“ከፋሲል ውጭ የትም አልሄድም ” ሱራፌል ዳኛቸው

በፋሲል ከነማ የተሳኩ ድንቅ የሁለት ዓመት ቆይታ በማድረግ ለተጨማሪ ዓመታት ለመቆየት ቅድመ ስምምነት ያድረገበትን ምክንያት ሱራፌል ዳኛቸው ይናገራል።

የአዳማ ከተማ ፍሬ የሆነው ሱራፌል በ2010 ክረምት ነበር አዳማ ከተማን በመልቀቅ ወደ ፋሲል ከነማ ያመራው። በሁለት ዓመት የዐፄዎቹ ቆይታም ከቡድኑ ጋር የጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ከማንሳቱ ባሻገር የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል። ዘንድሮ ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ከዐፄዎቹ ጋር ለተጨማሪ ዓመት ለመቆየት ተስማምቷል። ከክለቡ ጋር ለመጫወት ከተስማማ በኃላ ወደ ሌላ ክለብ ይሄዳል ወይ የሚል የብዙዎች ደጋፊዎች ሥጋት እና ጥያቄ ሆኗል። ይህን ተከትሎ ሱራፌል ከፋሲል ጋር ለመጫወት የተስማማበትን ሁኔታ እና ወቅታዊ ነገሮችን አስመልክቶ ተጫዋቹ እና ወኪሉ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

” ከፋሲል ጋር እቆያለሁ፤ በዚህ ደጋፊው ምንም ሥጋት አይግባው። የብዙ ክለቦችን ጥያቄ ውድቅ ያደረኩት እና ለፋሲል ለመጫወት የወሰንኩት የጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊ አሸናፊዎች ዋንጫን እንዳሳካሁት ሁሉ አሁን ዓምና ከጫፍ ደርሰን ያጣሁትን ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት ነው። ህይወት ከፋሲል ጋር ተመችቶኛል። ከሚወዱኝ ከምወዳቸው ደጋፊዎች ጋር አብሬ መቆየት እፈልጋለው። ፋሲል ብዙ ክብር ያሀኘሁበት ወደ ፊትም ብዙ ነገር የማስብበት በመሆኑ ከፋሲል ውጭ የተም አልሄድም”። ብሏል።

የሱራፌል ወኪል ያሬድ ገብረመድን በበኩሉ “በጣም ብዙ በሀገሪቱ ትላልቅ ክለቦች የስልክ ጥሪዎች እየደረሱኝ ነው። ስምምነቱ ያልፀደቀ በመሆኑ ወደኛ ክለብ ይምጣ የሚል። ሆኖም ደበኛዬ ለጃኖ ማልያ ታማኝ ነው። ለዛ ነው ከቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣልንን ጥያቄ ሳንቀበል ከፋሲል ከነማ ጋር የተስማማነው። ስለዚህ ሱራፌል ለለበሰው ማልያ ለህዝቡ ታማኝ እንደሆነ ማሳወቅ እንፈልጋለን።” ብሏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

error: