊት ፀሎት አደርጋለሁ።

የጊዜው የኢትዮጵያ ምርጡ ተጫዋች ማነው?

በጣም በጣም ከባድ ጥያቄ ነው። ግን ለኔ የጊዜው ምርጥ ተጫዋች አስቻለው ታመነ ነው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ