ለቀጣዩ የውድድር ዓመት የሚያገለግሉ ስታዲየሞች እና መሠረተ ልማቶች እየተገመገሙ ይገኛሉ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ አስራ ሰባት ስታዲየሞችን የመገምገም እና ሌሎች ተዛማጅ ግምገማ የማካሄድ ሥራ ከትናንት ጀምሮ እየከወነ ይገኛል።

የ2013 የውድድር ዓመት ውድድሮችን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ለማካሄድ ይረዳ ዘንድ ያለፉትን ሦስት ወራት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን እና ጤና ሚኒስቴር ጋር ምክክር በማድረግ በርካታ ሀሳቦችን ያዘለ የፕሮቶኮል ሰነዶችን አዘጋጅቶ ከሙያተኞች እንዲሁም በዋናነት የሚመለከታቸውን ክለቦች ጠርቶ በተዘጋጀው ፕሮቶኮል ላይ ውይይት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በሰነዱ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል ክለቦች ከዚህ ቀደም በየከተማው ተዟዙረው ከመጫወት ይልቅ ጥቂት በተመረጠ ሜዳ ላይ ማከወናወን የሚለው ይገኝበታል፡፡እነኚህን ሜዳዎች ገምግሞ ለመመርጥ ከትናንት (ረቡዕ) ጀምሮ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ ከጤና ሚኒስቴር እና ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የተውጣጡ ሦስት ኮሚቴዎች እያንዳንዳቸው አምስት አምስት አባላት ያሉት ባለሙያዎችን በማቀፍ ወደ የተመደቡበት ከተማ በመሄድ ግምገማ ማድረግ ጀምረዋል፡፡

ትናንት እና ዛሬ አራት ስታዲየሞች የታዩ ሲሆን የድሬዳዋ ስታዲየም፣ የሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ፣ የጎንደር እና የአዲስ አበባ ስታዲየሞች በተዋቀረው ኮሚቴ አማካኝነት ግምገማው ተደርጎባቸዋል፡፡ በቀጣዮቹ አንድ ሳምንት ቀናት ቀሪ ስታዲየሞች የሚገመገሙ ሲሆን ከሜዳው ባለፈ በከተማው ውስጥ ያሉ ተጨማሪ መሠረተ ልማቶች በግምገማው እንደሚካተት ሰምተናል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት በመስፈርትነት ከሚያዙ ጉዳዮች መካከል የመጫወቻ ሜዳው እና ለጥንቃቄ ያለው ምቹነት፣ በቂ የመለማመጃ ሥፍራዎች፣ በከተማው የሚገኙ በቂ የጤና ባለሙያዎች፣ ለክለቦቹ አባላት ፈጣን የጤና ምርመራን ስለማድረጋቸው እንዲሁም ሜዳዎች ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ሊያስተናገዱ ስለሚችሉ ስለሚደረግላቸው እንክብካቤ ከሚጠቀሱት የግምገማ መስፈርቶች ሆኖ ቀርቧል። በሌላ በኩል ተጫዋቾች በስታዲየም በሚገኙበት ጊዜ ቀደም ያለ የጤና ምርመራ ማድረጊያ ክፍሎች በከተማው ውስጥ የሆቴል እና የተጫዋቾች በቂ ማረፊያዎች በዋናነት በኮሚቴው እየተገመገሙ የሚገኙ ናቸው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!