አዲሱን የካፍ ኮንቬንሽን በተመለከተ መግለጫ ተሰጠ

ካፍ አዲስ ያፀደቀውን የስልጠና ስምምነት (ኮንቬንሽን) እና ኢንስትራክተሮችን በተመለከተ ከ2 ሰዓታት በላይ የቆየ መግለጫ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ 9 ሰዓት ወሎ ሠፈር በሚገኘው የጽህፈት ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የካፍ የስልጠና ኮንቬንሽንን አስመልክቶ ለብዙሃን መገናኛዎች መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን ለመስጠት በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ እና ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እና የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ስለጉዳዩ ጥልቅ ማብራሪያ ሰጥረዋል። በቅድሚያም የፌዴሬሽኑ ፀሀፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን መግለጫው የተዘጋጀበትን አላማ ካነሱ በኋላ ጉዳዩን በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች ማብራራት ጀምረዋል።

“መግለጫው የተሰናዳው ካፍ ያዘጋጀውን ኮንቬንሽን ለማስረዳት እና በሃገራችን የሚገኙ ኢንስትራክተሮችን በተመለከተ የሚነሳውን ሃሳብ ለማጥራት ነው። ሁላችሁም እንደምታቁት ላለፉት ሦስት ዓመታት ካፍ የኢንስትራክተር ስልጠናዎችን አልሰጠም። ይህ የሆነው ደግሞ ቀድሞ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ክፍተቶች ስላሉበት እና ካፍ ጥራት ላይ መሠረት ያደረገ ስራ ለመስራት አስቦ ነው። ከዚህ መነሻነት የእኛን ሃገር የእግርኳስ ባለሙያዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ በአህጉሪቱ የሚገኙ አሰልጣኞች ምንም ስልጠና ከካፍ አላገኙም።

“ካፍ የሚሰጡትን ስልጠናዎች አቁሞ አዲስ ዘመኑን የዋጀ የስልጠና ኮንቬንሽን አዘጋጅቷል። በዚህ ኮንቬንሽን ውስጥም በዋነነት 8 ነጥቦች አሉ። ነጥቦቹንም በዝርዝር ካፍ በወረቀት አስፍሮ ለአባል ሃገራቱ ልኳል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ይህንን ኮንቬንሽን ተስማምቶበት ፈርሞ ግብረ መልስ ልኳል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ካፍ አባል ሃገራት የራሳቸውን የሆነ የስልጠና መመሪያ (ማኑዋል) እንዲያዘጋጁ አዟል። ፌዴሬሽናችንም ሃገራችን የራሷ የሆነ የተጠና የስልጠና መመሪያ እንዲኖራት ማኑዋል እንዲዘጋጅ ለኢንስትራክተሮች ስራ ሰጥቷል። ኢንስትራክተሮቻችንም ይህንን የስልጠና መመሪያ እያዘጋጁ ነው። መመሪያው ተዘጋጅቶ ከተጠናቀቀ በኋላም በቀጣይ ሃገራዊ የውይይት መድረክ (workshop) ተዘጋጅቶ ባለሙያዎች እንዲያዩት እና እንዲተቹት ከተቻለም ጥሩ ገብአት እንዲሰጡ እናደርጋለን።” ብለዋል።

ከጽሕፈት ቤት ሃላፊው በመቀጠል የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ እና ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ሃሳብ ሰንዝረዋል።

“ዛሬ ከኢንስተራክተሮች ጋር የተያያዘውን የጠራ ነገር እንነግራችኋለን። በተለይ ከኮንቬንሽኑ ጋር የተያያዘውን ዝርዝር ነገር አብርሃም ያቀርበዋል። ከዛ በፊት ግን በተለይ በሃገራችን በሚገኙ ኢንስትራክተሮች ላይ የሚነሳው የተሳሳተ ወሬ ፍፁም ሀሰት ነው። የሚሰጡት አስተያየቶች የእግርኳሳችንን ችግር የሚያስተካክል ሳይሆነ ይባስ ተጨማሪ ችግር የሚሆን ነው። እኔን ጨምሮ በሃገራችን የሚገኙ ኢንስትራክተሮች ከፌዴሬሽኑም ሆነ ከካፍ የምናገኘው ገንዘብ የለም። ሲጀምርም ኢንስትራክተር የሆነው ተምረን እና ተፈትነን ነው። መአረጉን ካገኘን በኋላም ስንሰራ የነበረው ካፍ ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ነው። ስለዚህ በጥቂት ግለሰቦች እየተኬደበት ያለው መንገድ ስህተት ነው። ስልጠናውም የጥራት ችግር አለበት የተባለው አሁን ነው። ስለዚህ እኔን ጨምሮ በሃገራችን የምንገኝ ኢንስትራክተሮች ካፍ ኢንስትራክተርነታችሁን ሰርዣለሁ አላለንም። ስለዚህ የሚነሳው ሃሳብ ፍፁም ስህተት ነው።”

ከኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በመቀጠል የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ አጠር ያለ ሃሳብ ለጋዜጠኞች ካካፈሉ በኋላ ካፍ ያዘጋጀውን እና ኢትዮጵያ ተስማምታ የፈረመችበትን ኮንቬንሽን አስመልክቶ ገለፃ አድርገዋል።

“እንደተባለው መግለጫው የተዘጋጀው በጉዳዩ ዙሪያ የሚነሱ የተሳሳቱ ሃሳቦችን ለማጥራት እና ኮንቬንሽኑን በዝርዝር ለማስረዳት ነው። ካፍ ያዘጋጀው እና ኢትዮጵያ ተስማምታ የፈረመችው ኮንቬንሽን ለሃገራችን እጅግ የሚጠቅም ነው። በዋናነት ደግሞ ሃገራችን ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ላይ ያላትን ቀደምት የእግርኳስ ገናናነት ለመመለስ ይረዳል። ግን ይህ ዝም ብሎ አይመጣም። በሃገራችን የሚገኙ ሁሉም ባለሙያዎች ሲተባበሩ እና የተሻሉ ነገሮችን ለማምጣት ሲጥሩ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የካፍ pro ላይሰንስ የስልጠና እድል ወደ ሃገራችን ከመጣ 10 ወራት ሆኖታል የሚለው ስህተት ነው። በአህጉራችን ይህንን የpro ላይሰንስ ስልጠና የሰጠችነው ብቸኛ ሃገር ሞሮኮ ብቻ ነች። ሞሮኮም ከፈረንሳይ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በትብብር ስልጠናውን አዘጋጅታ ነው። ሌላ ሃገር ግን አልተሰጠም።

“ይህ ኮንቬንሽን የተዘጋጀው ሞሮኮ ራባት ላይ በተደረገ የ1 ሳምንት ስብሰባ ነው። እንደ እድል ሆኖ ሃገራችን ይህንን ኮንቬንሽን ካወጡ ጥቂት የአህጉራችን ሀገራት መካከል አንዷ ናት። በዛ የውይይት ጊዜ በፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ ውይይቱ ተደርጎ ኮንቬንሽኑ በእንግሊዝኛ፣ ፖርቹጊዝ፣ ፈረንሳይኛ እና አረብኛ ተተርጉሞ ለአባል ሃገራት እንዲበተን ተደርጓል።

“በአዲሱ ኮንቬንሽን መሠረት ትምህርቶች በዞን እንዲሰጥ ተወስኗ። በዚህም መሠረት ሃገራችን ኢትዮጵያ በሴካፋ ዞን ማለትም በዞን-14 በሚገኙ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሃገራት ጋር ትምህርቶችን እንድትወስድ ይደረጋል።

“ኮንቬንሽኑ ወደ ሃገራችን ከተላከ በኋላ በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በሚመራው የሃገራችን የኢንስትራክተሮች ፓነል ላይ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። ከዛም ኮንቬንሽኑ ለፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ቀርቦ እንዲፈረም ተደርጓል። ፌዴሬሽኑም ታህሳስ 24 በተላከ ደብዳቤ መስማማቱን ገልፆ ፈርሞ ለካፍ አሳውቋል።

“በኮንቬንሽኑ ላይ ከD እስከ A ድረስ የሚሰጡ ስልጠናዎችን የሚለከት ዝርዝር ነገር ተቀምጧል። እኛም ቀድሞ እንደተባለው ለሃገራችን የሚሆን የስልጠና መመሪያ በዚህ የስልጠና ደረጃ እያዘጋጀን ነው።”ብለዋል።

በኮንቬንሽኑ የተቀመጡ ዝርዝር ጉዳዮች

– በፊት በሦስት ደረጃዎች የሚሰጠው ስልጠና አሁን ወደ አምስት አድጓል። ማለትም D፣ C፣ B፣ A እና pro በሚባሉ ደረጃዎች።

-ከላይ ከተጠቀሱት አምስት ደረጃዎች በተጨማሪ በኮንቬንሽኑ የግብ ጠባቂ፣ የአካል ብቃት እና የፉት ሳል ስልጠናዎችን የሚመለከት የተለየ የስልጠና መንገድ ተዘጋጅቷል።

– የD እና C ላይሰንስ ስልጠናዎችን ማግኘት የሚፈልግ ሰው 18 ዓመት መሆን እና የሃገሪቱን ቋንቋ የሚችል መሆን አለበት። ስልጠናውም በአባል ሃገራት ተመዝግቦ መውሰድ ይችላል።

– የB ላይሰንስ ለማግኘት ቀድሞ የC ላይሰንስ መያዝ ሲገባ በተጨማሪም የC ላይሰንሱን ካገኘ በኋላ ቢያንስ ለ1 ዓመት በስራ ላይ መቆየት ይገባዋል።

– የA ላይሰንስ ለማግኘት የB ላይሰንስን መያዝ እና ፍቃዱን አግኝቶ ለ2 ዓመታት መስራት ይገባል። በተጨማሪም ከካፍ ይፋዊ ቋንቋዎች አንዱን ማወቅ እና የኮምፒውተር እውቀት ማዳበር ይገባል።

– የpro ላይሰንስ ለማግኘት የA ላይሰንስ መያዝ ሲገና ፍቃዱንም አግኝቶ ለ2 ዓመታት ግልጋሎት መስጠት ይገባል። በተጨማሪም የካፍን ይፋዊ ቋንቋዎች የሚያውቅ እና የኮምፒውተር እውቀት ያለው መሆን ይኖርበታል።

– በማንኛውም በአህጉሪቱ የሚገኝ ግለሰብ ስልጠናውን በማንኛውም የአህጉሪቱ ሀገራት ሄዶ መውሰድ ይችላል። ግን የሚሄድበት ሃገር ኮንቬንሽኑን የተቀበለ እና የፈረመ ሃገር መሆን አለበት።

– ለD ላይሰንስ 60 ሰዓታት (20 የክፍል ውስጥ፣ 40 የሜዳ ላይ)፣ ለC 120 ሰዓታት (60 ለክፍል ውስጥ ፣ 60 ለሜዳ ላይ)፣ ለB 170 (60 የክፍል ውስጥ፣ 100 ለሜዳ ላይ)፣ ለA 240 ሰዓታት (100 የክፍል ውስጥ፣ 140 ለሜዳ ላይ) እንዲሁም ለpro 360 ሰዓታት (140 የክፍል ውስጥ፣ 220 ለሜዳ ላይ) ለስልጠና እንደሚያስፈልጉ ተቀምጧል። አባል ሃገራት የስልጠና ሰዓታቱን መጨመር እንዲችሉ መብት የተሰጠ ሲሆን መቀነስ ግን አይቻልም ተብሏል።

– የD ላይሰንስ የምዘና ሰዓት እንደሌለው ነገርግን በስልጠና ወቅት ምዘናዎች እንዲካሄዱ የተቀመጠ ሲሆን ለC 3፣ ለB 4 ፣ ለA 6 እና ለpro ደግሞ 9 ሰዓታት የምዘና ሆነው ተቀምጠዋል።

– የአካል ብቃት እና የግብ ጠባቂ አሠልጣኝ ለመሆን የB ላይሰንስ መያዝ ያስፈልጋል።

– የፉት ሳል አሠልጣኝ ለመሆን የC ላይሰንስ ቀድሞ መያዝ ይገባል።

– የማነቃቂያ ኮርሶችን አባል ሃገራት እንዲሰጡ ነገርግን ትንሹ የማነቃቂያ ኮርስ መስጫ ሰዓት 15 ሰዓት ትልቁ ደግሞ 40 ሰዓት እንዲሆን ተወስኗል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ እግርኳስ ተጫዋቾችን ሆነው ያሳለፉትን ለመጥቀም የሚያስችል ልዩ መስፈርቶች መቀመጣቸው ተመላክቷል። በዚህም መሠረት ከተዘረዘሩት አንዱን ቅድመ ሁኔታ የሚያሟላ የቀድሞ ተጫዋቸ የD እና የ C ላይሰንስ መውሰድ ሳይጠበቅበት በቀጥታ የB ላይሰንስ እንዲወስድ ይደረጋል።

-20 ይፋዊ የዋና ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን ያደረገ

– በማንኛውም የዋና ውድድሮች ላይ ለፍፃሜ ደርሶ የተጫወተ

– በዓለማቀፍ ደረጃ በብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ያልተጫወተ ተጫዋች ቢያንስ በክለብ ደረጃ በሚገኙ አህጉራዊ የክለብ ውድድሮች ላይ ለ30 ጨዋታዎች መሳተፍ የቻለ። ( ከአንደ ድክለብ ጋር ብቻ መሆን አይጠበቅበትም)

-200 ጨዋታዎችን በፕሮፌሽናል ክለብ ወይም በከፍተኛ የሃገሪቱ የሊግ እርከን የተጫወተ

በተለይ በሃገራችን ያለው የመረጃ አያያዝ ችግር ይህንን ጉዳይ እንዴት ያስኬደዋል የሚለው ጉዳይ ትኩረትን የሚስብ ሆኖ ሳለ አቶ ባህሩ እና ኢንስትራክተር አብርሃም ይህንን የመረጃ አያያዝ ችግር ለማስተካከል እንደሚሰራ ጠቁመዋል። ገለፃው ከተደረገ በኋላ በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ጥያቄዎችን ለመድረኩ ሰንዝረው ተጨማሪ ማብራሪያ እና ምላሾች ተሰጥቷል።

ከዚህ ቀደም በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ ስልጠናዎችን ወስደው እስካሁን ሰርተፊኬት ያልተሰጣቸው ሰዎች አለ። የእኑ እጣ ፈንታ ምንድን ነው የሚሆነው?

ልክ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደዚህ አይነት ነገሮችን እየሰማን ነው። ፌዴሬሽናችን ይህንን ነገር ለማጣራት ይሞክራል። እኛ ብቻ ሳንሆን ሌሎች ሃገራቶችም ላይ እንደዚህ አይነት ክፍተት እንዳለ ሰምተናል። ስለዚህ ከካፍ ጋር ውይይቶችን አድርገን ያለውን ነገር እናሳውቃለን። (አቶ ባህሩ ጥላሁን)

ከዚህ ቀደም በምን መስፈርት ነው ኢንስትራክተሮች ተመርጠው የተላኩት?

ኢንስትራክተር ማለት አስተማሪ ማለት ነው። በእግርኳሱ ያለፈ ሁሉ ኢንስትራክተር መሆን ይችላል። ግን ተገቢውን መስፈርት እና መመዘኛ አልፎ። እኔን ፌዴሬሽኑ አደለም መርጦ የላከኝ። ካፍ ነው መርጦ የሰጠኝ። ካፍም ዝም ብሎ አደለም የሰጠኝ። እውቀቴን አይቶ ነው የሰጠኝ። የእኔ ኢንስትራክተርነት በጊዜ የተገደበ አደለም። ግን የማነቃቂያ ስልጠናዎችን መውሰድ እንዳለብኝ አቃለሁ። ስልጠናዎችን እንዳልወስድ ደግሞ ካፍ ስልጠናዎችን መስጠት አቆመ። ስለዚህ ይህ የእኔ ችግር አደለም። የፌዴሬሽንም ችግር አደለም። ከእኔ ውጪ ያሉትን በተመለከተ አሁን ላይ መናገር እችልም። ምክንያቱም በየጊዜው የሚመጡ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚዎች የየራሳቸው መመዘኛዎችን ስለሚያዘጋጁ። (ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው)

የኢንስትራክተሮች የጊዜ ሰሌዳ ማብቂያው መቼ ነው?

የኢንስትራክተርነት መአረግ አንዴ ከተሰጠ መቼም አይጠፋም። እስከምንሞት ድረስ መአረጉ አብሮን ይኖራል። ግን ኢንስትራክተር ሆኖ ስራዎችን ለመስራት በየ ሦስት ዓመቱ የማነቃቂያ ስልጠናዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። (ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ)

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!