የግል አስተያየት | ለእግርኳሳችን የማይጠቅመው የባለሞያዎቻችን ንትርክ [ክፍል ሁለት]

ባለፈው ሳምንት በዚሁ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ግላዊ ምልከታዬን በአስተያየት ዓምድ ላይ ማስፈሬ ይታወሳል፡፡ በዚህኛው ጽሁፌ ደግሞ በተጻራሪ ወገን ሆነው ጉንጭ አልፋ ሙግቱን የሚያጦዙት አካላት ላይ አተኩራለሁ፡፡ በአሰልቺው ንትርክ ውስጥ “ተጫውተው ያለፉ” እና የ”ስፖርት ሣይንስ የተማሩ” በመባል በተፈረጁት ባለሞያዎች መካከል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተደረገ ያለው ክርክር ለኢትዮጵያ እግርኳስ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ጠቅለል ያለ ሃሳቤን ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡
እንደሚታወቀው የእነዚህ ወገኖች የክርክራቸው መነሻ የሚያውጠነጥነው “….የመሥራት ዕድል አልተሰጠንም፤ የተሻለ ለማበርከትም ሁኔታዎች አልተመቻቹልንም፡፡” የሚል ይዘት ያለው አጀንዳ ሆኗል፡፡ ይህ ቅሬታ በዋናነት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፓርት ሳይንስ ትምህርት ተከታትለው በእግርኳሱ አካባቢ በተለያዩ ዘርፎች በተሳተፉ ባለሞያዎች ተዘወትሮ ይነሳል፡፡

“…..በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ መስራት አልቻልንም፤ ተገቢው ቦታ ተነፍጎናል፤ ጭራሹኑ ተገፍተናል፡፡ እግርኳሱን እኛ ብንይዘው ለውጥ ያመጣ ነበር፡፡ እኛን ያላሳተፈው እግርኳስ እድገት ሊያሳይ አይችልም፡፡”  የሚል ተደጋጋሚ አስተያየት የሚሰጡት ደግሞ ቀደም ሲል በተጫዋችነት ያሳለፉት አካላት ናቸው፡፡

ለመሆኑ እነዚህ የእግርኳስ ባለሞያዎች የሚከራከሩበት አጀንዳ ሚዛናዊ ነው? መነሻ ሐሳቦቻቸውስ እውነታ አላቸው? ለዚህ ንዝንዝ-መሰል ጉዳይ እንግዳ ለሆኑ የእግርኳስ ቤተሰቦች ነገሩን ግልፅ ለማድርግ ታስቦ ይህ አስተያየት መጻፉን ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ በቅድሚያ “በስፓርት ሳይንስ የተማሩ ባለሞያዎች በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የማሰልጠን እና በተለያዩ ኃላፊነቶች የመሳተፍ እድል ተነፍገዋልን?” ብዬ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ “ተጫውተው ያለፉትስ ቢሆኑ እስካሁን በነበራቸው-አሁንም ባላቸው የማሰልጠን ጉዞ የሃገራችንን እግርኳስ የመለወጥ እድሎችና አጋጣሚዎች አልነበራቸውም ወይ?” የሚል ጥያቄ ማንሳትም የግድ ነው፡፡ የእነዚህ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ በየጊዜው የሚነሳው ረብ የለሽ ክርክር ለእግርኳሳችን አንዳችም የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ያሳየናል፡፡ በኢትዮጵያ የእግርኳስ አሰልጣኝነት መድረክ ሁለቱም አካላት “የማሰልጠን በቂ እድል አላገኘንም፡፡” ካሉ ታዲያ ማን ነው እያሰለጠነ የነበረው- አሁን እያሰለጠ ያለውስ? ለጥያቄዎቹ በሚቀርበው መልስ በሁለቱም ጎራ የሚገኙት ተከራካሪ ባለሞያዎች ባለፉት ሃያ ዓመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ  የነበራቸውን ተሳትፎ ስናይ ክርክሩ ምክንያታዊ አለመሆኑን እንረዳለን፡፡ የሃገሪቱን እግርኳስ በአዎንታዊ ገጽታ ለመለወጥ የነበራቸውን እድል እንዳልተጠቀሙበትም እናያለን፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ባለሙያዎቹ በተለይ በክርክሩ ጽንፍ ይዘው የቆሙት ወገኖች እውቀታቸውን በአግባቡ ለሌሎች ከማካፈልና ራሳቸውም በሙያቸው የተሻለ ለማበርከት ከመጣር ይልቅ እግርኳሳችንን ለመለወጥ የበኩላቸውን አድርገው ማለፍ ሲገባቸው በከንቱ እዬዬ ጊዜያቸውን እያባከኑ መሆናቸውን አንባቢው እንዲረዳ እፍልጋለሁ፡፡

የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች    

ቀደም ብዬ በተለያዩ አስተያየቶች ለማንሳት እንደሞከርኩት እግርኳስ በአንድ የሙያ ዘርፍ ላይ ብቻ በሚደረግ ርብርብ ወይም ጥረት አያድግም፡፡በኢትዮጵያ እግርኳስ ከባቢ ውስጥ ከስልጠናው ባሻገር ሌሎች ብዙ ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ባለፉት ዓመታት ጎራ ለይተው ተከራካሪዎች የሆኑት የሥልጠና ባለሙያዎች እግርኳሱ የተዘፈቀባቸውን ችግሮች ተቋቁመው ለሃገራችን እግርኳስ እድገት አዎንታዊ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉበት እድሎች ነበሯቸው፡፡ በመጀመሪያ የስፓርት ሳይንስ ባለሞያዎች የነበራቸውን እውቀትና ልምድ በመጠቀም፣ አቅማቸውን በማሳየት እና ትምህርታቸውን በተግባር ወደ መሬት በማውረድ ረገድ የኢትዮጵያን እግርኳስ መለወጥ ይችሉ የነበሩባቸውን እድሎች እንመልከት፡፡ እዚህ ጋር እንዲታወቅልኝ የምፈልገው አስተያየቴ የሚመለከተው በዚህ ክርክር ውስጥ ይብዛም-ይነስ እየተሳተፉ ያሉትን አካላት ነው፡፡ የአስተያየቱ ዓላማም መተቸት ብቻ ሳይሆን ባለሙያዎቹ ቆም ብሎ ስህተታቸውን እንዲያዩ እና አቅጣጫቸውን እንዲያስተካክሉ ይሆናል፡፡
” በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉ ክለቦችን ካላሰለጠንን ለውጥ ማምጣት አንችልም፡፡” ካላሉ በስተቀር የስፓርት ሳይንስ ባለሞያዎች ወረድ ባሉ እርከኖች ብዙ የመስራት እና ለውጥ የማምጣት እድል ነበራቸው፡፡

የስፖርት ሳይንስ ባለሞያዎች ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉበት የመጀመሪያው ቦታ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የአካዳሚው አጠቃላይ ግንባታ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ከፍተኛ አበርክቶ እንደሚኖረው ብዙ የተባለለት ይህ ማዕከል ስራውን ከጀመረ አስር ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም በምልመላ ሥርዓቱ፣ በስልጠና ጥራቱ፣ በሰልጣኞች አያያዙ፣ በአስተዳደራዊ መዋቅሩ እና በሌሎችም መስኮች የተለየ የሚባል ፍሬ ሳያሳይ ይኸው ነባር ጉዞውን እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ በቁጥር በርከት ባሉ የስፓርት አይነቶች የሚሳተፉ ታዳጊዎችን ለማሰልጠን ታስቦ የተመሰረተው አካዳሚ በእግርኳሱ እንደሌሎች ክለቦች ሁሉ ከ17 ዓመት በታች፣ ከ20 አመት በታች እና በሴቶች ዘርፍ በውድድሮች ላይ ተሳታፊ ከመሆን ውጪ በግል ተቋቁመው ከሚሰሩ የታዳጊ ፕሮጀክቶች እምብዛም የተለየ ውጤት አላሳየም፡፡በእርግጥ አካዳሚው-በተለይ ለአሰልጣኞቹ- የተሻለ ስኬት እንዳያገኙ አያሌ ማነቆዎች ያሉበት ቢሆንም በዘረጋው የምልምላ አድማስ፣ በያዘው የመገልገያ መሳሪያዎች መጠን፣ ባለው አመቺ የስፖርት ማዘወተሪያ መሰረተ ልማት እና በሚመደብለት በጀት ሲታይ ከሌሎች በግል ከተቋቋሙ ፕሮጀክቶች አንጻር የተሻለ አስተዋፅኦ ማበርከት ነበረበት ባይ ነኝ፡፡ ይህ አካዳሚ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ በማሰልጠን- አልፎ አልፎም በአመራር አካልነት ጭምር በስፓርት ሳይንስ የተማሩ ባለሞያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ይሁን እንጂ ባገኙት ዕድልም ሆነ በተሰማሩበት የሥራ መደብ ሰርተው አቅማቸውን ለማሳየትና የሃገራችን እግርኳስ ላይ መጠነኛ ለውጥ ለማምጣት የቻሉ አልመሰለኝም፡፡ ብዙውን ጊዜ የእግርኳስ ችግራችን መሰረቱ የሚገኝበት “ታችኛው” የሥልጠና ቦታ እንደሆነ ይነገራል፡፡ እዚህኛው ከባቢ ላይ የመስራቱ አጋጣሚ ትልቅ ችግሩን ለመቅረፍ ጥሩ እድል ይሆን ነበር ባይ ነኝ፡፡

በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የተጠነሰሰው  <የአምቦ ጎል ፕሮጀክት> ሌላው የስፓርት ሳይንስ ባለሞያዎች የተሳተፉበት ቦታ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀከት በፊፋ የተመሰረተ ሲሆን ይህንን ማዕከል በመምራት እና በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ሰልጣኞችን በማሰልጠን በኩል ሙሉ ለሙሉ የስፓርት ሳይንስ ባለሞያዎች መሳተፋቸው ይታወሳል፡፡ ይህ የአንቦ ጎል ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ ወጥተው የእግርኳስ ደረጃቸው ከፍ ባሉ ሃገራት የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ባያፈራ እንኳ በሃገራችን እግርኳስ በንጽጽር በትልቅ ደረጃ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ማፍራት ይገባው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ለረጅም ዓመታት በነበረው ህልውና እ፡ይህንን ማድረግ ሳይችል ቀርቷል፡፡ የተገኘን የመሥራት እድል ተጠቅሞ ተተኪዎችን ማፍራት ሲቻል ምንም የረባ ውጤት ሳያስመዘገብ ይከው እስካሁንም  የአምቦው ፕሮጀክት ባለበት ይረግጣል፡፡

ሌላኛው የስፖርት ሳይንስ ባለሞያዎች ለረጅም ጊዜ በስፋት የሠሩበት ቦታ የኢትዮጵያ የታዳጊዎች ፕሮጀክት ስልጠና ነው፡፡ በስፖርት ኮሚሽን ይደገፍ በነበረው የታዳጊዎች ፕሮጀክት በመላ ሃገሪቱ በርካታ ማዕከላትን በመያዝ ሲሰራ ቆይቷል፡፡እነዚህን የታዳጊ ፕሮጀክቶች የሚመሩት ሙሉ በሙሉ የስፓርት ሳይነስ ባለሞያዎች የነበሩ ሲሆን ከሚያሰልጥኑት ባለሙያዎችም አብዛኞቹ እነርሱ ናቸው፡፡ በወረዳ፣ በክፍለ ከተማ እና በከተማ ደረጃ ያሉትን የስልጠና ሒደቶች ክትትል የሚያደርጉትም የስፓርት ሳይንስ ባለሞያዎቹ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ለስልጠና እና ለወድድር ተብሎ ብዙ ገንዘብ የሚወጣበት ይህ የታዳጊዎች ፕሮጀክት ብዙ ገንዘብ ከማባከኑ ውጪ በሃገሪቱ እግርኳስ ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ሚና አልተጫወተም፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ በአንድ ዓመት ውስጥ ተገቢውን ስልጠና የማያገኙ ልጆችን በመሰብሰብ አንዳንዴ ከክለብ ታዳጊ ቡድኖችም ጭምር ተጫዋቾችን በመምረጥ በዓመቱ መጨረሻ ውድድር ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ እጅጉን ደካማ  የሥልጠና ሥርዓት በታየበት በዚህ ፕሮጀክትም ሆነ በውድድሩ ላይ ወደ ፖለቲካዊ አድልኦ የሚያጋድል አዝማሚያ ከማሳየት እና የተወሰኑ ግለሰቦችን ኪስ በአበል ከመሙላት ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም፡፡ ለዚህ ዓይነቱ የሃገሪቱ እግርኳስ መልክ ከዳረጉን ተግባሮቻችን መሃል ተራ የስልጠና እና የውድድር መርሃግብሮች አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፈዋል፡፡ በዚህ የአሰራር ድክመታችን ሳቢያ ለተላመድነው ውድቀታችን ዋነኛዎቹ ተጠያቂዎች በዘርፉ ቀጥተኛ ተጠሪዎች ከነበሩት የስፓርት ሳይንስ ባለሞያዎች የበለጠ ድርሻ የነበራቸው አካላትን መጥቀስ አስቸጋሪ ነው፡፡

ምንም እንኳ ብዙ አስተዳደራዊ ችግሮች ቢኖሩም በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና በአንዳንድ የክልል ፌዴሬሽኖች እንዲሁም በጥቂት ክለቦች ውስጥ እንዚህ ባለሞያዎች እምነት ተጥሎባቸው ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ የቴክኒክ ዳይሬክተር በሚያስፈልግበት የታዳጊዎች ስልጠና ላይ ለውጥ የማምጣት እድል የነበራቸው ቢሆንም ባገኙት የመሥራት አጋጣሚ አንዳቸውም በጎ አሻራቸውን ለማሳረፍ ሲሞክሩ አይታዩም፡፡ በዚህም ምክንያት ከፊሎቹ ሚናቸው ምን እንደሆነ እንኳ ሳይውቁ ከዋናው ቡድን አሰልጣኞችና ከአመራሮች ጋር በመላተም መጨረሻቸው ሥራቸውን መልቀቅ ሲሆን ብዙዎች ታዝበናል ፡፡

በሌላ በኩል እነዚህን ባለሞያዎች ያስተማሩት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንጻራዊ በሆነ መልኩ ለእግርኳስ የተመቻቸ ከባቢ አላቸው፡፡ የተወሰኑ ዩንቨርሲቲዎች ቀደም ባለው ዓመታት የአዋቂዎች ቡድን በመመስረት በውድድሮች ላይ ሲሳተፉ እናስታውሳለን፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ አብዛኞቹ የትምህርት ተቋማት የታዳጊ ፕሮጀክቶችን በማቋቋም ከ”ታች” ለመስራት ጥረት እያደረጉ እንደሆኑም ይታወሳል፡፡ እንደሚታወቀው በዓለም አቀፍ ደረጃ  በርካታ ስፓርተኞች ከዩንቨርሲቲዎች ይወጣሉ፡፡ በእኛም ሃገር ኮሌጆች ወይም ዩንቨርሲቲዎች ይህንን ለማድረግ  አቅም አላቸው፡፡ የስፓርት ሳይንስ ምሩቃንም ይህንን እድል ለመጠቀም የረጅም ጊዜ ስልታዊ እቅድ በመንደፍ እግርኳሳችን ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ስራ መስራት፥ አቅማቸውን ማሳየትም ይችላሉ፡፡ ለዚህ የሚያስፈልገው ቁርጠኝነት ብቻ ይመስለኛል፡፡

እንግዲህ ከላይ ለመዘርዘር እንደሞከርኩት በሃገራችን እግርኳስ የስፓርት ሳይንስ ባለሞያዎች -አንዳንዶቹ እንደሚሉት ሳይሆን በመሪነት፣ ተጫዋቾችን በማሰልጠን፣ አሰልጣኞችን በማሰልጠን፣ የእግር ኳሰችንን ችግር በማጥናት፣ በቴክኒክ ዳይሬክተርነት እና ሌሎችም ቦታዎች ላይ የመስራት እድል አግኝተዋል፡፡ እነዚህ ቦታዎች የሃገራችንን እግርኳስ ለመለወጥ ትልቅ እድል መፍጠር የሚችሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን በተመለከተ ግን በብልሹ አሰራር የተሞላ ፣ የአሰልጣኞች የቅጥር መስፈርት ምን እንደሆነ የማይታወቅበት፣ አንድ አሰልጣኝ ያለምንም ውጤት በርካታ ክለቦችን የሚያዳርስበት እና በበርካታ ችግሮች የተተበተበ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህም በዚህ ክርክር የሚሳተፉ ስፓርት ሳይንስ ባለሞያዎች ቆም ብለው ቢያስቡ መልካም ነው ባይ ነኝ፡፡

በተጫዋችነት ያሳለፉት

ባለፈው ሳምንት ጠቀስ አድርጌ እንዳለፍኩት በኢትዮጵያ እግርኳስ በተለያዩ የሊግ እርከኖች  የተጫወቱና የአሰልጣኝነት ደረጃ ላይ የደረሱ ወገኖች “እግርኳሱን እኛ ካልያዝነው ለውጥ አይመጣም፡፡ ‘ከእኛ ውጪ ላስር!” እያሉ ነው፡፡ይህንን ስል ግን ሁሉንም ማለቴ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ጥቂቶች የዚህ ሃሳብ አቀንቃኝ ሆነው አደባባይ ከወጡ ሰንበትበት ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ በቀደሙት ዘመናትም ይሁን በአሁኑ ጊዜ በማሰልጠን የአንበሳውን ድርሻ የያዙት ተጫውተው ያለፉት አሰልጣኞች ናቸው፡፡በወቅቱ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦቻችን ያሉትን እንጥቀስ ብንል እንኳ ፡-ገብረመድህን ኃይሌ፣ ውበቱ አባተ፣ ካሳዬ አራጌ፣ ፋሲል ተካልኝ፣ ስዩም ከበደ፣ አሸናፊ ከበደ፣ ጳውሎስ ጌታቸው፣ ሙሉጌታ ምህረት እና ስምዖን ዓባይ የተወሰኑትን ይወክላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በከፍተኛው ሊግና በብሄራዊ ሊግ ከሚያሰለጥኑት አሰልጣኞችም አብዛኞቹ ተጫውተው ያለፉት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአልጄሪያውን አዋራጅ ሽንፈት ሲቀዳጅም ሆነ ታዳጊና ወጣት ቡድናችን ለብዙ ዓመታት በውጤት ቀውስ ውስጥ ሲዳክር አብዛኞቹ አሰልጣኞች ተጫውተው ያለፉት ነበሩ፡፡

በኢትዮጵያ የክለቦች አሰልጣኝነት ነባር የቅጥር ልማድ ይህንኑ ሒደት የሚመሰክር ነው፡፡በተመሳሳይ ሁኔታ በታዳጊና ወጣት ቡድኖች ውስጥም ላለፉት በርካታ ዓመታት ሥልጠናውን ሲመሩ የከረሙት አብዛኞቹ አሰልጣኞች ቀደም ሲል ተጫውተው ያሳለፉት ናቸው፡፡ በእርግጥ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት በሃገራችን እግርኳስ ላይ አመርቂ ውጤት ለማምጣት ተገቢው ስራ በሁሉም ስፍራ መሰራት ይኖርበታል፡፡ በበርካታ ችግሮች ተጠፍንጎ የተያዘውን እግርኳስ ” እኛ ብንይዘው ይለወጣል፡፡” ይሉናል፡፡ እስካሁን ከጠቀስኳቸው እድሎች በላይ ምን ያግኙ? ምናልባት ብዙ ዓመት እግርኳሱ ላይ ካልሰራው የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ውጪ ሁሉም ይህንኑ እድል አግኝተዋል፡፡ እርግጥ ጥሩ የአሰልጣኝነት ብቃት ኖሯቸው የመሥራት “እድል ያልተፈጠረላቸው” አሰልጣኞች አሉ፡፡ ችሎታ ይዞ እንኳ በእግርኳሳችን መሥራት መቻል ከእድል መቆጠሩ ያስገርመኛል፡፡ ይህ ደግሞ ከዚህ ቀደም እንደተጠቀሰው አሰልጣኞች የእግርኳስ ዘርፍ ላይ በተለይም በአሰልጣኝነት ሙያ የቅጥር መስፈርቱ ችሎታና አቅም (Merit) አለመሆኑ ያመጣው ችግር ነው፡፡

በ1990ዎቹ መጀመሪያ በሃገራችን እግርኳስ ላይ ጥናት ተደርጎ መሰረታዊ ችግራችን “ከታች” ታዳጊዎች ላይ አለመሰራቱ እንደሆነ ተነገረ፡፡ከዚያም ቀጠለና በታዳጊዎች ሥልጠና ፍሬያማ አለመሆን ደግሞ የታዳጊዎቹ አሰልጣኞች “ተጫውተው ባለማለፋቸው” ነው ተባለ፡፡ ቆይቶም “የስፖርት ሳይንስ ባለሞያዎች” በስልጠናው ላይ አለመሳተፋቸው የውጤታማነት ችግር እንዳስከተለ ተጠቀሰ፡፡ ስለዚህም እነዚህ ተከታታይ “ክፍተቶች” ቀርበው መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ሲደረግ “ተጫውተው ያለፉትን” እና “የስፓርት ሳይንስ ባለሞያዎችን” በጋራ በማጣመር በተለያዩ የስልጠና ማዕከላት እንዲሰሩ ተወስኖ ነበር፡፡እውነታው ግን ይህኛውም መፍትሄ የተለየ ስኬት ያላመጣ መሆኑ ነበር፡፡

ተጫውተው ያሳለፉና ኋላ አሰልጣኞች የሆኑት የእግርኳስ ባለሙያዎች ከታዳጊ ስልጠና አንስቶ በሃገሪቱ ደረጃ ትልልቅ ቡድኖች እስከማሰልጠን ድረስ ሰርተዋል፡፡ ሆኖም ቀደም ብዬ በጠቀስኳቸው መንገዶች “ይህ ነው!” የሚባል ውጤት አላስመዘገቡም፡፡ ተመሳሳይ የአጨዋወት ሥልት ተከትለው ዋንጫን ደጋግመው ሲያሸንፉ አላየንም፤ ለጀማሪ እና ወጣት አሰልጣኞች ተምሳሌት የሆነ የተጫዋቾች አያያዝ ሥርዓት ሲዘረጉ አልታዘብንም፤ ለሌሎች አስተማሪ የሚሆን የአጨዋወት ፍልስፍና ኖሯቸው በተግባር ሲያውሉ ለመመልከት አልታደልንም፡፡ በተለይም በኢትዬጵያ ፕሪሚየር ሊግ የማሰልጠን እድል ያገኙ አሰልጣኞች ዋናውን ቡድን ከማሰልጠን አልፈው በታደጊና በወጣት ቡድኖች ውስጥ ተመሳሳይ አጨዋወት እንዲንሰራፋ እና ክለቦች በራሳቸው የጨዋታ ዘይቤ ለረጅም ጊዜ ውጤታማ እየሆኑ  እንዲሄዱ ሲያደርጉ አልታየም፡፡ አዳዲስና ዘመናዊ የስልጠና መንገዶችን እና የቡድን ግንባታ ስልቶችን አላመጡም፡፡ ከሁሉም በላይ በመጽሃፍ ደረጃ በሙያቸው ያሳለፉትን ውጣ-ውረድ፣ ተግዳሮቶች፣ ያለፉባቸውን እግርኳሳዊ ተመክሮ ለቀጣዩ ትውልድ አላስቀመጡም፡፡ የሥልጠና መመሪያ፣ የአመራር ዘዴ ወይም “ማንዋል” አልተዉልንም፡፡

በሌላ በኩል ከእነዚህ የቀድሞ ተጫዋቾች መካል አንዳንዶቹ ” እኛ የሰለጠንበት መንገድ ልክ አይደለም፡፡ በተሳሳተ የሥልጠና አካሄድ እዚህ ደርሰናል፡፡” ሲሉ እንሰማለን፡፡ ታዲያ እነዚህ በተጫዋችነት ያሳለፉና አሰልጣኞች የሆኑት አካላት “በተሳሳተ የስልጠና ሥርዓት ያለፉ ከሆነ በመጫወታቸው ያገኙት የተለየ ጥቅም ምንድን ነው?” የሚለውንም ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስልኛል፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ አሁንም በጣም ኋላ-ቀር የሆነ የሥልጠና መንገድ እንደሚከተሉ ይታወቃል፡፡ በአንድ ወቅት እንደ አጋጣሚ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተገኝቼ እንዳስተዋልኩት የአንድ ትልቅ ፕሪሚየር ሊግ ቡድን 5፡00 ሰዓት ላይ በነበረው የልምምድ ፕሮግራም አሰልጣኙ ከመደበኛ ልምምዱ በፊት ተጫዋቾችን ለአንድ ሰዓት ያህል በጠራራ ጸሃይ ትጥቃቸውን እንደለበሱ ካወራቸው በኋላ ለሁለት ሰዓት ተኩል ያህል ልምምድ እንዳሰራቸው መታዘብ ችያለሁ፡፡ እስቲ በከፍተኛ ሊግ እና በብሄራዊ ሊግ የሚካሄዱትን የክለቦች ጨዋታ ተመልከቱ፡፡ የእረፍት ሰዓት አጠቃቀማችን በራሱ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ በተለይም የረባ አጥር በሌላቸው ሜዳዎች ላይ የሚጫወቱ ቡድኖች በእረፍት ሰዓት ተጫዋቾቹ በደጋፊ ተከበው አስራ አምስት ደቂቃ ሙሉ ይጨቀጨቃሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ይህንን ኹነት ሳይ ወደ አዕምሮዬ አንድ ተደጋጋሚ ጥያቄ ይመጣል-“የተጫዋቾቹ የእረፍት ሰዓት መቼ ነው?” የሚል፡፡ እነዚህኞቹ ከሌሎች በርካታ  ችግሮቻችን ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ከተመለከትነው ተጫውተው ያለፉትም ሆነ የስፖርት ሳይንስ የተማሩ አሰልጣኞች በኢትዮጵያ እግርኳስ በማሰልጠን ሙያ ሰርተው ያሳዩን ተዓምር የለም፤ በአለም ዓቀፉ የእግርኳስ ደረጃ ወደላይ እንድንንደረደር እንኳ አላገዙንም፡፡ ከኋሊት ጉዟችን አልገቱንም፡፡ “ስኬት አንጻራዊ ነው፡፡” በሚል አባባል ንጽጽራችን እዚሁ ሃገራችን ተገድቧል፡፡ ማናቸውም  ከፍ ወዳለው የእግርኳስ ደረጃ አላሻግሩንም፡፡ እኛ ደግሞ “እገሌ ያሰልጥን! እገሌ አያሰልጥን!” በሚል አሰልቺ ሙግት እንነታረካለን፡፡

እንግዲህ በሁለቱም ሳምንታት እንዳነሳሁት የስፓርት ሳይንስ ባለሞያዎችም ሆኑ እግር ኳስን ተጫውተው ያሳለፉት አሰልጣኞች ይብዛም-ይነስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ በማሰልጠን ተሳትፈዋል፡፡ እግርኳሰችን ግን አሁንም የቁልቁለት ጉዞውን እንደቀጠለ ነው፡፡ ተጠቃሽ አዎንታዊ ጎን የሌለው እግርኳሳችን የማይረባ ክርክር አይሉት ንትርክ ሲታከልበት ምን ሊመስል እንደሚችል አስቡት፡፡ የእውቀት አድማሳችንን በማስፋት፣ የጋራ ስራን በማበረታታት፣ መደማመጥንና መከባበርን በማሳደግ እግር ኳሰችንን ማሳደግ ስትችሉ እባካችሁ የጎሪጥ እየተያያቹና እየተወዛገባቹ እኛንም አታወዛግቡን፡፡ ስለእውነት አንዳንዶቻቹ በመገናኛ ብዙሃን ቀርባቹ ስለዚህ ጉዳይ ስታወሩ የምታቀርቡት መከራከሪያ ሐሳብ ውሃ የማያነሳ መሆኑ ያሳፍራል፡፡ “ከእኔ በላይ ላሳር!” ባዮችም አላችሁ፡፡ እውነታው ግን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ረብ ያለው ነገር አለማበርከታችሁ ነው፡፡ በእግርኳስ ስልጠና ምሉዕ የሆነ ባለሙያ የለም፡፡ እነ ፔፕ ጓርዲዮላ እንኳን በስራቸው ብዙ ባላሞያዎችን በማሳተፍ ጠንክረው ለመስራት ይተጋሉ፡፡ እናንተም ሥራው በእጃችሁ እስካለ ድረስ ተነጋገሩ፣ ተቀራረቡ፣ ተደጋገፉ፣ አብራችሁ ለመስራት ሞክሩ፡፡ ከከንቱ ንትርክ ውጡና ከእናንተ የምንጠብቀውን ብቻ አሳዩን፡፡  

🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻


ስለ ፀሐፊው

የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ  ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: