የዳኞች ገፅ | ሩቅ የሚያልመው ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለሥላሴ

ትውልድ እና እድገቱ መቐለ ከተማ ነው። ብዙም ካልገፋበት የተጫዋችነት ሕይወቱ በጊዜ ተገልሎ ወደ ዳኝነት ዓለም በመግባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊጉ ላይ ካሉ ጥሩ ዳኞች አንዱ መሆን ችሏል። ከሁሉም የሙያ አጋሮቹ ተግባቢ እና ሞያውን አክባሪ መሆኑ የሚነገርለት አማኑኤል የዳኝነት ሕይወቱ፣ የኢትዮጵያ ዳኞች ፈተና እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኃል።


የዳኝነት አጀማመርህ እንዴት ነው?

ዳኝነት በ1994 ነው የጀመርኩት። ዓዲግራት ላይ የተሰጠው ስልጠኛ ወስጄ በቀጣይ ዓመት ዳኝነት ጀመርኩ። የመጀመርያ የዳኝነት ዓመታት ጥሩ ነበሩ። ብዙ ስልጠናዎች ወስጄ ራሴን ለማሻሻል ጥረት አደርግ ነበር። በዛ ምክንያት ደግሞ ቶሎ ነው ወደ አንደኛ ደረጃ ዳኝነት ያደግኩት። ይህ የሆነው 1996 ነው።

ዳኛ ለመሆን ያነሳሳህ ነገር ምንድነው?

ዳኛ ለመሆን ብዙ ነገር አነሳስቶኛል። እግርኳስ ተጫዋች ነበርኩ፤ ከዛ በኃላ ግን የነበረው ሁኔታ ደስተኛ ስላላደረገኝ ቶሎ ነው ከእግር ኳስ የተገለልኩት። በዘጠናዎቹ መጀመርየ ጉና እና ትራንስ የወዳጅነት ጨዋታ ሲያደርጉ አጫውታቸው ነበር። የጉና ተጫዋች የነበረው ዳንኤል ፀሀዬ ና ዳኘን ብሎኝ ሄጄ አጫውታቸው ነበር። በዛ ሰዓት ዳንኤል ፀሀዬ በጣም የማደንቀው ተጫዋች ነበር። ካጫወትኳቸው በኃላ በጣም ጎበዝ ነህ ስልጠና ውሰድ አለኝ። ከዛ ስልጠና ወስጄ ሙሉ ለሙሉ ወደ ዳኝነት ገበሁ።

ወደ ዳኝነት እንድትገባ ምክንያት የሆኑት ዳኞች ካሉ ?

አዎ በጣም ብዙ ብቃት ያላቸው ዳኞች ነበሩ በሰዓቱ። አንዱ ምሑር ኃይለ ነው፤ በጣም የምወደው የማደንቀው ዳኛ ነው። የነበረው ብቃት፣ ተሰሚነት እና አቅም በጣም የሚገርም ነው። ከምሑር ኃይለ ውጭም ዓለም ወኸለ የማደንቀው ዳኛ ነበር።

መጀመርያ የወሰድከው ስልጠና መቼ ነበር?

መጀመርያ የወሰድኩት ስልጠና 1994 በዓዲግራት የወሰድኩት ስልጠና ነው። ከዛ በኃላ ደግሞ ከሁለት ዓመት በኃላ 1996 የአንደኛ ደረጃ ስልጠና ወሰድኩ። ከ2007 ጀምሮ ደግሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ ስልጠና ወስጄ ኢንተርናሽናል ዳኞ ሆንኩ። በየዓመቱ ግን የአቅም ማሳደጊያ ስልጠናዎች ነበሩ። ከዛ ውጭ አቅሜን ለማሳደግ በግል የማደርጋቸው ነገሮች ነበሩ።

የመጀመርያ የዳኝነት ዓመታት ፈተናዎች ምን ይመስላሉ?

የዳኝነት ሞያ በጣም ከባድ ነው፤ ብዙ ፈተናዎች አሉት። በተለይም መጀመርያ አከባቢ ለሁሉም ጀማሪ ዳኛ የሚያጋጥሙት የተለመዱ ፈተናዎች አሉ። በስፖርተኛው ዘንድ ተቀባይነት ማጣት እና አንተን አሳንሶ የማየት ነገር ይበዛል። ለምንድነው ይህን ሞያ የመረጥኩት እስክትል ድረስ ፈተናዎች ሊደራረቡ ይችላሉ። በመጀመርያው የዳኝነት ጊዜዬ የገጠሙኝም ተመሳሳይ ችግሮች ናቸው። በኃላ ግን በብቃትና የሞያ ሥነ-ምግባር ጠብቄ ሁሉንም ፈተናዎች በብቃት አልፍያቸዋለው። እግርኳስ ተጫዋች ስለነበርኩ ምን አስቦ ነው ይህ ያደረገው የሚለውን በደምብ ስለማውቀው ሜዳ ላይ ጥሩ ለመሆን ብዙ ጊዜ አልወሰደብኝም። ከዛ ይልቅ ግን ውጭ የሚገጥሙኝ ፈተናዎች ትንሽ ከባድ ነበሩ።

የመጀመርያ ያጫወትከው ጨዋታ ታስታውሰዋለህ?

መጀመርያ መቐለ እንዳ ፀባ ነው ማጫወት የጀመርኩት፤ የቀበሌ ጨዋታዎች በማጫወት ነው የጀመርኩት። በብሔራዊ ሊግ ደረጃ ደግሞ የመጀመርያው ጨዋታዬ በ1999 ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ ከባቱ ከነማ በማጫወት ነው የጀመርኩት። በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ደግሞ በ2000 አዲስ አበባ ስታዲየም ንግድ ባንክ ከ ሀረር ቢራ በማጫወት ነው የጀመርኩት። እንደውም በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር። ከሚድያዎችም ሙገሳ ደርሶኝ ነበር። መጀመርያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ስመደብ የዳኞች ሰብሳቢ ዓለም ተፀቤ ነበር፤ አዲስ አበባ ላይ ነው የመደብኩህ ሚድያዎች ብዙ ደጋፊ ያለው ሜዳ ነው ጥሩ ካጫወትክ እሰየው ካልሆነ ግን መጥፍያህ ነው የሚሆነው ሲለኝ በደምብ ተዘጋጅቼ ሄድኩ። በጣም በጥሩ ሁኔታ መርቼ አድናቆትም ተቸረኝ።

የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ መቼ ነው ያገኘኸው?

ኢንተርናሽናል ዳኛ በ2007 ነው የሆንኩት። ግን እንደሚፈለገው ብዙ ጨዋታዎች አልዳኘሁም። በብሩንዲ አዘጋጅነት የተካሄደው ሴካፋ ከ17 ዓመት በታች እስከ ግማሽ ፍፃሜ አጫውቻለው። አራተኛ ዳኛ ሆኜም ሄጃለው፤ በዋና ዳኝነትም ከሀያ ዓመት በታች ጨዋታዎች አጫውቻለው። ኢንተርናሽናል ዳኝነት ላይ ብዙ ፈተናዎች አሉ። ቅድም እንዳልኩህ የራሳችን ችግር እንዳለ ሆኖ እንደሚፈለገው የሚያግዘንም የለም። አሁን በዓምላክ በራሱ ጥረት ነው እዚ ደረጃ ላይ የደረሰው። ለስም ሀያ ሁለት ዳኞች አለን። ግን በተለያየ ችግሮች በካፍ ውድድሮች ብዙም ተሳትፎ የለንም።

ካጫወትካቸው ጨዋታዎች ከባዱ የቱ ነበር ?

ብዙ ከባድ ጨዋታዎች ይገጥሙኛል። አብዛኛው የሊጉ ጨዋታም ቀላል የሚባል አደለም። በ2005 ግን ደደቢት የሊጉ ሻምፒዮን በሆነበት ዓመት ደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ያደረጉት ጨዋታ በጣም ከባድ ጨዋታ ነበር። ጨዋታው ምንም እንኳ ደደቢት አራት ለአንድ ቢያሸንፍም ድባቡ እና ጨዋታው ከባድ ነበር።

ባንተ ዕይታ የኢትዮጵያ ዳኞች ፈተና ምንድነው ?

ፈተናዎቹ ተዘርዝረው አያልቁም። በተለይም በቅርብ ዓመታት ፖለቲካው እና እግር ኳስ ተቀላቅሎ ፈተናዎቹ ከባድ አድርጎብናል። ያደረግነው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ወደ ሌላ እየተተረጎመ ችግር ፈጥሮ ነበር። ማኅበራችንም ሞያውን እስከመተው ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። ሜዳ ላይ የሚፈጠር ነገር ብዙም ከባድ አይሆንም። ስፖርተኞችም በስነ-ምግባር ረገድ ብዙ ክፍተቶች ነበሩባቸው። ዘንድሮ ግን ሊጉ እስኪቋረጥ ድረስ ብዙ መሻሻሎች ነበሩ በሁሉም በኩል።

በሀገራችን የዳኞች አቅም ላይ ብዙ ጥያቄ ይነሳል። በዚ ጉዳይ ላይ ምን ሀሳብ አለህ ?

እንዲ ተጋኖ የሚወራ የዳኞች አቅም ማነስ አለ ብዬ አላስብም። ከዛ ይልቅ ዳኞቻችን በምን ሁኔታ ሆነው ነው እየሰሩ ያሉት ብለን እስኪ እናስብ። ምቹ ባልሆኑ ሜዳዎች፣ ምንም ዋስትና በሌለባቸው ሁኔታዎች፣ በቂ ከለላ በማያገኙበት ሁኔታና የፖለቲካ ውጥረት በተቀላቀለባቸው ጨዋታዎች መሐል እየሰሩ እንዴት ይህን ያክል ተጋኖ የአቅም ችግር አለባቸው ተብሎ ይነገራል። እነ በአምላክ ተሰማ ሊድያ ታፈሰ አይነት በአፍሪካ ደረጃ ቁንጮ የሆኑ ጠንካራ ዳኞች አሉን እኮ።

በዳኝነት አሁን ሆነህ ስታስበው ይህ ስህተት ነበር ብለህ የምታስታውሰው ውሳኔ አለ ?

ብዙም የለም። አንዳንድ ጥቃቅን ስህተቶች ይኖራሉ። የሞያ ጓደኞችህ ይሄ እንዲህ ቢሆን ብለው የሚነግሩህ ከዛ ውጭ ግን ብዙም የለም። ለምን መሰለህ ወደ ሜዳ ስገባ ለህሊናዬ ብዬ ነው ገለልተኛ ሆኜ ነው የምገባው በህሊናዬ አልደራደርም። ሰው ነኝ፤ ሰውኛ ስህተት ልሳሳት እችላለው። አስልቼ ግን ወደ ሜዳ አልገባም። ወደ ሜዳ ስገባ በጣም ተረጋግቼ ነው የምመራው።

ከጨዋታ በፊት የተለየ ልምድ አለህ ?

አዎ ምደባ ሲነገረኝ ለጨዋታ በደምብ እዘጋጃለው። ለቡድኖቹ አጨዋወት የሚሆን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አደርጋለሁ። የተጫዋቾቹ ፀባይን ለማጥናት እሞክራለሁ። ሁሉም ዳኞቻችን በዛ መንገድ ነው የሚዘጋጁት። መረጃዎችም እንለዋወጣለን።

የኢትዮጵያ ዳኝነት በምን ደረጃ ይገኛል ትላለህ ?

በጥሩ ደረጃ ነው የሚገኘው። በተለይም ትልቅ ደረጃ ላይ ያሉት ዳኞቻችን እነ በዓምላክ ተሰማ ፣ ሊዲያ ታፈሰ እና ተመስገን ሳሙኤል የሚያጫውቷቸው ጨዋታዎች ስታይ ዳኝነት በሃገራችን ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለ ትገነዘባለህ። በአፍሪካ ደረጃ ያለን ተቀባይነት በጣም ጥሩ ነው። ክለቦች የኢትዮጵያ ዳኛ ሲመደብላቸው በጣም ነው ደስ የሚላቸው። ሁሉም ዳኞቻቸን ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያሉት።

ራስህንስ በየትኛው ደረጃ ነው የምትመድበው ?

አንድ ዳኛ የሚያቅደው ደረጃ ላይ ደርሻለው፤ ማለቴ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆኛለው። እንደምፈልገው ዓይነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ግን ገና አልሆንኩም። በኢትዮጵያ ደረጃ ግን እግዚአብሔር ይመስገን ጥሩ ደረጃ ላይ ካሉት ዳኞች አንዱ ነኝ ብዬ አስባለሁ። ለቀጣይም ያቀድኩት ነገር ለማሳካት በሁሉም ረገድ ጠንክሬ መስራቴን እቀጥላለሁ።
በኢንተርናሽናል ደረጃ ብዙ ተሳትፎ እንዳይኖረን የግላችን ችግሮች ቢኖሩም ከኢትዮጵያ በሴካፋ እና ካፍ ብዙ ተወካይ ስለሌሉን ብዙ ዕድል እንዳናገኝ ሆኗል።

ለጀማሪ ዳኞች ምን ትመክራለህ ?

መጀመርያ የሞያ ፍቅር ይኑራችሁ ነው የምለው። በዳኝነት የመጀመርያ ዓመታት ብዙ ፈተናዎች አሉ። ፈተናዎቹን በብቃት ለማለፍ በሁሉም ረገድ ራሳችሁን ዝግጁ አድርጉ። ከዛ ውጭም ከሁሉም ነገር ከፖለቲካ እና ተመሳሳይ ነገሮች ነፃ መሆን ይኖርባችኋል። ስለ ዳኝነት ህጎች ለማወቅ ጥረት አድርጉ፤ በአካል ብቃትም ሁልጊዜ ብቁ ለመሆን ሥሩ ነው የምለው።

ከዳኝነት ውጪ በምን ሞያ ላይ ተሰማርተሃል?

አሁን ጎን ለጎን የግል ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነኝ። ከባለቤቴ ጋር ሆኜ በንግድ ለመስራት ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ።

የቤተሰብ ሁኔታህ ምን ይመስላል?

ባለ ትዳር እና የአንድ ሴት ልጅ አባት ነኝ። በዚህ አጋጣሚ ባለቤቴን አምለሰት ዘርዑን ማመስገን እፈልጋለው፤ በሁሉም ነገር ታግዘኛለች።

በመጨረሻ …?

መጀመርያ እዚ ደረጃ ለመድረሴ እግዚአብሔርን አመሰግናለው። ቀጥሎ ደግሞ በዚ ሞያ እገዛ ያደረጉልኝን ሁሉም አመሰህናለሁ። በተለይም አንገሶም ካሕሳይ እና ለሁሉም የሞያ አጋሮቼ ለእነ ሊዲያ ታፈሰ ሽዋንግዛው ተባበል እና ሌሎች በጣም ማመስገን እፈልጋለው። በተጨማሪም ለሁሉም ጀማሪ ዳኞች ጠንክራቹ ሥሩ ራሳችሁን ብቁ ካደረጋቹ ሁሉም ነገር ቀላል ነው ማለት እፈልጋለው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!