ሶከር ታክቲክ | ከፍተኛ ጫናን መቋቋም የሚችሉ ተጫዋቾችን የመጠቀም ስልት

አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡

ጸሃፊ – ሃይኮ ሰይጁሮ


ትርጉም – ደስታ ታደሠ

ወደ ተጋጣሚ ክልል እጅጉን ተጠግቶ በሚከወነው ተጭኖ የመጫወት ዘይቤ ወይም High-Press
ስኬታማ የሆኑት እና ተወዳጅነትን ያተረፉት የፔፕ ጓርዲዮላው ባርሴሎና፣ ባየርሙኒክ እና ማንችስተር ሲቲ፥ የየርገን ክሎፑ ቦሩሺያ ዶርትሙንድ እና ሊቨርፑል እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የጀርመኑ አር.ቢ.ላይብዚሽን የመሳሰሉት ቡድኖች ይህ የአጨዋወት ሥልት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ መነሻ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ቡድኖች በመጫወቻ ሜዳው ሁሉም ክፍሎች ተጋጣሚዎቻቸውን ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳርፋሉ፡፡ ይህም ሁኔታ የጨዋታ ጫናን መቋቋም የሚችሉ ተጫዋቾች አስፈላጊነታቸው ከፍ እንዲል አድርጓል፡፡

በእግርኳስ ጨዋታ አንዱ ቡድን ሲያጠቃ ሌላኛው መከላከሉ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ በሥረ-መሰረታዊ ደረጃ ማጥቃት ማለት በቀላሉ ጎል ለማስቆጠር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጫናን የማምለጥ ጥበብ ነው፡፡ መከላከል ደግሞ ግብ እንዳይቆጠር ለማድረግ ወይም ኳስን መልሶ ለማግኘት ጫናን በተጋጣሚ ላይ የማድረስ ሒደት ነው፡፡ ስለዚህም ለሚያጠቃ ቡድን ጫናን የሚቋቋም ተጫዋች መያዝ ዋጋ የማይተመንለት ውሳኔ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ያለእነዚህ ተጫዋቾች የተቃራኒ ቡድንን ጫና ተቋቁሞ ጎል ማስቆጠር እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡

                   ጫናን መቋቋም

በቀላል አገላለጽ ለማስቀመጥ ያህል ጫናን መቋቋም ማለት በተጋጣሚ ቡድን ጫና ውስጥ ሆኖ እንኳን ኳስን ተቆጣጥሮ የመቆየት ብቃት ማለት ነው፡፡

በመሰረቱ ሁለት የተለያዩ ጫናን የመቋቋም ዓይነቶች አሉ፡፡
1. በጋራ ጫናን መቋቋም
2. በተናጠል ጫናን መቋቋም

በጋራ ጫናን የመቋቋም ሒደት አንድ ቡድን የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በሚወስድ ጊዜ በሚኖረው እንቅስቃሴያዊ አደረጃጀት ላይ ይወሰናል፡፡ በዚህ ቅጽበት ተጋጣሚ ቡድን ስኬታማ ተጭኖ የመጫወት እንቅስቃሴ ለማድረግ ይቸገራል፡፡

ከላይ የሚታየው ምስል ኬቨን ደብርይነ ከቡድኑ ጋር በምን መልኩ እንደተቀናጀ ያመለክታል፡፡ ፖግባ እግር በእግር እየተከታተለው ኳሱን ሊቀማው ቢጥርም አልሰመረለትም፡፡ ይሁን እንጂ ለዚህ ፅሑፍ ዓላማ ሲባል በግል ወይም  በተናጠል ጫናን መቋቋም የሚችሉ ተጫዋቾች አያያዝና አስፈላጊነታቸውን እናነሳለን፡፡      

ጫናን የሚቋቋሙ ተጫዋቾች ብቃት

በእግርኳስ በተመሳሳይ ቦታ በሚጫወቱ ተጫዋቾች መሃል እንኳን የብቃት ደረጃቸው ለየቅል የሆኑ ተጫዋቾች አሉ፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ተጫዋቾች ጫናን የሚቋቋሙ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የተለያዩ ቴክኒካዊ ብቃቶች አሉ፡፡ እነዚህም ኳስን በአግባቡ መቆጣጠር፣ በጠባብ ቦታዎች ኳስን ወደፊት መግፋት እንዲሁም ጠንካራ የአካል ብቃትና ፈርጣማ ተክለሰውነት መገንባት፡፡ ዝላታን ኢብራሂሞቪች እና ሮሜሎ ሉካኩ ያሉት ተጫዋቾች በግዙፍ ተክለ ቁመናቸው የሚታወቁ ቢሆኑም ጫናን በመቋቋም ባሕሪያቸውም ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ ከጫና ለማምለጥ ታስቦባቸው የሚደረጉ ረጃጅም ቅብብሎች በተጻራሪው ጫና ፈጠሪ ሆነውም ይገኛሉ፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት ረጃጅም ቅብብሎች በባህሪያቸው እንዲደርሱ የሚታለምላቸው ተጫዋቾች አልያም ቦታዎች ላይ ለመድረስ ሰፋ ያለ ጊዜ ይወስዳሉ፡፡ ስለዚህም ተጋጣሚ ቡድን የኳሱ ተቀባይ ተጫዋች ላይ  ጫና ለማድረስ በቂ ጊዜ እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡ ነገርግን ተቀባዩ የሚደርስበትን ጫና ተቋቁሞ ኳስን በተገቢው መንገድ መያዝ ከቻለ በንጽጽር ከእርሱ በተሻለ ነጻ ለሆነ የቡድን አጋሩ ኳሱን አቀብሎ የጨዋታውን ሒደት ማስቀጠል ይቻላል፡፡ ፔፕ ጓርዲዮላ ቀደም ባለው ጊዜ የተናገረው ጥሩ አባባል አለ፡፡ ታክቲሺያኑ አሰልጣኝ ስለ እንግሊዛዊው አጥቂ የሰጠው አስተያየት የሚከተለውን ይመስላል፡፡

” ተጫዋች በእግሩም በጭንቅላቱም የሚሰራውን ያውቃል፡፡” የእርሱ አንደኛው ምርጡ ብቃት ከሌሎች ጋር ተቀናጅቶ መጫወት ነው፤ የተለያዩ ዲፓርትመንቶችንም ማገናኘቱ (Link-up play) ነው፡፡ በተጋጣሚ የግብ ክልል የሚቆመው ሳጥኑ ውስጥ ለሚጣሉ ተሻጋሪ ኳሶች ብቻ እንዳልሆነ ይረዳል፡፡ ይልቁንም የጨዋታውን ፍሰት እንዴት ማስቀጠል እንዳለበት ይገነዘባል፡፡ እርሱ በአየር ላይ ኳስን አንድ ሺህ ጊዜ ሊያገኛት ይችላል፡፡ሁልጊዜም ደግሞ ይይዛታል፡፡ ነገሩ ቀላል ይመስላል፤ ግን በጣም ጥቂት አጥቂዎች ብቻ ናቸው ይህን መከወን የሚችሉት፡፡ ጭራሹኑ ከሌሎች ጋር መጫወት የማይችሉ አጥቂዎች አሉ፡፡ ሌሎች አጥቂዎች ደግሞ አጨዋወታቸው ከሌሎች የተለየ የሚመስላቸውም ይኖራሉ፡፡ ይህ ግን ሜዳ ላይ የተለጠጠ ቡድን እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ከዚህ አንጻር እንግሊዝ ታድላለች፤ ክራውችን ይዛለች፡፡” ብሎ ፔፕ ጓርዲዮላ ስለ ፒተር ክራውች ተናግሮ ነበር፡፡

በከፍተኛ ደረጃ ጫናን የሚቋቋሙ ተጫዋቾች ከቴክኒካል ክህሎት ውጪ አንደኛው ብቃታቸው መረዳት ወይም መገንዘብ ነው፡፡ ለቡድናቸው ቅጽበታዊ ነገርግን ምርጥ ውሳኔ እንዲወስኑ የሚያስችላቸው ዙሪያቸውን የመረዳት ብቃት፣ ክፍት ቦታ ላይ ላለ የቡድን አጋር ማቀበል ወይም ከጫና ውስጥ ገፍቶ መውጣት ሊሆን ይችላል፡፡ 

ይቀጥላል…


የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ